ሪፖርት| ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ተሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል

በ2020 ህንድ ለምታስተናግደው የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ያከናወነው ቡድኑ በዩጋንዳ አቻው 3-1 ተረቷል።

ገና ጨዋታው በተጀመረ በ15ኛው ሰከንድ በፍጥነት የጀመሩትን ኳሱ ወደ መስመር ያወጡት ተጋባዦቹ ፋውዚያ ናጂምባ ለናሉኬንጌ ጁሌት አቀብላ ጁሌት በሞከረችው ጥሩ ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝረዋል። በዚህ የመጀመሪያ አስደንጋጭ ሙከራ ያልተደናገጡት ባለሜዳዎቹ በ8ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሙከራ በራሳቸው በኩል አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ ከመስመር የተሻገረን ኳስ መሳይ ተመስገን በግንባሯ ወደ ግብ መትታው ግብ ጠባቂዋ ዳፊኒ ኒያይንጋ እንደምንም አውጥታባታለች። ይህ ለግብነት የቀረበ ሙከራ ሞራል የሆናቸው ተጨዋቾቹ ከሁለት እና ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ አረጋሽ ካልሳ እና ቤቲ ዘውዴ በሞከሩት ሌላ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው መክኖባቸዋል።

በጥሩ የኳስ ፍሰት ጨዋታውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ ተጨዋቾች በድጋሜ በ17ኛው እና በ20ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብነት የቀረበ አጋጣሚ ፈጥረው ወቶባቸዋል። ተደጋጋሚዎቹ የኢትዮጵያ ጥቃቶች አጀማመራቸውን ያከበደባቸው ዩጋንዳዎች ግብ ላለማስተናገድ ስራዎች ላይ ተጠምደው ታይተዋል። በተቃራኒው ጥሩ ጊዜን እያሳለፉ የሚገኙት ኢትዮጵያዎች በ22ኛው ደቂቃ ሌላ እጅግ የማይታመን ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። በዚህ ደቂቃ ከመስመር መሬት ለመሬት የተላከን ኳስ ያገኘችው መሳይ ጥሩ ሙከራ ብታደርግም ኳስ እና መረብ ሳይገናኙ ቀርቷል።

ጥቃቶች ቢበዛባቸውም በሜዳቸው የያዙት ውጤት የልብ ልብ የሰጣቸው ዩጋንዳዎች ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ተረጋግተው ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል። በዚህም ቡድኑ በ32ኛው ደቂቃ ኪቭን ናካሲዋ አክርራ በመታችው ኳስ መሪ ለመሆን ጥሯል። ከጨዋታው ጎል እጅግ ፈልገው ሲታትሩ የነበሩት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በ33ኛው ደቂቃ ሌላ የሚያስቆጭ እድል አምልጧቸዋል። በዚህ ደቂቃ ከመስመር የተሻገረን ኳስ ፋና ዘነበ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ መትታው የግቡ ቋሚ አምክኖባታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ዳግም የተነቃቁት ዩጋንዳዎች 2 ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ሰንዝረዋል። በቅድሚያ ሻኪራ ኒይናጋሂራዋ በ39ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅማ የሞከረችው ኳስ ወደ ውጪ ሲወጣባት በመቀጠል ፋውዚያ ናጂምባ በ43ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ያገኘችውን ኳስ በቀጥታ መትታ የግቡ አግዳሚ መልሶባታል። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ምንም ጎል ተጠናቆ ተጨዋቾቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ስልታቸውን በሚገባ አጠናክረው ወደ ሜዳ የገቡት ዩጋንዳዎች የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ጎል ለማስቆጠር ትተውት የሚወጡትን ቦታ በረጃጅም ኳሶች ለመጠቀም ሲጥሩ ተስተውሏል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም ቡድኑ ረጅም ኳስ ወደ ፊት መትቶ ማርጌት ኩኒሂራ ፍጥነቷን ተጠቅማ በ55ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥራ መሪ ሆኗል። በተቃራኒው ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ 4 ጎል የሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያዎች ሙሉ ለሙሉ ማጥቃት ላይ ተወጥረው ታይተዋል። በ55ኛው ደቂቃ ግብ ያስቆጠረችው ማርጌት ኩኒሂራ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ሌላ አስደንጋጭ አጋጣሚ በግል ጠረቷ አግኝታ ወጥቶባታል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ እንደ አዲስ ጥረቶችን የጀመሩት ባለሜዳዎቹ ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው ንግስት በቀለ ወደ ጎል የመታቸው ኳስ በእጅ በመነካቱ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በ61ኛው ደቂቃ የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምግ አረጋሽ ካልሳ ወደ ግብነት ቀይራ ቡድኑ አቻ ሆኗል። ከ3 ደቂቃዎች በኋላም ዩጋንዳዎች ለተቆጠረባቸው ጎል አፋጣኝ ምላሽ ሰጥተው ዳግም መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ የቡድኑ አምበል ናሉኬንጌ ጁሌት ከግብ ጠባቂዋ ጋር የተገናኘችበትን ኳስ ከርቀት ተቀብላ ግብ አስቆጥራለች።

ጨዋታውን በሚገባ የተቆጣጠሩት ተጋባዦቹ በ67ኛው ደቂቃ ሌላ የቆመ ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክረው የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። ዩጋንዳዎች ይህንን ለግብነት የቀረበ ሙከራ ከሰነዘሩ ከ6 ደቂቃዎች በኋላ ሁለተኛውን የቡድኑን ግብ በሚገርም እርጋታ ያስቆጠረችው ናሉኬንጌ ጁሌት ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይራ የቡድኗን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ አድርጋለች።

ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነው ባለሜዳዎቹ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሞክረዋል። እርግጥ ቡድኑ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ በቀሩት ጥቂት ደቂቃዎች አምስት ግቦችን ለማስቆጠር ተዓምሮችን ቢፈልግም ሙከራዎችን ማድረግ አልተወም። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃዎች ሲቀሩትም አረጋሽ ከጥሩ ቦታ ያገኘችውን የቅጣት ምት ወደ ግብ መትታ መሪነቱን ለማጥበብ ሞክራለች። ከአረጋሽ በተጨማሪ ንግስት እና አርያት በግላቸው የተሻሉ ሙከራዎችን ለማድረግ ቢጥሩን ፍሬያማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 4 ደቂቃዎች ሲቀሩት ናሉኬንጌ ጁሌት በጨዋታው ሐት-ትሪክ ሰርታ ለመውጣት ያደረገችውን ጥረት የግቡ ቋሚ አምክኖባታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድንም ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያደርገው ጉዞ ከእንጭጩ ተቋጭቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ