ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወልቂጤ ከተማ

ሁለቱ አዲስ አዳጊዎችን የሚያገናኘው የሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታን የዳሰሳችን ማሳረጊያ አድርገነዋል።

ከመጥፎ አጀማመር በኋላ በጥሩ ጎዳና ላይ መጓዝ ጀምሮ በአስረኛው ሳምንት ሽንፈት ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና በድጋሚ የቀመጠበትን የመጨረሻ ደረጃ ለመላቀቅ ማሸነፍ ላይ ተመስርቶ ጨዋታውን ያደርጋል።

የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

ለተለያዩ አጨዋወቶች አመቺ የሆነ የተጫዋቾች ስብስብ ያለው ሀዲያ ሆሳዕና በነገው ጨዋታ ፈጣን እንቅስቃሴ እና ተሻጋሪ ኳሶችን አብዝቶ በመጠቀም በአግባቡ ለመዋሀድ ያልቻለው ወልቂጤ ከተማ ላይ ጫና ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም እንዲረዳው ሁለቱ ቢስማርኮችን ጨምሮ የመስመር ተጫዋቾቹ ሚና ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል። በተጨማሪም ተጋጣሚው በዲፓርትመንቶች መካከል (በተለይ በአማካይ እና ተከላካይ መካከል እንዲሁም በአማካይ እና አጥቂዎች መካከል) የሚተወውን ሰፊ ክፍተት ለመጠቀም ታታሪዎቹ የመሐል አማካዮች ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ቡድኑ በነገው ጨዋታ የመጀመርያ እቅዱን የመስመር አጨዋወት ካደረገ ባለፈው ሳምንት ጥሩ ጥምረት የታየበትን የወልቂጤ የመከላከል አደረጃጀት ለመስበር እና የአየር ላይ ኳሶችን ለማሸነፍ ሊቸገር እንደሚችል ሲጠበቅ አጥቂዎቹ ከግዙፎቹ ተከላካዮች የሚኖራቸው ፍልሚያ የነገው ጨዋታ የትኩረት ማዕከል ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

በሆሳዕና በኩል ሱራፌል ዳንኤል በቅጣት እንዲሁም  አብዱልሰመድ ዓሊ በጉዳት አይኖሩም።

የወልቂጤ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ

ከተከታታይ ድል አልባ ጉዞ በኋላ ባለፈው ሳምንት ወደ አሸናፊነት የተመለሱት ወልቂጤ ከተማዎች በድጋሚ ግርጌው ላይ ላለመቀመጥ ማሸነፍን እያሰላሰሉ የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃሉ።

የቡድኑ ችግር የሆነው የጎል ማስቆጠር ችግር ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች (ምንም እንኳን ሁለት ጎል ብቻ ቢያስቆጥሩም) በመጠኑ ቢቀርፉም አሁንም ከባድ ስራ እንደሚቀራቸው እሙን ነው። በነገው ጨዋታም የኳስ ቁጥጥር ላይ የበላይነቱን ሊይዙ እንደሚችሉ ቢገመቱም የተደራጀ የማጥቃት ኃይል አለመኖሩ ጨዋታውን ሊያከብድባቸው እንደሚችል ይገመታል።

ቡድኑ በነገው ጨዋታ በአስረኛው ሳምንት የተጠቀመበትን የሦስት የመሐል ተከላካዮች ጥምረት ይዞ እንደሚገባ ሲጠበቅ በሜዳው ስፋት የተጋጣሚን ጥቃት መከላከልን ትኩረት እንሚያደርጉ ይጠበቃል። ፈጣኑ ጫላ ተሺታ ላይ ያተኮረው የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ጥሩ የአጥቂዎች ጥምረት መፍጠር ከቻሉ እና ባለፈው ሳምንት ጎል ያስቆጠረው ሳዲቅ ሴቾ ስልነትን ካከለ ከጨዋታው የሚፈልጉትን ሊያገኙ ይችላሉ።

በወልቂጤ በኩል ይበልጣል ሽባባው በጉዳት ለጨዋታው አይደርስም።

እርስ በርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች ነገ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

አቤር ኦቮኖ

ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቃታ – ፀጋሰው ዴልሞ

ፍራኦል መንግስቱ – አፈወርቅ ኃይሉ – ይሁን እንደሻው – በኃይሉ ተሻገር – ሄኖክ አርፊጮ

ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ

ወልቂጤ ከተማ (3-5-2)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ቶማስ ስምረቱ – ዐወል መሀመድ – ዳግም ንጉሴ

ዓባይነህ ፌኖ – አሳሪ አልመሀዲ – አዳነ ግርማ – ፍፁም ተፈሪ – ጫላ ተሺታ

ሳዲቅ ሴቾ – አህመድ ሁሴን

© ሶከር ኢትዮጵያ