ሪፖርት | ፈረሰኞቹ እንደምንም ከድሬዳዋ ከተማ ሦስጥ ነጥብ ወስደዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን አዲስአበባ ላይ እየተንገዳገደ የሚገኘውን ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል። ሁለቱ አጥቂዎቹም ባጋጠማቸው ጉዳት ተቀይረው ከሜዳ ወጥተዋል።

ፈረሰኞቹ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀዋሳ አቅንቶ ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው የቡድን ስብስብ ምንም ቅያሬ ሳያደርጉ ወደ ዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በሜዳው በወልዋሎ ሽንፈት ካስተናገደው የቡድን ስብስብ ውስጥ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሬ በማድረግ አዲሰገን ኦላንጂ እና ያሬድ ዘውድነህን ወደ ሜዳ በማስገባት የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

የቀድሞው የፈረሰኞቹ አለቃ የነበሩትና በቅርቡ ከዛማሌክ አሰልጣኝነታቸው ተሰናብተው ክለብ አልባ የሆኑት ሰርዮቪች ሚሉትን “ሚቾ” በስታዲየም ተገኝተው የተከታተሉት ጨዋታ ገና በ4ኛው ደቂቃ ነበር ጎል የተቆጠረበት። ሀይደር ሸረፋ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ጌታነህ ከበደ በጭንቅላቱ በመግጨት ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎል በጨዋታው በመጀመሪያ ሙከራ ማስቆጠር ችሏል።

ድሬዳዋ ከተማዎች ከሰሞኑ ከፍተኛ ስህተቶች ይስተዋሉበት የነበረውን የመከላከል አወቃቀራቸው ላይ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት በማሰብ በዛሬው ጨዋታ በ5 ተከላካዮች ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። ምንም እንኳን በተጫዋቾቹ ዘንድ በዛሬው እየዕለት ለነበረው የተጫዋቾች አደራደር ትግበራ ላይ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃ መተረማመሶች በስፋት ሲስተዋሉ ነበር።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያ ደቂቃ በተቆጠረችው ግብ የተነሳ በመጠኑም ቢሆን በፍላጎት ረገድ ተቀዛቅዘው የተስተዋሉ ሲሆን በ41ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ከመሀል ያሳለፈለትን ድንቅ ኳስ ሰልሀዲን ሰዒድ ከፍሬው ጌታሁን ጋር 1ለ1 ተገኛኝቶ የተመለሰበትን ጌታነህ ከበደ ወደ ጎል ሲልክ ድሬ ተከላካዮች ካወጡበት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል የግብ እድል መፍጠር ሳይችል ቀርቷል። በዚህኛው ሙከራ ወቅት መጠነኛ ግጭት ገጥሞት የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ አዳኝ ሰልሀዲን ሰዒድ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በአቤል እንዳለ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

ድሬዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች ምንም እንኳን በግብ ሙከራ ባይታጀብም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ነበራቸው። በ13ኛው ደቂቃ ያሬድ ታደሰ ከቅጣት ምት እንዲሁም በ29ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታውን በተመሳሳይ ባህሩ ነጋሽ ካዳናቸው ሙከራዎች ውጭ የጠሩ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ተስተውሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከመጀመሪያው በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የተስዋለበት ነበር። 54ኛው ደቂቃ ላይም ጋዲሳ መብራቴ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ጌታነህ ከበደ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።


በጨዋታው የተቆጠሩ ጎሎችን በዩቲዩብ ቻነላችን ይመልከቱ

በደቂቃዎች ልዩነት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን የቅጣት ምት ጋዲሳ መብራቴ ከጠባብ አንግል በቀጥታ በመምታት እጅግ ማራኪ የሆነች ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን አሸናፊነት ያረጋገጠች የምትመስል ግብ በ58ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችሎ ነበር።

ሦስተኛ ግብ ካስተናገዱ በኃላ በነፃነት ውጤቱን ለማጥበብ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ድሬዳዎች በ60ኛው ደቂቃ ኤደረዊን ፍሬምፖንግ የሰራውን ስህተት ተጠቅመው በሪችሞንድ አዶንግ አማካኝነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያላቸውን ተስፋ ያለመለመች ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

በዚህ ያላበቁት ድሬዳዎች በተደጋጋሚ ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል በመድረስ አደጋ ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በስተመጨረሻም በ90+2ኛው ደቂቃ ሙህዲን ሙሳ ከርቀት ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ የጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ስጋት ውስጥ ቢከትም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በፈረሰኞቹ የ3-2 የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

በጨዋታው በ78ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ጎሎች ያስቆጠረው ጌታነህ ከበደ ባጋጠመው ጉዳት ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል።

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ ሲያደርግ ድሬዳዋ ከተማ ወደ 15ኛ ዝቅ ብሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ