ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ሠራተኞቹ መቐለ 70 እንደርታን የሚያስተናግዱበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ የያዙት ወልቂጤዎች በደጋፊያቸው ፊት የመጀመርያ ድል በማስመዝገብ ደረጃቸውን ማሻሻልን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የወልቂጤ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
ተሸነፈ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

እንደተጋጣሚያቸው አጨዋወት የሚቀያየር አቀራረብ ያላቸው ባለሜዳዎቹ ባለፉት ጨዋታዎች ሲያስፈልግ ኳስ ተቆጣጥሮ የሚጫወት በተቀሩት ደሞ ቀጥተኛ ኳስ የሚጠቀም ቡድን ያሳዩ ሲሆን በነገው ጨዋታ ግን ከተጋጣሚያቸው የመከላከል ጥንካሬ አንፃር ተነጥሎ በሚጫወተው አጥቂው ጃኮ አረፋት መሰረት ያደረገ ቀጥተኛ አጨዋወት ይመርጣሉ ተብሎ አይጠበቅም።

በነገው ጨዋታ ሁለቱም መስመሮች ላይ ትኩረት ያደረገ የማጥቃት አጨዋወት ይከተላሉ ተብለው የሚጠበቁት ወልቂጤዎች በተለይም ጥሩ ወቅታዊ ብቃት በሚገኘው ጫላ ተሺታ በሚሰለፍበት መስመር ዋነኛ የማጥቂያ መንገዳቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

ሠራተኞቹ በነገው ጨዋታ ቶማስ ስምረቱ እና አዳነ በላይነህን በጉዳት አዳነ ግርማ እና ፍፁም ተፈሪን ደግሞ በግል ጉዳይ ምክንያት አያሰልፉም።

በስድስተኛው ሳምንት በፈረሰኞቹ ከገጠማቸው ሽንፈት ውጪ ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ወደ መሪው የተጠጉት መቐለዎች በነገው ጨዋታም ሦስት ነጥብን አልመው ይገባሉ ተብሎ ይገመታል።

የመቐለ 70 እንደርታ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ አቻ

በሊጉ መጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ከተከተሉት አጨዋወት የተወሰነ ለውጥ አድርገው አጥቂዎቹ ላይ መሰረት ያደረገ ቀጥተኛ አጨዋወት በመተግበር ላይ የሚገኙት መቐለዎች በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ምዓም አናብስት በሊጉ መጀመርያ ላይ ጠንካራ የተከላካይ ጥምረት ለመፍጠር ተቸግረው የነበሩ ቢሆንም በሒደት ችግሩን እየቀረፈ ይገኛል። ሆኖም ቡድኑ ከነገ ተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃር የቆሙ ኳሶች መከላከል ላይ ያለውን ችግር ቀርፎ መግባት የግድ ይለዋል።

ምዓም አናብስት በነገው ጨዋታ በረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው ሚካኤል ደስታ ውጪ በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ይበልጣል ሽባባው – ዐወል አህመድ – ዳግም ንጉሴ – አቤኔዘር ኦቴ

ኤፍሬም ዘካሪያስ – በረከት ጥጋቡ – አብዱልከሪም ወርቁ

ሄኖክ አወቀ – ጃኮ አራፋት – ጫላ ተሺታ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – ላውረንድ ኤድዋርድ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ዮናስ ገረመው – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ዳንኤል ደምሴ – ያሬድ ከበደ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦኪኪ ኦፎላቢ


© ሶከር ኢትዮጵያ