ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ስሑል ሽረ

ወላይታ ድቻ እና ስሑል ሽረ በሶዶ ስቴድየም የሚያደርጉትን ጨዋታ የዛሬ ቀዳሚ ዳሰሳችን አድርገነዋል።

በመጀመርያው ሳምንት ሲዳማ ቡናን ካሸነፉ በኃላ ወደ ድል መመለስ ያልቻሉት የጦና ንቦች ከአስከፊው አጀማመር ለመውጣት ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል።

ባለፈው ሳምንት በሜዳቸው ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ የተለያዩት ወላይታ ድቻዎች ከመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ማሳካት የቻሉት ሦስት ነጥቦች ብቻ ነው።

የወላይታ ድቻ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ አቻ

የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መሰረት ያደረገ እና የመስመር አጨዋወት መርጠው ጨዋታዎቻቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙት የጦና ንቦች በነገው ወሳኝ ጨዋታም በራሳቸው ምርጫም ይሁን በተጋጣሚያቸው የአጨዋወት ባህርይ ምክንያት በኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት ያደረገ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቡድን ከውጤት ማጣት ጋር በተያዘ ጫና ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች አንዱ እንደመሆኑ የደጋፊውን ተቃውሞ ለማርገብ ነገ በሙሉ ኃይሉ ማጥቃቱ አይቀሬ ነው። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ስሑል ሽረ በተደራጀ ሁኔታ ተጠቅጥቆ የሚከላከል በመሆኑ በቀላሉ አስከፍተው ጎሎች ለማስቆጠር ሊቸገሩ ይችላሉ።

ባለፉት ጨዋታዎች በርካታ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ያላሰለፉት የጦና ንቦች በነገው ጨዋታም መኳንንት አሸናፊ፣ ነጋሽ ታደሰ እና ያሬድ ዳዊትን በጉዳት አያሰልፉም።

የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
አሸነፈ አቻ አቻ አቻ ተሸነፈ

ባሳለፍነው ሳምንት ከተከታታይ አቻ ውጤቶች በኋላ ሰበታ ከተማን አሸንፈው ደረጃቸውን ያሻሻሉት ስሑል ሽረዎች ከከባዱ የሜዳ ውጭ ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ አሳክተው ለመመለስ ወደ እንደሚገቡ ይገመታል።

ባለፉት የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ጠጣር እና በጥብቅ የሚከላከል ቡድን ይዘው የቀረቡት ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ ለተጋጣሚ ክፍተት የማይሰጥ ቡድን ይዘው እንደሚቀርቡ ይገመታል። ኳስ ተቆጣጥሮ ለሚጫወት እና ማጥቃት ላይ አተኩሮ ለሚቀርብ ቡድን በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የማይቸገሩ በመሆኑ ነገም መልሶ ማጥቃት ዋነኛ የቡድናቸው የማጥቂያ መንገድ እንደሚሆን ይታመናል።

በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች የኃላ ጥምረታቸው ላይ ተጫዋቾች እያቀያየሩ የተጠቀሙት ሽረዎች በነገው ጨዋታ ግዙፉ ተከላካያቸው አዳም ማሳላቺ በጉዳት ማጣታቸውን ተከትሎ በጥምረቱ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊም በጉዳት ወደ ሶዶ አልተጓዘም።

እርስበርስ ግንኙነት

– የነገው ተጋጣሚዎች በሊጉ ሁለት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሶዶ ላይ 1-1፣ ሽረ ላይ 0-0 ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

መክብብ ደገፉ

ፀጋዬ አበራ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – እዮብ ዓለማየሁ

ተስፋዬ አለባቸው

ዘላለም ኢያሱ – እድሪስ ሰዒድ – በረከት ወልዴ – ዳንኤል ዳዊት

ባዬ ገዛኸኝ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ምንተስኖት አሎ

ክብሮም ብርሀነ – በረከት ተሰማ – ዮናስ ግርማይ – ረመዳን የሱፍ

ነፃነት ገብረመድህን – አክሊሉ ዋለልኝ

ዲድየ ለብሪ – ያስር ሙገርዋ – ዓብዱለጢፍ መሐመድ

ሳሊፍ ፎፋና


© ሶከር ኢትዮጵያ