“እንደ ሙሉጌታ ምህረት መሆን እፈልጋለሁ” የወላይታ ድቻው አማካይ እድሪስ ሰዒድ

ተወልዶ ያደገው በኮምቦልቻ ከተማ ነው፡፡ ወደ ክለብ እግር ኳስ ደግሞ የገባው በ2003 ጥቁር ዓባይ ቡድን ውስጥ አንደኛ ሊግ ላይ በመጫወት ነበር፡፡ በአብዛኛው የእግር ኳስ ህይወቱን በከፍተኛ ሊግ ቡድኖች ውስጥ ያሳለፈ ሲሆን 2007 ላይ በጥቂት ጨዋታዎች ለወልዲያ በመጫወት ከፕሪምየር ሊጉ ጋር ተዋውቋል፡፡ ለጥቁር ዓባይ፣ ስሑል ሽረ፣ መቐለ፣ አውስኮድ እና ለትውልድ ከተማው ወሎ ኮምቦልቻም አገልግሏል። በ2011 የውድድር ዘመን ወደ ቀድሞ ቡድኑ ወልዲያ ዳግም ተመልሶ በመጫወት ላይ ሳለ በክረምቱ ወላይታ ድቻን በአሰልጣኝነት የተረከቡት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በአንድ የወዳጅነት ጨዋታ ከተመለከቱት በኃላ ወደ ክለቡ እንዲመጣ አድርገዋል፡፡ በያዝነው የውድድር ዓመትን በክለቡ ለመጫወት ከፈረመ በኃላ ከዕለት ወደ ዕለት አስገራሚ አቋሙን በሜዳ ላይ እያሳየ ይገኛል፡፡

አማካዩ እድሪስ ሰዒድ ለአጥቂዎች ኳስ ከማቀበል በዘለለ እስካሁን ለቡድኑ ወሳኝ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን ካለው አቋሙ ባሻገር ስለ ዕድገቱ እንዲሁም አጠቃላይ ስለእግር ኳስ ህይወቱ ከድረ-ገፃችን ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡


በቅድሚያ ስለዕድገትህ እና ስለእግር ኳስ አጀማመርህ አጫውተን…

” የተወለድኩት በኮምቦልቻ ከተማ ነው፡፡ እግር ኳስንም እዛው በቀበሌ ውስጥ በመጫወት ነው የጀመርኩት። ከቀበሌ በቶሎ ወደ ዲቪዚዮን ገብቼም መጫወት ችያለው፡፡ አሁን ሱፐር ሊግ ሳይባል በፊት ብሔራዊ ሊግ በሚባል ወቅት ጥቁር አባይ በሚባል ቡድን ውስጥ ገብቼ በ2003 እና 2004 ተጫወትኩ ፤ ከዛ በኃላ ወደ ሽረ ሄጄ ለግማሽ ዓመት ብቻ ቆይቻለው፡፡ ከዚያም በኃላ ወደ ወልዲያ ሄጄ ክለቡ በ2006 ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲገባ የበኩሌን አስተዋፅኦ አድርጊያለሁ። ከወልዲያ ጋር በ2007 ፕሪምየር ሊጉ ላይ ለግማሽ ዓመት ያህል ብቻ ቆይቻለው፡፡ ቀጣዩን ግማሽ ዓመት ደግሞ ወደ ኮምቦልቻ ተመልሼ ለኮምቦልቻ በከፍተኛ ሊግ ተጫወትኩ። ኮምቦልቻን ለቅቄ ደግሞ መቐለ ፕሪምየር ሊግ በገባበት ዓመት ለመቐለ ተጫውቻለሁ። በቀጣይም ወደ ባህርዳር በማምራት ለአውስኮድ 2010ን እየተጫወትኩ አሳለፍኩ። አምና ደግሞ ወደ ወልድያ ድጋሚ ተመልሼ ስጫወት ከቆየው በኃላ ነው ወደ ወላይታ ድቻ ዘንድሮ የመጣሁት። ”

በአንዳንዶቹ ክለቦች ለግማሽ የውድድር ዓመት ብቻ የመጫወትህ ምክንያት ምን ነበር?

” እኔ በተረዳሁት ለምሳሌ መቐለ ስሄድ ግማሽ ላይ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሊገቡም ስለነበር እና ውጤታቸውም ጥሩ ስለሆነ ቡድኑ እንዲጠናከር ነበር እኔን ግማሽ ዓመት ላይ የጠሩኝ። ሽረም ስሄድ የሄድኩት በተመሳሳይ ቡድኑን ለማጠናከር ስለፈልጉ ነው፡፡ በሁለቱ ብቻ ግማሽ ዓመታትን አሳልፌዬለሁ። በወልዲያ ፣ ኮምቦልቻ እና አውስኮድ ግን አንድ አንድ ዓመት ነው የተጫወትኩት። ”

ዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ አቅማቸውን እያሳዩ ካሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆነሀል። ወላይታ ድቻን ስለተቀላቀልክበት አጋጣሚ እናውራ…

” ወላይታ ድቻ ልመጣ የቻልኩት በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አማካይነት ነው፡፡ በወዳጅነት ጨዋታ ይመስለኛል፡፡ ወልዲያ እየተጫወትኩ ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ስናደርግ አይቶኝ መሰለኝ የጠራኝ። በተጨማሪ ደግሞ ወልዲያ እየተጫወኩ ብርሀኔ አንለይ የሚባል የቡድኔ ተጫዋች ነበር። ከአሰልጣኙ ጋር ስለሚቀራረቡ ከገብሬ ጋር ስለእኔ አውርቶት ከዛም ደውሎልኝ ፍቃደኛ ሆኜ ቡድኑን ተቀላቅያለሁ”

በአብዛኛው በታችኛዎቹ የሊግ ዕርከኖች በመጫወት ነው ያሳለፍከው። በእርግጥ በወልዲያ በጥቂት ጨዋታዎች ላይ በፕሪሚየር ሊጉ ተጫውተሀል። ከዚህ አንፃር ፕሪምየር ሊጉን እንዴት አገኘኸው?

” ወላይታ ድቻ የተደራጀ ነው፡፡ ብዙዎቹ የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የነበሩ ልጆች ስለሆኑም አንድ ሁለት ልጅ ብቻ ሲጨመር ይከብደዋል ብዬ አላስብም፡፡ እኔም አልተቸገርኩም ፤ ቶሎ መላመድ ችያለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን ፕሪምየር ሊግ ለመጫወት ፍላጎት ያደረብኝ 2010 ላይ ነው፡፡ አውስኮድ እያለው ‘በ2012 ፕሪምየር ሊግ ላይ መጫወት አለብኝ’ ብዬ ለራሴ ነገርኩት። ‘ለምንድነው በ2012 በፕሪምየር ሊግ የማልጫወተው? በቃ መጫወት አለብኝ’ ብዬ አሰብኩኝ። ከዛም አምና ወልዲያ በነበርኩበት ሰዓት አሰልጣኙ ከሚሰጣቸው ልምምዶች በተጨማሪ በሳምንት ሦስቴ ድክመቶቼ ላይ ስሰራ ነበር። ያው ፈጣሪም ተጨመረበት ፤ ከእኔ ሚጠበቀው ማሰብ ነበር ፤ ማስበውን ነገር ደግሞ ለማድረግ መጣር። ያም ሆኖ የፈጣሪ ዕርዳታም ተደማምሮ ወደ ድቻ ልመጣ ችያለሁ። ፍላጎቴንም በተወሰነ መልኩ ማሳካት ችያለው። ፕሪምየር ሊጉ ከብዶኛል ብዬ አላስብም ፤ ከፍተኛ ሊግ እንደውም ትንሽ ይከብድ ነበር። ከፍተኛ ሊግ ስጫወት ‘እድሪስን ማርክ አድርጉት’ ተብሎ ነበር የምጫወተው ፤ እኔ ላይ የሆነ ሰው ተመድቦልኝ። እሱም ጨዋታውን አይጫወትም ፤ ከእኔ ጋር ብቻ የሚጫወት ተጫዋች አጋጥሞኛል። ያያ ነገር እዚህ ፕሪምየር ሊጉ ላይ አልገጠመኝም። በነፃነት መጫወትም ስለቻልኩኝ የተሻለ እየሰራው ልመጣ ችያለሁ። ከዚህ በኃላም የሚከብደኝ አይመስለኝም። ”

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሊጉ ጋር በደንብ የተዋሀድክ ትመስላለህ። ቡድኑ ከአንተ በሚነሱ ኳሶች በደንብ ሲጠቀምም እናያለን። በሌላ በኩል ደግሞ ግብም ታስቆጥራለህ። ስለዚህ ብቃትህ እናውራ…

“ብዙ ጊዜ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ላይ ብቻ ነበር ትኩረት የማደርገው። ቅድም እንዳልኩህ እዚህም ከመጣሁ በኃላ ከቡድኑ ጋር ከማደርገው ውጪ በግሌም እሰራለሁ፡፡ ስሰራ ከተረዳሁት መሀል ደግሞ ግብ ያለማስቆጠር ድክመቴ አንዱ ነበር። በድክመቴም ላይ ሰርቻለሁ። ‘ ለምንድን ነው ወደፊት በደንብ የማልጠጋው? ኳሶችን ለምንድን ነው ወደ ግብ የማልመታው? ‘ ብዬ አሰብኩ። እንደውም አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ” ደካማ ጎንህ? ” ብሎ ሲጠይቀኝ ‘ብዙ ጊዜ ሳጥኑ አካባቢ አልመታም ፤ ከመምታት ይልቅ መስጠትን ነው የማስበው’ ብዬ መልሼለት ነበር። ስለዚህ ወደ ጎል ቶሎ ቶሎ ስለምጠጋ ‘መምታት አለብኝ’ ብዬ አስቤ ስወስን ተሳካልኝ። ያን ተግባራዊ ሳደርግ ደግሞ ማግባት እየቻልኩ መጥቻለሁ፡፡ ”

ምንም እንኳን በዚህ ሳምንት በሀዋሳ ቢሸነፍም ቡድናችሁ ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ስንብት በኋላ ወደ መልካም ጉዞው መመለሱን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አሳይቶናል። ስለቡድንህ ምን ትላለህ?

” ቡድናችን ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ጎል የሚቆጠርብን በብዛት በስህተት ነው፡፡ እኛ የምንሳሳተው አንድ ኳስ ጎል ይሆንብናል፡፡ እኛ ደግሞ ጎሎች ላይ ብንደርስም በተደጋጋሚ አጨራረስ ችግሮች አሉብን። በተለይ ከመቐለ ጋር በነበረው ጨዋታ በሌሎቹም ላይ ተመሳሳይ ችግር ነበር፡፡ በደንብ የአጨራረስ ድክመት አለብን። እናም ስህተቶቻችንን መቀነስ ከቻልን ደግሞም የጎል ማግባት ችግራችንን መቅረፍ ከቻልን አሁንም ጥሩ ነገር የመስራት አቅሙ አለን እንሰራለንም ብዬ አስባለሁ። ”

“ዝምተኛ እና ስራውን ሰርቶ ብቻ የሚወጣ ነው” ሲባል እንሰማለን ላንተ እድሪስ ምን ዓይነት ተጫዋች ነው?

” በባህሪዬ እንዳልከው ዝምተኛ ነኝ ፤ ብዙ አላወራም። ከጓደኞቼ ጋርም ያን ያህል ቀልዶች ላይ አላተኩርም ፤ ባደርግም አላበዛም። የማውቀው ባህሪዬ የትም ቢሆን ዝምተኛ እንደሆንኩ ነው። ”

በእግር ኳሱ ‘እንደእሱ መሆን እፈልጋለሁ’ የምትለው አርአያ የሆነህ ተጫዋች ማነው?

” የአሁኑ የብሔራዊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ነው፡፡ እሱ ሀዋሳ እያለ እኔ ደግሞ ወልድያ እያለው በተቃራኒው አብሬው ተጫውቻለሁ። 2007 ላይ ስለሱ ብዙ ጊዜ ሲወራ እሰማ ነበር። በስብዕናው መልካም መሆኑንም እሰማ ነበር ፤ ብዙም የመቀራረብ ዕድሉ ባይኖረኝም። አማካይም ስለሆነ በመልካም ባህሪውም ብቻ በእግር ኳሱ እንደ ሙሉጌታ ምህረት መሆን እፈልጋለሁ ፤ በጣም ነው የምወደውም። በልጅነቴ ደግሞ ሮናልዲንሆ ደስ ይለኝ ነበር። እሱ የሚያደርገውን ለማድረግ እጥር ነበር። ኳስን ሳንቀረቅብ እንኳን እሱ ያደረጋትን ለማድረግ እታገል ነበር። ወደ ኳስም ስገባ ኳስ ጨዋታን ሳይሆን እሱ ሚያደርገው ለማድረግ ነበር የምሞክረው፡፡ ሌላ ደግሞ የሰፈሬ ልጆች ኳስ ተጫዋች እንድሆን ይገፋፉኝ ነበር። “አንተ ኳስ ተጫዋች ካልሆንክ ሌላ ማን ይሆናል ?” እያሉ ይመክሩኝ ነበር ፤ ቀበሌ አብረውኝ ይጫወቱ የነበሩ ልጆች። ያም ነገር ወደዚህ እንድገባ ያደረገኝ ይመስለኛል”

በቀጣይ በሊጉ ከዚህ በበለጠ ቦታ ለመገኘት ዕቅድህ ምንድ ነው?

” እንደ እግር ኳስ ተጫዋች ያሰብኳቸው ነገሮች አሉ በተለይ የሆነ ቡድንን ፕሪምየር ሊግ ባስገባ ብዬ አስብ ነበር። ያም ተሳክቶ ከአንድም ሁለት ፕሪምየር ሊግ በገቡ ቡድኖች ውስጥ ተጫውቻለሁ። ከዚያ በተጨማሪ ቅድም እንዳልኩት ፕሪምየር ሊግ መጫወት አለብኝ ብዬም አስብ ነበር፡፡ ከነዚህ ባለፈ ግን ማንም ተጫዋች ሊኮራበት የሚችለው ያው ለሀገሩ ሲጫወት ይመስለኛል እና እኔ ብሔራዊ ቡድን ብጫወት ደስ ይለኛል ፤ ከአሁን በኃላ ማስበውም እሱን ነው፡፡ በጣም በጣም ለሀገሬ ብጫወት ደስ ይለኛል፡፡ ”

በመጨረሻም እዚህ ለመድረሴ በእኔ ትልቅ አሻራ አሳድረዋል ብለህ የምታመሰግናቸው ካሉ?

” ፕሪምየር ሊግ ለመጫወቴ እና እዚህ ለመምጣቴ ቅድም እንዳልኩህ ብርሀኔ አንለይ እና አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እንዲሁም ገብሬ ኃላፊነት ወስዶ ስላመጣኝ ለኔ ትልቅ ቦታ አላቸው ፤ እነሱን ማመስገን እፈልጋለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ በተወለድኩበት አካባቢ የተሻለ ኳስ ተጫዋች እንድሆን የደግፉኝ ሰዎች ነበሩ፡፡ የኮምቦልቻ ምክትልም የነበረ አለ ፤ እነሱ እነሱን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡ ከብዙ አሰልጣኞች ጋር ሠርቻለሁ ኃላፊነት ወስዶ ያመጣኝ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ በኔ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው ብርሀኔንም እንደዛው። ደግሜ አመሠግናለሁ። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ