የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ውሎ

በከፍተኛ ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ከሁለት ጨዋታዎች በስተቀር ትላንት ተካሂደዋል። የተመዘገቡ ውጤቶች እና ሌሎች ክስተቶችንም እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

ምድብ ሀ

መሪው ለገጣፎ ለገዳዲ በሜዳው ወሎ ኮምቦልቻን አስተናግዶ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።

ለገጣፎ ለገዳዲዎች ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም አጀማመራቸው አመርቂ ያልነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመግባት በፋሲል አስማማውና ዘካርያስ ቱጂ አማካኝነት ወደ ግብ ተቃርበው ነበር።

አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመከላከሉ ላይ ተጠምደው የታዩት ወሎ ኮምቦልቻዎች በ3ኛው ደቂቃ በብርሃኑ ኦርዴላ አማካኝነት ካደረጎት ብቸኛ ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል አጋጣሚዎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ቀስ በቀስ ጨዋታው እየገፋ በሄደ ቁጥር በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተለይም በእንግዳው ቡድን ወሎ ኮምቦሎቻዎች በኩል የሀይል አጨዋወት አይሎ ተስተውሏል።

በ35ኛው ደቂቃ አብዲሳ ጀማል የሞከረውን ኳስ የወሎ ኮምቦልቻው ግብጠባቂና አግዳሚው ተረዳድተው የመለሱበትን ኳስ በቅርብ ርቀት የነበረው ልደቱ ለማ ቢያስቆጥርም የእለቱ ዳኞች ግቧን ከጨዋታ ውጭ በማለት ሳያፀድቋት ቀርተዋል። የለገጣፎ ተጫዋቾችና ደጋፊዎችም ውሳኔው ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተስተውሏል።

በቀሩት የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ፋሲል አስማማው ሞክሮ በወሎ ኮምቦሎቻ ግብጠባቂ ከከሸፈበት ሙከራ ውጭ ተጨማሪ ሙከራ ሳንመለከት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ለገጣፎዎች ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት ከጅምሩ ተጭነው መጫወት ሲችሉ ወሎ ኮምቦሎቻዎች በአንፃሩ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ለመሄድ በማሰብ በጥንቃቄ ተከላክለዋል።

ለገጣፎዎች በፋሲል አስማማው ልደቱ ለማና አብዲሳ ጀማል አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም የወሎ ኮሞቦልቻው ግብጠባቂ አቡበከር ኑራ በሶስቱም አጋጣሚዎች በአስደናቂ ብቃት የሚቀመስ አልሆነም። በወሎ ኮምቦልቻዎች በኩል ሄኖክ ጥላሁንና ሀብታሙ ወርቁ አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።

በጨዋታው ላይ ሌላው የተመለከትነው አስገራሚው ነገር ሰሞነኛ ድንቅ ብቃቱ ላይ የሚገውን የለገጣፎውን አጥቂ ልደቱ ለማን ለማቆም እግር በእግር እንዲከተለው ትዕዛዝ ተሰጥተቶት የገባው የወሎ ኮምቦልቻው ስለሺ ዘሪሁን ልደቱን ውሃ ለመጠጣት እንዲሁም የአሰልጣኝ ምክር ሊቀበል በሚሄድበት አጋጣሚ ጭምሮ ይከተልበት የነበረው መንገድ እጅግ አዝናኝ ነበር።

ዓድዋ ላይ ሶሎዳ ዓድዋ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በኃይልሽ ፀጋይ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ጎሎች አማካኝነት 2-0 ማሸነፍ ችለዋል።

አክሱም ላይ አክሱም ከተማ ደደቢት 3-1 አሸንፏል። ዘንድሮ ቡድን የተቀላቀለው ዘካሪያስ ፍቅሬ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ልዑልሰገድ አስፋው ተጨማሪዋን ግብ አስቆጥሯል። ለደደቢት ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ደግሞ አፍቅሮት ሰለሞን ነው።

ደሴ ላይ ደሴ ከተማ ፌዴራል ፖሊስን 1-0 አሸንፏል። ረዘም ላለ ደቂቃ ያለ ግብ በተጓዘው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መገባደጃው ላይ ደሴዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት በድሩ ኑርሁሴን ወደ ግብነት በመለወጥ ሶስት ነጥብ እንዲያሳኩ ማድረግ ችሏል።

ቢሾፍቱ ላይ ገላን ከተማ ከ ወልዲያ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

በጥምቀት በዓል ምክንያት ሜዳው በመያዙ የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና አቃቂ ቃሊቲ ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

ምድብ ለ

በምድቡ ከሚደረጉት ጨዋታዎች ተጠባቂ የነበረው የካፋ ቡና እና ነቀምቴ ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተገባዷል። በ16ኛው ደቂቃ ተከተል ደፋር ብቸኛዋን የድል ግብ አስቆጥሯል።

ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ከኢኮስኮ ያደረጉትን ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በሳምሶን ደጀኔ ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችለዋል።

ጨንቻ ላይ ጋሞ ጨንቻ ከሀላባ ያደረጉትን ጨዋታ በተመሳሳይ ባለሜዳው ጨንቻ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። የሚቆራረጥ የኳስ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ተጠቃሽ የግብ ሙከራ ሳያደርጉበት የተጠናቀቀ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ጋሞ ጨንቻ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት ሲያደርግ በአንፃሩ ሀላባ ከተማዎች ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም ሲጥሩ ተመልክተናል። ባለ ሜዳዎቹ ጥሩ በተንቀሳቀሱበት ሁለተኛውአጋማሽ በ78ኛው ደቂቃ ዘላለም በየነ ሳጥን ውስጥ በስተቀኝ በኩል ያገኛትን ኳስ ወደ ግብ ሲመታ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አጥቂው ማቴዎስ ኤልያስ አግኝቶ በማስቆጠር ባለሜዳዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በሁዋላ ሀላባ ከተማዎች በተደጋጋሚ ግብ ለማስቆጠር እድል ቢፈጥሩም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በጋሞ ጨንቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሚዛን ላይ ቤንች ማጂ ቡና ጅማ አባ ቡናን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። በዞኑ በተጫዋችነት፣ በቤንች ማጂ ቡና ክለብ በቴክኒክ ኮሚቴ ሲያገለግል ለነበረውና ባሳለፍነው ረቡዕ ህይወቱ ላለፈው አቶ መንግስቱ ማሞ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው ጨዋታ ተመጣጣኝ የሚባል ፉክክር የታየበት ሲሆን ወደ ግብ በመቅረብ ቤንች ማጂ ቡና የተሻለ ነበር። በ2ኛ አጋማሽ ጅማ አባ ቡና ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት የሚመስል የአጨዋወት መንገድ የተከተለ ሲሆን ቤንች ማጂ ቡና ጫና ፈጥሮ በመጫወት መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ሙሴ እንዳለ ከኦኒ ኡጁሉ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቀይሮ ቤንች ማጂ ቡና በሜዳው የዓመቱን ድል አሳክቷል፡፡

ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ከአዲስ አበባ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ ሀምበሪቾ ከመከላከያ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በፀጥታ ጉዳዮች ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።

ምድብ ሐ

(በፋሪስ ንጉሴ)

ኦሜድላ ሜዳ ላይ 4:00 ላይ በተከናወነ ጨዋታ የጀመረው ይህ ምድብ በረፋዱ ጨዋታ ኮልፌን ከ ነገሌ አርሲ አገናኝቶ 2-2 ተጠናቋል። ለነገሌ አርሲ አብዱላዚዝ አብደላ እና አላዛር ዝናቡ ሲያስቆጥሩ አዳነ አየለ እና ሀብታሙ ኃይሌ የባለሜዳው ጎሎች ባለቤት ናቸው።

በ7:00 ላይ የካ ክፍለ ከተማ ከ ቡታጅራ ከተማ ያደረጉትን ጨዋታ እንግዳው ቡድን 2-1 አሸንፎ የምድቡ መሪ መሆን ችሏል። ለቡታጅራ እያዩ ሲሳይ እና በላይ ገዛኸኝ የማሸነፊያ ጎሎቹን ሲያስቆጥሩ ለየካ ብቸኛዋን ግብ አሸናፊ ምትኩ አስቆጥሯል።

9:00 ላይ ቂርቆስን ከሜዳው ውጪ የገጠመው ሺንሺቾ ሚሊዮን ካሳ ከእረፍት መልስ በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ጎል 1-0 አሸንፏል።

ባቱ ላይ ባቱ ከተማ ከ ከጌዲኦ ዲላ ያደረጉት ጨዋታ በዲላ 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ዮሐንስ ኪሮስ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል።

አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ከ ስልጤ ወራቤ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ገና ከጅምሩ ድባቡ ያማረ የነበረው ጨዋታ ሙከራ ለማስተናገድ የፈጀበት የ3 ደቂቃ ዕድሜ ብቻ ነበር። በዚህ ደቂቃ ላይ ፍቃዱ መኮንን ጥሩ እድል አግኝቶ ባለመረጋጋቱ በቀላሉ ተበላሽቶበታል። 14ኛው ደቂቃ ላይ ከተካልኝ ደጀኔ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ኤደም ኮድዞ ወደ ጎል ሞክሮ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል። 15 ደቂቃ ላይ ደግሞ በድጋሚ ኤደሞ ኳሷን መቆጣጠር ባለመቻሉ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

28ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ የአርባምንጭ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ጢሞቲዮስ ቢረጋ በአግባቡ በመጠቀም መሪ መሆን የቻሉበት ጎል አስቆጥሯል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በ32ኛ ደቂቃ ላይ ፍቃዱ መኮንን ተከላካዮችን አታሎ ለማለፍ ሲሞክር በመጠለፉ የፍፁም ቅጣት ለአርባምንጮች ተሰጥቶ ኤደም ኮድዞ ወደ ጎል ቀይሮ አቻ ማድረግ ችሏል። ከግብ መቆጠር በኋላም ስልጤ ወራቤዎች በፍፁም ቅጣት ምቱ ላይ ቅሬታ አሰምተዋል።

ሁለተኛ አጋማሽ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት እንግዳዎቹ ደግሞ ሰዓት በማባከን ጨዋታውን በማቆራረጥ ያሳለፉበት ነበር። የአርባምንጭ ከተማን የፊት መስመር በቀላሉ ተቆጣጥረው በመጫወት ሙከራዎችን ላለማስተናገድ ጥረት ሲያደርጉም ተስተውሏል።
ባለሜዳዎቹም መረጋጋት ተስኗቸው የታዩ ሲሆን ውጤቱን አብዝቶ የመፈለግ ስሜትም ይታይባቸው ነበር። ከረፍት መልስ እንግዳዎቹ የአርባምንጭ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅመው በ65ኛ ደቂቃ ለይ ከድር ሸሪፍ ያገኘው እድል ሳይጠቀም የቀረበት በእንግዶቹ በኩል የሚያስቆጭ ሙከራ ሲሆን አዞዎቹ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግም ግብ ለማስቆጠር ቢሞክሩም ጠንካራ የነበረውን የስልጤ ወራቤ ተከላካይ ክፍልን አልፎ ግብ ለማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጽያ መድን ከ ደቡብ ፖሊስ ያለ ጎል የተለያዩበት ጨዋታም ሌላው የዚህ ሳምንት መርሐ ግብር ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ