የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 3-1 ባህር ዳር ከተማ

በስምንተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና በሜዳው ከተከታታይ ሽንፈት በኃላ ባህርዳር ከተማን 3ለ1 ከረታ በኃላ ሁለቱም አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተውናል፡፡


👉 “በፍፁም መነሳሳት ነበር የምንጫወተው” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለጨዋታው

ጥሩ ነው ወደ ማሸነፉ መንገድ መምጣታችን ጥሩ ነው፡፡ ያው ስንሸነፍም ያው ትናንሽ ስህተቶች ነበሩ፤ ግን ቡድናችን ጥሩ ነበር፡፡ በጥቃቅን ስህተቶች ነበር ጎሎች ሲገቡብን የነበሩት፤ ያንን ዛሬ አስተካክለናል። በተለይ ወደመከላከሉ አካባቢ በራስ መተማመን ችግር ነበር፡፡ በቀላሉም ጎሎች ይቆጠሩብን ነበር። ዛሬ እስከመጨረሻው ድረስ ቀርፈናል ማለት ይቻላል። ይሄን ማስቀጠል ነው፡፡

ቡድናችን ዛሬ ሁለት ጨዋታ የተሸፈ አይመስልም። ፍፁም በመነሳሳት ነበር የምንጫወተው፤ አቅም እንዳለው የሚያሳይም ቡድን ነው፡፡ አሁንም ረጅም ዕርምጃ እንራመዳለን ብዬ አሰባለሁ። ዛሬ የነበረው ነገር በጣም ጥሩ ነው፡፡

የመከላከል ስህተት

እውነት ነው ሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ሲገቡብን የነበረው በዚህ መንገድ ነው። አሁንም መጨረሻ ላይ የተቆጠረብንም ተመሳሳይ ነው። ግን ዛሬ እንሻላለን ማለት ይቻላል፡፡ ቢያንስ ዘጠና ደቂቃውን ተቆጣጥረው የተባሉትን ተጫዋቾች ማርክ አርገው በአግባቡ ተጫውተዋል፡፡ እዛ ጋር ክፍተት አልነበረም፤ ደስተኛ ያልሆኑት መጨረሻ ላይ በገባው ጎል ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም እዛ ጋር በንግግር የሚፈታ ነው። በስራ ሳይሆን በንግግር የመግባባት ችግር ነው። ስለዚህ ይሄን እየቀረፍን ቡድናችንን ይበልጥ ጠንካራ እያደረግን እንሄዳለን፡



👉 “ከመሀል ሜዳ የሚመጡ ጠንካራ ኳሶችን ማቆም ስላልቻልን ዋጋ ከፍለናል” ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)

ስለ ጨዋታው

በመጀመሪያ ተጋጣሚዬ ጨዋታውን ስላሸነፉ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት ፈልጋለሁ። ሁለት መልክ ነበረው፤ ምንም እንኳን በመጀመሪያ አስር እና አስራ አምስት ደቂቃ ተጭነውን ቢጫወቱም በመጀመሪያው አርባ አምስት የተመጣጠነ ጨዋታ ነበር። በሁለተኛው አርባ አምስት የተሻለ ነበር። ተጋጣሚያችን በተለይ ከመሐል ሜዳ የሚመጡ ጠንካራ ኳሶችን ማቆም ስላልቻልን ዋጋ ከፍለናል። ኳስ ነው ህይወት ይቀጥላል፤ ለሚቀጥለው ጨዋታ ራሳችንን እናዘጋጃለን። የመከላከል ድክመታችንም ዛሬም እንዳለ ነው። እሱን በቀጣይ መቅረፍ በግድ ይጠበቅብናል፡፡

ወሳኝ ተጫዋቾች ያለመኖር ጉዳት

ምንም ጥያቄ የለውም፤ ቋሚ ተሰላፊዎች ናቸው። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ውጤትን መቀየር የሚችሉ ተጫዋቾች ናቸው። እና እነሱ አልጎዱኝም ማለት አልችልም። ግን በነሱ አለመኖር ሽንፈቱን ማሳበብ አልፈልግም። በመጀመሪያው አርባአምስት ዕድሎች አግኝተን ነበር፡፡ በተለይ ጎል ከገባብን በኃላ ያንን አለመጠቀማችን በሁለተኛው አርባአምስት ከሜዳችን ወጥተን እንድናጠቃና በቂ የማጥቂያ ቦታ ለተጋጣሚያችን ለመስጠት ተገደናል፡፡

የአሰልጣኝ ቡድን አባላት በተወሰነ መልኩ በዳኛው ላይ ሲያሳይ ስለነበረው ቅሬታ

እኔ ብዙ ስለዳኛ ማውራት አልፈልግም። ግን የአሰልጣኝ ቡድን ባትል ደስ ይለኛል። በመጀመሪያው አርባአምስት የተደረገውን ሁላችሁም አይታችዋል። አሰልጣኙ ይሄን ተናገረ ለማለት ካልሆነ በስተቀር መጀመሪያ የገባብን ጎል ያገባነውንም ጎል እናንተ አይታችሁ መፍረድ ነው፡፡ ከዛ ውጪ የሚያናደኝ ነገር የዳኝነት ስህተት አይደለም። ደጋፊዎችን በማነሳሳት ጨዋታን ለማሸነፍ ታክቲክ ይዞ መምጣት ግን ለሀገራችን ዕግር ኳስ ይጠቅማል ብዬ አላስብም። የእውነት በዚህ ቅር ብሎኛል፡፡ ይሄ በሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች እየከረሩ ሲወጡ ለእግር ኳሱ አደጋ ነው እና በዚህ ከልብ አዝኛለሁ፡፡

የወጥነት ችግር ስለመስተዋሉ

“እውነት ነው ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አልቻልንም። ያንን የስነ ልቦና ችግር መቅረፍ ይጠበቅብናል። እንዳያችሁት ወደ ሜዳ የመጣነው ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ነው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደምንፈልገው ጨዋታው ሄዷል። ግን ቀድመን ጎል ማስተናገዳችን እኛ ለማግባት ሜዳችንን ለቀን በመውጣታችን በለቀቅነው ሜዳ ተጋጣሚያችን ተጠቅሟል፡፡ ከዚህ እንማራለን እናስተካክላለን። አሁንም በድጋሚ ተጋጣሚን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ