ሪፖርት | የሆሳዕና እና የጊዮርጊስ ጨዋታ በአሰልቺ አንቅስቃሴ ታጅቦ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ

በዘጠነኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታድየም ሀዲያ ሆሳዕናን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ነብሮቹ ወደ መቐለ አቅንተው ወልዋሎን በመርታት ከተመለሰው ስብስባቸው ሀዲያዎች በጉዳት ሱራፌል ዳንኤልን በማሳረፍ ሄኖክ አርፊጮን ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ ፈረሰኞቹ በአንፃሩ ከድሬደዋ ድል መልስ ግብጠባቂው ባህሩ ነጋሽ፣ ሙሉዓለም መስፍን፣ አቤል ያለው እና ሳላዲን ሰዒድን ከስብስቡ ውጪ በማድረግ ግብጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ ያብስራ ተስፋዬ እና አቡበከር ሳኒን በመተካት በዛሬው ጨዋታ ላይ ተጠቅመዋል።

ሜዳ ላይ ከነበረው እንቅስቃሴ ይልቅ በአቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታድየም የነበረው በርካታ ቁጥር ያለው የተመልካች ድባብ ትኩረት ሳቢ የነበረ ሲሆን የሚባክኑ ኳሱች የበዙበት፣ በጉልህ የሚጠቀስ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ ያላየንበት እና አሰልቺ የጨዋታ እንቅስቃሴ የመርሐ ግብሩ ገፅታ ነበር።

ጋዲሳ መብራቴ ከቀኝ ወደ ግራ ያሻገረውን የቅጣት ምት ኳስ ደስታ ደሞ ከግብጠባቂው አቤር ኦቮኖ ቀድሞ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ከግቡ አናት ከፍ ብላ የወጣችው ኳስ የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። እግራቸው ላይ ከአንድ አልያም ከሁለት በላይ ያልሆነ ቅብብል ከማድረግ ይልቅ ረዣዥም ኳሶች አብዝተው ይጠቀሙ የነበሩት ፈረሰኞቹ ይህ አጨዋወታቸው የተመቸው ለባለ ሜዳዎቹ ለሆሳዕና ቢሆንም ሀዲያ ሆሳዕና በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ሆነውም መታየት አልቻሉም። የሜዳውን ባህሪ የሚያቁ በመሆናቸው እና ወደ ጎል በመቅረብ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተሻሉ እንጂ አጨዋወታቸው ረዥም ኳሶችን መሠረት ያደረገ ነበር።

ይሁን እንደሻው ከግራ መስመር ወደ ሳጥን አጥብቦ ለመግባት በሚያደርገው ሂደት ውስጥ ለአጥቂው ቢስማርክ ኦፖንግ ለማቀበል ያሰበውን ኳስ አልፎ ሳጥን ውስጥ ከጀርባ ለቆመው ቢስማርክ አፒያ ጋር ደርሳ ተረጋግቶ ኳሱን በመቆጣጠር የፈረሰኞቹን ግብጠባቂ ፓትሪክ ማታሲን በማለፍ 22ኛው ደቂቃ ሀዲያ ሆሳዕናን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።

ኳሷ ተረጋግቷ መሬት ላይ አንሸራሽሮ ለሚፈልጉት ተጫዋች ለመስጠት ተቸግረው ረዣዥም ኳስ ሲጠቀሙ የቆዩት ፈረሰኞች ከ35ኛው ደቂቃ በኃላ ነበር ኳስ መሬት ላይ በመያዝ አደራጅተው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የተመለከት ነው። ያም ቢሆን በጎል ሙከራ ያልታጀበ በመሆኑ ምንም ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።

ብዙም ዛቢ ባል ነበር ወደ ጎል ለመቅረብ ከሚደረግ ትርጉም አልባ ጥረት ውጭ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ መመልከት ባልቻልንበት በዚህ ጨዋታ ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ከማዕዘን ምት ፍራኦል መንግስቱ ያሻገረውን አብዱልሰመድ ዓሊ አግኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረችው ኳስ ለሀዲያ ሁለተኛ ጎል መሆን የምትችል አጋጣሚ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዲያዎች ተዳክመው ሲቀርቡ በተሻለ ተጭነው የተጫወቱት ጊዮርጊሶች ከአማካይ ከሚሰጡ ኳሶች አጥቂዎች ጎል ለማስቆጠር በተቸገሩበት አጋጣሚ ደስታ ደሙ በግሩም ሁኔታ ከርቀት የሞከረው እና ለጥቂት የወጣበት መልካም አጋጣሚ ነበር። በተለይ 54ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ በቀጥታ ወደ ጎል መቶት የሀዲያው ግብጠባቂ አቤር ኦቮኖ የተፋውን ሀይደር ሸረፋ ነፃ ዕድል አግኝቶ ወደ ጎል ቢመታውም የግቡ አግዳሚ የመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊሶችን አቻ ማድረግ የሚችል የሚያስቆጭ ዕድል ነበር።

ተነቃቅተው በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ፈረሰኞቹ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ደቂቃ በዝምታ ተውጠው የነበሩት ጥቂት የማይባሉ ደጋፊዎችም ጭምር ነበር በመነቃቃት ቡድናቸውን መደገፍ የጀመሩት። ከእረፍት መልስ ተዳክመው የገቡት ነብሮቹ በአንፃሩ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚደርስባቸውን ጫና ለመቆጣጠር ጥረት ለማድረግ ከማተኮር ውጭ የራሳቸውን የጨዋታ መንገድ በመጠቀም የጎል እድል ለመፍጠር አልቻሉም።

ወደ ሆሳዕና ከመጡ በኃላ ጉዳት ያስተናገደውን የሙሉዓለም መስፍን ቦታን ዛሬ ባልተለመደ ሁኔታ ተረክቦ እስከ ጨዋታው 78ኛው ደቂቃ ድረስ የተከላካይ አማካይ በመሆን ሲያገለግል የቆየውን አስቻለው ታመነን ወደተለመደው ቦታው በመመለስ ምተስኖት አዳነን ወደ ፊት እንዲጫወት ያደረጉት የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ ያደረጉት ለውጥ ተሳክቶላቸዋል። በዚህም በ84ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ወደ ጎል ሲያሻግረው ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ጎል ፈረሰኞቹን አቻ ማድረግ ችሏል።

ጊዮርጊሶች ተጨማሪ ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን አሸንፈው ሊወጡበት የሚችሉበትን ዕድል በጨዋታው መጨረሻ ደቂቃ ላይ ቢያገኙም ዛቦ ቴጉይ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም የተጠበቀውን ያህል በሜዳ ላይ የረባ ነገር ሳንመለከትበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

የሳምንቱ ብቸኛ የአቻ ውጤትን ተከትሎ ሆሳዕና ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የነረውን እድል ሳይጠቀምበት ሲቀር ጊዮርጊስም ወደ አናት የሚጠጋበትን እድል አምክኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ