ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ስምንት – ክፍል ስምንት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም የዛሬው መሠናዶ የስምንተኛው ምዕራፍ ስምንኛ ክፍልን ይዞላችሁ ቀርቧል።


በ1965-66 የውድድር ዘመን ጅማሮ ላይ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ጉዞ እምብዛም አመርቂ የሚባል አልነበረም፡፡ በታህሳስ መጨረሻ ግን መሃል ክፍሉ በአለን ቦል፣ ቦቢ ቻርልተን እና ኖቢ ስታይልስ፥ የፊት መስመሩ ደግሞ በሮጀር ሃንት፣ ኢስትሃም እና ጆ ቤከር የተዋቀረው የራምሴይ ቡድን በአቋም መለኪያ ጨዋታ ስፔይንን በአስገራሚ ብቃት2-0 መርታት ቻለ፡፡ የመረጠው የአጨዋወት ሥርዓት እጅግ አዋጭ መሆኑን የተመለከተው እንግሊዛዊው አሰልጣኝ የአሸናፊነት ሥልቱን ምስጢር አድርጎ ለመሸሸግ ወደደ፡፡ ” በአለም ለሚገኙ ተቀናቃኞቻችን ምን እየሰራን እንዳለን ይፋ ማድረግ ፍጹም ስህተት ይመስለኛል፡፡ የተወሰኑ ተጫዋቾቻችን ይበልጡን በሚያስፈልጉን ጊዜ እስከምንጠራቸው ድረስ እነርሱን ከጉዳት መጠበቅ የእኔ ኃላፊነት እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ይህ እንደ አንድ የእድገት እርከን ሊወሰድ ይችላል፤ በእግርኳሱ ዘርፍ ለምንሳተፍ ሙያተኞችም ትልቅ ትምህርት ይሆነናል፡፡ እኔ ዋነኛ ሥራዬ በአስፈላጊው ጊዜ ጠንካራ ቡድን መገንባት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በተለመደ የተጫዋቾች ጥምረት ተጋጣሚን ተጭኖ የሚያጠቃ ቡድን ማቅረብ ላይሆን ይችላል፤ ይህኛው መላ አንዴ ውጤታማ ስላደረገን ሁሌም እርሱን የሙጥኝ ልንል አይገባም፡፡” ይላል ራምሴይ፡፡

እንግሊዝ ከፖላንድ ጋር ባደረገችውና 1-1 አቻ በተለያየችበት እንዲሁም ምዕራብ ጀርመንን 1-0 በረታችባቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ራምሴይ በድጋሚ 4-2-4 ፎርሜሽንን ተጠቀመ፡፡ በፖላንዱ ግጥሚያ ጂኦፍ ኸርስት የመጀመሪያ ጨዋታውን አከናወነና ወዲያውኑ ከአጥቂው ሃንት ጋር ጥሩ መግባባት ፈጠረ፡፡ በቀጣይ ጨዋታ እንግሊዝ ስኮትላንድን 4-3 ያሸነፈችበት ውጤት ደጋፊዎች እና ብዙኃን መገናኛዎችን ጮቤ አስረገጠ፤ ነገርግን ራምሴይ ቀድሞ እንደገመተው 4-2-4 በመከላከሉ ረገድ ቡድኑን ተጋላጭ እንዳደረገው አረጋገጠ፡፡ በግንቦት 1966 በዌምብሌይ እንግሊዝ ዩጎዝላቪያን 2-0 ድል ባደረገችበት ጨዋታ ቁጥቡንና እርጋታ የተላበሰውን የዌስትሃም አማካይ ማርቲን ፒተርስን እንቅስቃሴ በተመስጦ ተከታተለ፤ በዚህም የዋና ቡድኑ የመጨረሻውን ያልተደፈነ ክፍተት ይኸው ተጫዋች ይሞላው ዘንድ ፈቀደ፡፡ ምንም እንኳ አሰልጣኙ ፒተርስን “ከጊዜው አስር ዓመት ቀድሞ የተገኘ” ሲል ማሞካሸቱ ተጫዋቹ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር ውዳሴ ቢሆንበትም የዌስትሃሙ አማካይ እንደ ቦልና ሃንት ዘመናዊና ሁለገብ ተጫዋች መሆኑ የሚያጠያይቅ አልነበረም፡፡ ፒተርስ ከፈጠራ ክህሎቱ በተጨማሪ በመከላከሉም ረገድ ጠንካራ ብቃት ያሳይ ነበር፡፡

እንግሊዛዊው አሰልጣኝ የዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ በፊት ሃገሪቱ በርካታ የወዳጅነት ጨዋታዎች እንድታደርግ ጥሯል፡፡ በዚህም መሠረት እንግሊዝ ወደ ፊንላንድ አቅንታ ባደረገችው ጨዋታ መሃለኛው የሜዳ ክፍልን በፒተርስ፣ ቦልና ቻርልተን አዋቅሮ ካላሃንን በብቸኛ የመስመር አማካይነት አሰለፈው፡፡ እንግሊዝ በጨዋታው 3-0 ድል አደረገች፤ ከሶስት ቀናት በኋላም በኦስሎ ኖርዌይን 6-1 ደቆሰች፡፡ በዚህኛው ጨዋታ ግን ቡድኑ ሁለት የመሥመር አማካዮችን ወደ ሜዳ ይዞ ገባ፤ ኮኖሊ በቀጥተኛ የመስመር አማካይነት (Orthodox Winger) ፔይን ደግሞ ከመደበኛ ቦታው በመጠኑ ወደኋላ አፈግፍጎ (Withdrawn Winger) በሊድቤተር ሚና ተጫወቱ፡፡ ይሁን እንጂ ፒተርስ እስካሁንም የመጀመሪያ አስራ አንድ ውስጥ መካተት አልቻለም፤ በብዙኃን መገናኛዎች አይንም መግባት ተሳነው፡፡ ያም ሆኖ እንግሊዝ በካቶዊስ ከፖላንድ ጋር ላለባት የመጨረሻ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ጥሪ ተደረገለት፡፡ ይህ እንግዲህ ራምሴይ በዓለም ዋንጫው ሊተገብረው ያቀደው ፎርሜሽን አካል ነበር፡፡ ለጋዜጣዊ መግለጫ በተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ፊት የቋሚ ቡድኑን አባላት ስም ዝርዝር እየጠራ በማስተዋቅ ላይ እያለ የመለያ ቁጥር-11 ጋር ሲደርስ ቆም ብሎ የብዙሃኑን ቀልብ ሳበና ባልተለመደ ድራማዊ መልኩ ቦታውን ለፒተርስ እንደሰጠ አሳወቀ፡፡ ይህም ዝርዝር ብሄራዊ ቡድኑ ያለ መስመር አማካዮች (Wingers) መገንባቱን ገሃድ አወጣ፡፡ ቀጥተኛም ሆነ በሌላ ድርብ ሚና የሚሰለፍ የመስመር አማካይ አለመካተቱ ብዙዎችን አስገረመ፡፡ አሰልጣኙ ሊተገብር የወጠነው ፎርሜሽን 4-3-3 መሆኑ እየተጠቀሰ ቢዘልቅም ኖቢ ስታይልስ በግለ ታሪክ መጽሃፉ ላይ እንዳሰፈረው ፎርሜሽኑ በትክክል 4-1-3-2 መሆኑን ገልጿል፡፡ ስታይልስ እንደሚያብራራው እርሱ በብቸኛ ተከላካይ አማካይነት (Anchor) የመሃል ክፍሉን እየዘወረ ከፊቱ ፒተርስ፣ ቻርልተንና ቦል የማጥቃት ነጻነት ተሰጥቷቸው ለአጥቂዎቹ ሃንትና ከእርሱ ጎን ይሰለፋል ተብሎ ቅድመ ግምት ላገኘው ጂሚ ግሪቭስ እገዛ እንዲያደርጉ ኃላፊነት ተጣለባቸው፡፡ እንግሊዝ በሃንት ግብ ፖላንድን 1-0 አሸነፈች፡፡ ራምሴይ ከሶስት ዓመታት ቀደም ብሎ እንግሊዝ የዓለም ዋንጫን በእርግጠኝነት እንደምታነሳ ሲወተውት የነበረውን ማመን የጀመረው በዚህ ጊዜ እንደነበር ሬይ ዊልሰን ይገልጻል፡፡

የዓለም ዋንጫው ውድድር ተጀምሮ በመክፈቻው ጨዋታ እንግሊዝ ከኡሯጓይ ስትፋለም ራምሴይ ከፒተርስ ይልቅ ኮኖሊን ማሰለፍ መረጠ፤ የመሃል ክፍሉ ቅርጽ ከተለመደው ጋደድ ያለ (Lopsided) 4-3-3 ፎርሜሽንም ተጠቀመ፡፡ ምናልባት ራምሴይ ያኔ የአጨዋወት እቅዱን እየሸሸገ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው ነገርግን የተጠቀጠቀ የተከላካይ ክፍል ላለው ቡድን የመስመር አማካይ መያዝ አስፈላጊ ሳይሆን እንደማይቀር እያብሰለሰለም ይሆናል፡፡ ሁለቱም መላምቶች ግን አልሰሩም፤ አማካይ ክፍሉ በማጥቃቱ ሒደት ሶስቱን የፊት መስመር ተሰላፊዎች ማገዝ ተስኖት ሲቸገር ተስተዋለ፤ በመጨረሻም ጨዋታው 0-0 ተጠናቀቀ፡፡

ከሜክሲኮ ጋር በተከናወነው ሁለተኛ ጨዋታ ፒተርስ በመጀመሪያው ጨዋታ ጉዳት በደረሰበት ቦል ምትክ ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ወደ ሜዳ ገባ፡፡ ፔይንም እንዲሁ ኮኖሊን አስቀምጦ የመሰለፍ ዕድል አገኘ፡፡ ይህኛው አሰላለፍ በቀደመው ጨዋታ እንግሊዝ መሃል ክፍሏ ላይ የታየውን ወደ አንድ ጎን ዘምበል ያለ ቅርጽ ገለበጠው፡፡ ስለዚህም የመስመር አማካዩ ከግራው ይልቅ በቀኙ በኩል ተሰለፈ፡፡ የአጨዋወት ሥርዓቱ መሰረታውያን ግን እንዳሉ ነበሩ፡፡ ራምሴይም የመስመር አማካይ ተጠቅሞ ተጋጣሚን ለማሸነፍ አሰበ፡፡ ውጥኑ ተሳካለተት፤ ማራኪ ባልሆነ መንገድም ቢሆን እንግሊዝ 2-0 ድል አደረገች፡፡ ከፈረንሳይ ጋር ለሚከናወነው የምድቡ ሶስተኛ ጨዋታ ካላሃን ተመረጠ፤  ይህኛው ፍልሚያ ይበልጡን የሚታወሰው ኖቢ ስታይልስ ጃኪ ሲሞን ላይ በፈጸመው አሰቃቂ ታክል ቢሆንም እንግሊዝ ተመሳሳይ ድል ቀናት፤ ይህንንም ጨዋታ 2-0 ረታች፡፡ የአለም አቀፉ እግርኳስ ማህበር ወደፊት ስታይልስ ላይ ቅጣት እንደሚጥል ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበርም ስታይልስ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች የግድ መሰለፍ ይኖርበት እንደሆነ የሚጠይቅ መልዕክት ለራምሴይ ላከ፡፡ አሰልጣኙ በአንድ በኩል የመርህ ተገዥ በመሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ አማካዩ ለቡድኑ እጅጉን ወሳኝ ተጫዋች ስለሆነ ይመስላል ራሱን ከሥራው ሊያገል እንደሚችል ዛተ፡፡

በመጨረሻም ከአርጀንቲና ጋር በተደረገው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ፎርሜሽኑን ወደ 4-1-3-2 ቀየረ፡፡ ምናልባት ታክቲካዊ ለውጡ ለራምሴይ በቂ ይሆን ነበር፡፡ ነገርግን የጂሚ ግሪቭስ መጎዳት ሳይጠቅመው አልቀረም፡፡ በእርሱ ምትክ የጋዜጦቹን ተወዳጅ ተጫዋች ባያሰልፍ የሚደርስበት ተቃውሞ ሳያሰጋው ኸርስትን የማጫወት አጋጣሚ ተፈጠረለት፡፡ ኸርስት የግሪቭስን ያህል አስደናቂ አጥቂ ባይሆንም የአየር ላይ ኳሶችን በማሸነፍ እንዲሁም እነዚሁኑ ኳሶች ተቆጣጥሮ በመያዝ ረገድ ትልቅ ብቃት ነበረው፡፡ ከአርጀንቲና ጋር የተካሄደው ጨዋታ የጋለና ሁከት የበዛበት ነበር፡፡ ” በሃገራት መካከል የተፈጠረ ግጭት እንጂ እግርኳሱ ጨርሶ የጨዋታ ይዘት አልነበረውም፡፡” ሲል ሂዩጅ ማክቫኒ ፍልሚያውን ገልጾታል፡፡ እንግሊዞች በቆራጥነት ታገሉ፤ የአርጀንቲናው አምበል አንቶኒዮ ራቲን በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ ጂኦፍ ኸርስት በግንባር ያስቆጠራት ግብ ጨዋታውን 1-0 እንዲጨርሱ ረዳቻቸው፡፡ ምንም አይነት የማዝናናት ገጽታ ባይላበስም ራምሴይ ያሳሰበው ጉዳይ ከሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ በማራካኛ ስታዲየም ከተከሰተው የእንግሊዝ ሽንፈት ትምህርት መወሰዱ ነበር፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ ስታይልስ የኤርሚንዶ ኦኔጋ እንቅስቃሴን በቅርብ ክትትል እንዲቆጣጠረው (Man Marking) ታዘዘ፤ አማካዩም በከፍተኛ ትጋት የተባለውን ተገበረ፡፡ በቀኙ መስመር ለአጥቂዎቹ ቀርቦ ሲጫወት የነበረው ቦል አስገራሚ ብቃት አሳየ፤ እንግሊዛዊው የመስመር አማካይ አርጀንቲናዎችን በማጥቃት እንቅስቃሴው ከማሸበሩ በላይ በመከላከሉም ተሳትፎ የላቀ ሆኖ ተገኘ፥ በተለይ የተጋጣሚውን የመስመር ተከላካይ (FullBack) ሲልቪዮ ማርዞኒ ወደፊት እንዳይሮጥ አድርጎት አላንቀሳቅስ አለው፡፡

እንግሊዝ ፓርቱጋልን በገጠመችበት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታም የኖቢ ስታይልስ ሚና ወሳኝ ነበር፡፡ በአለም ዋንጫው አስተናጋጅ ሃገር አሸናፊነት 2-1 በተጠናቀቀው ይህም ጨዋታ ዩዞቢዮ የረባ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳይችል ስታይልስ የፖርቱጋሉ ድንቅ አጥቂ መፈናፈኛ እንዳያገኝ አደረገው፡፡ ያን ዕለት ሁለቱንም ግቦች ቦቢ ቻርልተን አስቆጠረ፡፡ ሶስቱ አማካዮች የተጋጣሚን ቡድን የመከላከል አደረጃጀት ሰብረው የሚገቡበት ሥልት ውጤማነት በፍጻሜው ጨዋታም ታየ፡፡ የእንግሊዝን የመጀመሪያውን ጎል ፒተርስ አገባ፤ አይደክሜው የቀኝ መስመር አማካይ ቦል ደግሞ ሁለተኛዋን አከለ፡፡ በተጨማሪ ደቂቃ ቦል ከቀኝ መስመር ወደ ጀርመኖች ግብ ክልል የላከውን ተሻጋሪ ኳስ (Cross) ኸርስት በግምባሩ ገጭቶ ሶስተኛ ጎል ሲያስቆጥር አወዛጋቢ ንትርክ ተፈጠረ፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ሲቀሩ ወሳኟንና አራተኛዋን ግብ ከቦቢ ሙር የተሻገረችውን ረዥም ኳስ ኸርስት የጀርመኖቹ መረብ ውስጥ መሰጋት፡፡ ሊድቤተር ይህችን ግብ ሲያስታውስ ራምሴይ በኢፕስዊች ሳለ ከሚደሰትባቸው የጎል አይነቶች እንደምትመሳሰል ጠቅሷል፡፡ ጎሏ ከቀላል ኳስ የተገኘች፣ ትርምስ ያላጀባትና በማያሻማ የአጨራረስ ሒደት ውስጥ ያለፈች ድንቅ ነበረች፡፡
ይህ የገቢራዊነት (Pragmatism) ጉዳይ ምናልባት ለዚያ ወቅት ለእንግሊዞች ተስማሚ ሥልት ሊሆን ይችላል፤ ነገርግን አሳሳች አቅጣጫን አስይዟቸውም አልፏል፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ በሜክሲኮ በሚደረገው የዓለም ዋንጫ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን በላቀ ብቃት መተግበር እንደሚችሉ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋልና፡፡

ጊዜያት እየገፉ ሲሄዱ ከንድፈ ሃሳብ ይልቅ በአመዛኙ በተግባር ውጤት ላይ ማተኮር የግድ ስለመሆኑ የሚወተውተው የራምሴይ እግርኳሳዊ አስተምህሮ አሰልቺ እየሆነ መጣ፡፡ በ1972 እንግሊዝ በሜዳዋ በምዕራብ ጀርመን 3-1 ከተሸነፈች በኋላ ማክቫኒ በመብከንከን ስሜት ውስጥ ሆኖ “ድል ቢያጎናጽፍ እንኳ ጥንቃቄ የበዛበትና ቀልብን የማይስብ የአጨዋወት ሥልት ዘላቂ ሆኖ መቀጠል አይችልም፡፡ ይህኛው መንገድ ሽንፈት ማምጣት ሲጀምር ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ይሆናል፡፡” በማለት የሰጠው አስተያየት ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡ ያን ቶማዜውስኪ ዌምብሌይ ላይ ለሃገሩ ፖላንድ የሰራው ገድል እንግሊዝ ለ1974 የዓለም ዋንጫ እንዳታልፍ አደረጋት፤ ያኔ ራምሴይ ከሥራው ተባረረ፡፡
ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያለው እጥር ምጥን ያለ ግንኙነት እንዳለ ሆኖ ራምሴይ ላይ የታየው ጥላቻ ሥር የሰደደው በእግርኳስ ውበትና ውጤት መካከል የነበረውን ውጥረት መልሶ ማክረር ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ አሰልጣኙ በየትኛው ጽንፍ እንደሚገኝ ማወቅ ከባድ አልነበረም፡፡ ለአርጀንቲና የጨዋታ አቀራረብ ንቀት ያሳይ ነበር፡፡ ያ ማለት ግን ያሰለጠናቸው ቡድኖች በሙሉ በ”ጸረ-እግርኳስ”/ Anti-Futbol/ አቋም የሚፈረጁ ነበሩ ለማለት አያስደፍርም፡፡ አልፍ ራምሴይ አሰልጣኞች በእግርኳስ ሊኖራቸው ስለሚገባው ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለው እምነት ከታላቁ አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ ኦዝቫልዶ ዙቤልዲያ አስተሳሰብ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ራምሴይ ዘወትር የሚለው ይህንኑ ነበር፡፡ ” እኔ የተቀጠርኩት የእግርኳስ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ነው፡፡ አለቀ፡፡”

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡