የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-0 ሲዳማ ቡና

በአስረኛው ሳምንት ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው ጨዋታዎች መካከል ፋሲል ከነማ በሜዳው ሲዳማ ቡናን 1-0 ከረታበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


👉 “በዛሬው ጨዋታ ጫና ነበረብን” ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

የዛሬውን ጨዋታ ጫና ውስጥ ሆነን ነው ያከናውነው። የዘጠነኛ ሳምንት ተጋጣሚያችን የነበረው ስሑል ሽረ (የዛሬ ዓመት 30ኛ ሳምንት ከዋንጫ ውጭ ያደረገንን ቡድን) ለማሸነፍ ነበር ያሰብነው፤ ነገር ግን አልተሳካም። ከዛ መልስ በሜዳችን የምናደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ አለብን ብለን ነው ወደ ሜዳ የገባነው። በሜዳችን ያደረግነውን አራቱን ጨዋታ አሸንፈናል፤ ይህን ሪከርድ ለማስቀጥልም ጭምር ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። በጨዋታው ላይ ወደፊት መስመር ጠጋ ብለን ለመጫወት ጥረት በማድረግ ውጤት ይዘን መውጣት ችለናል። በሚቀጥለው ጊዜ ከሜዳ ውጪ እያጣን ያለነውን ነጥቦች ማግኘት አለብን። አብዘኛውን ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ላይ ነው ግብ ያስተናግድነው። ይህን ለማሻሻል እንሰራለን።”

👉 “እንደ እንቅስቃሴያችን መሸነፍ አልነበረብንም” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ ጥሩ ኳስ የታየበት ነበር ብዬ አስባለው። ከዚ በተረፈ በእንቅስቃሴ ደረጃ ከዕረፍት በኃላ ለአስራ አምስት ደቂቃ ያክል ብልጫ ወስደውብን ነበር። ከዛ መልሰን ተቆጣጥረነዋል። እንደ እንቅስቃሴያችን መሸነፍ አልነበረብንም። ጥሩ ነበርን ፤ ብዙ ዕድሎች ፈጥረናል። በተለይም ከዕረፍት በፊት ከስድስት እስከ ሰባት ጎል የሚሆኑ ኳሶች አምክነናል። አንዳንዴ እንዲህ ያጋጥማል። በማይሆን ስህተት ነው ጎሉ የተቆጠረብን። በእንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነበርን።

ስለ ቡድኑ ውጤት

ውጤት ነው እንጂ በእንቅስቃሴ ያው ነው። በየትኛውም ሜዳ ብልጫ ወስደን ነው የምንጫወተው። በጥቃቅን ስህተቶች ነጥብ እየጣልን ነው። እዛ ላይ ጠንክሮ መስራት ነው። ከዛ ውጭ ግን በእንቅስቃሴ እንዳያችሁት ጥሩ ነው። ግን ሶስት ነጥብ ማሳካት አልቻልንም። በቀጣይ ያንን ለማሳካት እንሰራለን።

ከሜዳቸው ውጭ ስላለው ውጤት

ቅድም እንዳልኩት ተመሳሳይ ችግር ነው። በሜዳችንም ከሜዳችም ውጭም የምንሰራቸው ስህተቶች ተመሳሳይ ናቸው። ያንን ሰው በሰው ቀይረን ሞክረናል። በሁለተኛው ዙር ያንን ለማሻሻል የተሻሉ ተጫዋቾች በማምጣት ቡድናችን ማጠናከር ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ