ወላይታ ድቻ ከአሰልጣኙ ጋር ሲለያይ በርካታ አመራሮችንም አሰናብቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ባስመዘገበው ውጤት በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጋር ሲለያይ አመራሮችንም ማሰናበቱ ታውቋል፡፡

ወላይታ ድቻ በሊጉ ጅማሮ በሜዳው ሲዳማ ቡናን ከረታ በኃላ ባሉት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ ተስኖት ግርጌ ላይ በስድስት ነጥቦች ለመቀመጥ ተገዷል፡፡ ክለቡ ከሜዳ ላይ ውጤት ባሻገር በአመራሮቹ ላይ የደጋፊዎች የተቃውሞ ድምፅ ሲስተጋባ የሰነበተ ሲሆን የክለቡ ቦርድም የስንብት ውሳኔዎች ማስተላለፉን ለማወቅ ችለናል፡፡

የክለቡ ቦርድ ከውጤት መጥፋት ጋር በተገናኘ የክለቡን አሰልጣኞች ሰብስቦ ባናገረበት ወቅት ቀጣይ የሁለት ጨዋታዎች እድል መስጠቱንና በሜዳው በስሑል ሽረ 2ለ0 ሽንፈት ከቀመሰበት ጨዋታ በኋላ ዋና አሰልጣኙ ገብረክርስቶስ ቢራራ “የተነጋገርነውን ተግባራዊ ባለማድረጌ ከአሁን በኃላ ከድቻ ጋር አልቀጥልም።” በማለት ለጋዜጠኞች አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ክለቡ ዛሬ ከሰአት የክለቡ ቦርድ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን የማሰናበት ሀሳብ የሌለው ቢሆንም አሰልጣኙ ስልካቸውን ዘግተው በመሄዳቸው ውሳኔ ለማስተላለፍ ተገዶ አሰልጣኙ በራሳቸው ፍላጎት ከክለቡ እንደተለያዩ ተደርጎ እንዲነሱ መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም የክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ታደሰ መታፈሪያን ጨምሮ ባለፉት አስር ዓመታት በሥራአስኪያጅነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አሰፋ ሆሲሶ ያስገቡት የመልቀቂያ ደብባቤ ተቀባይነት አግኝቶ ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል። ለአምስት ዓመታት የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት በመሆን ያገለገለው አንዱዓለም ሽብሩ ከኃላፊነቱ እንዲነሳ የክለቡ ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉንም ሶከር ኢትዮጵያ የደረሳት መረጃ ይጠቁማል፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ