ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በ9ኛ ሳምት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚደረጉ መርሐ ግብሮች መካከል የድሬዳዋ ከተማ እና የአዳማ ከተማን ጨዋታ የዳሰሳችን መዝጊያ አድርገነዋል።

ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ከደረሰባቸው ሁለት (ወልዋሎ እና ጊዮርጊስ) ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም እና ከደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ለመውጣት ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የድሬዳዋ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ ተሸነፈ

በሊጉ ከሚሳተፉ 16 ክለቦች መካከል ከፍተኛ ግቦችን ያስተናገደው (17) ድሬዳዋ በነገውም ጨዋታ የተከላካይ መስመሩ መፍትሄዎችን ካላዘጋጀ ሊቸገር ይችላል። በዚህ ረገድ አሁንም መፍትሔ ለማበጀት የተቸገሩት የቡድኑ አሰልጣኝ ስምዖን ይበልጥ ለመከላከል አደረጃጀት የተመቸውን እና ለደህንነት ቅድሚያ በሚሰጠው የ5-4-1 አደራደር በተጫወቱበት የ8ኛ ሳምንት ጨዋታ (ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር) 3 ግቦችን ማስተናገዳቸው የቡድኑ ሁነኛ ችግር እንዳልተፈታ የሚጠቁም ነው። በነገውም ጨዋታ ይህ የመከላከል አደረጃጀት ካልተስተካከለ ለተጋጣሚ ምቹ አጋጣሚን ሊፈጥር ይችላል።

ለወትሮው ግብ ለማስቆጠር የሚቸገረው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት 2 ግቦችን የሊጉ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ክለብ ላይ ማስቆጠሩ መልካም ነው። ምንም እንኳን ጎሎቹ በተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች ስህተቶች የተገኙ ቢሆንም የቡድኑን የግብ ማስቆጠር ድክመት ለመቅረፍ እንደ መነሻ የሚሆኑ ግብአቶች የተገኙበት ነበር። ከምንም በላይ በግራ መስመር አጋድሎ ለማጥቃት የሚጥረው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ተጋጣሚን በዚህ መስመር በማስጨነቅ እንደሚጫወት ይገመታል።

በቡድኑ በኩል ሳምሶን አሰፋ እና ያሬድ ሀሰን ከጉዳት ሲመለሱ በረከት ሳሙኤል እና ሳሙኤል ዘሪሁን ለጨዋታው እንደማይደርሱ ተጠቁሟል። ከዚህ ውጪ ከጉዳቱ ያገገመው ረመዳን ናስር የመሰለፍ ነገር አጠራጥሯል፡፡

የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ ተሸነፈ አቻ አቻ አቻ

ከደሞዝ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ቅሬታ ለቀናት መደበኛ ልምምድ አቁመው የነበሩት የአዳማ ከተማ ተጨዋቾች በሊጉ የ2ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ያገኙትን ድል (ወልቂጤ ከተማን 1-0) በአምሯቸው በማሰላሰል ነገ ጠዋት ወደ ምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል ያመራሉ።

በሊጉ ብዙ የአቻ ውጤቶችን (6) ያስመዘገበው አዳማ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮቹ የቁልቁለት ጉዞውን ተያይዞታል። በተለይ በሜዳ ላይ ገና ያልተቀናጀ የሚመስል እንቅስቃሴ (በይበልጥ ከወገብ በላይ) እያስመለከተ ያለው ቡድኑ ከፍተኛ የግብ ማስቆጠር ችግር ይስተዋልበታል። እርግጥ ቡድኑ ከተለያዩ አማራጮች ግቦችን ለማስቆጠር ቢሞክርም ኳስን ከመረብ ጋር የማዋሃድ ችግር ተጠናውቶታል። በነገውም ጨዋታ ይህ የግብ አይናፋርነቱ ካለቀቀው እንደከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች ቁጭትን ብቻ ከሜዳ ይዞ ሊወጣ ይችላል።

በአንፃራዊነት ጠንካራ የሚባል የተከላካይ ክፍል የገነባው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ካለ በቂ ልምምድ ወደ ሜዳ ስለሚገባ መከላከልን የመጀመርያ ምርጫው ከማድረግ ባሻገር የጨዋታውን ፍጥነት በማቀዝቀዝ ውጤት ይዞ ለመውጣት እንደሚጥር ይገመታል። ፈርጣማ እና ረጃጅሞቹ የቡድኑ ተከላካዮች ቡድኑ ግብ እንዳያስተናግድ ብቻ ሳይሆን ግብም እንዲያስቆጥር በራሳቸው መንገድ መፍትሄ ለመስጠት ይጥራሉ። ከዚህ ውጪ በእንቅስቃሴ ደረጃ የተሻሉ ስራዎችን በሜዳ ላይ ለመስራት የሚሞክሩት ከነዓን እና በረከት በነገው ጨዋታ ለቡድኑ ጥሩ ነገሮችን ሊያመጡ ይችላሉ።

ከቡድኑ ጋር በተያያዘ የአዳማ ልዑካን አመሻሽ አዲስ አበባ መግባታቸው ሲገለፅ ነገ ማለዳ 1:30 ወደ ድሬዳዋ እንደሚጓዙ (በአውሮፕላን) ተነግሯል።

ሚካኤል ጆርጅ፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ አማኑኤል ጎበና እና አዲስ ህንፃ በጉዳት በነገው ጨዋታ ላይ እንደማይኖሩ ተገልጿል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 16 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ ስምንት ጨዋታዎችን በድል ሲያጠናቅቅ ድሬዳዋ አምስቱን አሸንፏል። 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 17 ፣ ድሬዳዋ 12 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

ፍሬዘር ካሣ – ዘሪሁን አንሼቦ – አማረ በቀለ – ያሲን ጀማል

ፍሬድ ሙሸንዲ – ዋለልኝ ገብሬ

ያሬድ ታደሰ – ኤልያስ ማሞ – ሙህዲን ሙሳ

ሪችሞንድ ኦዶንጎ

አዳማ ከተማ (3-4-3)

ጀኮ ፔንዜ

መናፍ ዐወል – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ

ሱሌይማን ሰሚድ – እስማኤል ሳንጋሪ – ከነዓን ማርክነህ – ሱሌይማን መሐመድ

በረከት ደስታ – ቡልቻ ሹራ – ዳዋ ሆቴሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ