ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ አዳማ ከተማ

ነገ 9 ሰዓት በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የሚደረገው የባህር ዳር ከተማ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በሜዳቸው ዘንድሮ ምንም ጨዋታ ያልተሸነፉት ባህር ዳር ከተማዎች ከደረሰባቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ለማገገምና ዳግም ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት 9 ሰዓትን ይጠባበቃሉ።

የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

በሜዳቸው እና ከሜዳቸው ውጪ የተለያዩ የጨዋታ አቀራረቦችን እያስመለከቱን ያሉት ባህር ዳሮች ነገ እንደ ሌሎቹ የሜዳቸው ላይ ጨዋታዎች ኳስን በቁጥጥራቸው በማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ይገመታል። ነገር ግን ቡድኑ ለዚህ የጨዋታ አቀራረብ የሚሆኑ ተጨዋቾችን ቢይዝም ባሳለፍነው ሳምንት የተጠቀመበትን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ስልት እንደ አማራጭ በመያዝ ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል። በዚህም ከቡድኑ አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እግር ስር የሚነሱን ኳሶችን በማፋጠን የሚደረጉ ፈጣን ሽግግሮች ቡድኑን ሊጠቅሙ ይችላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ፈጣኖቹ የቡድኑ የመስመር አጥቂዎች ጥሩ ብቃት ላይ መገኘታቸው ቡድኑን ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል። በተለይ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው ግርማ ዲሳሳ ከፍፁም ዓለሙ እና ማማዱ ሲዲቤ ጋር እየፈጠረ ያለው ጥምረት ለባለሜዳዎቹ በጎ ነገሮችን ይዞ ሊመጣ ይችላል። ከግርማ በተጨማሪ ቡድኑ በሜዳው ሲጫወት የሚያንፀባርቀው ፍፁም የማማዱን ሽፋን በማግኘት የሚያደርጋቸው የተከላካይ ጀርባ ሩጫዎች አዳማዎችን ፈተና ውስጥ ሊጥል ይችላል።

በሊጉ ብዙ ጎሎችን (16) ተጋጣሚ ላይ ካስቆጠሩ ቡድኖች መካከል ሁለተኛው የሆነው ቡድኑ ያለበት ግብ የማስተናገድ አባዜ እስካሁን አለቀቀውም። ቡድኑ በእንቅስቃሴ ደረጃ ያለው የተከላካይ መስመር የከፋ ባይሆንም እንደአጠቃላይ ያለው የመከላከል መዋቅር ግን ዋጋ ሲያስከፍለው ይስተዋላል። በዋናነት ደግሞ ወደ መሃል አጥብበው የሚጫወቱት የአማካይ ተጨዋቾች እንቅስቃሴ የቡድኑን የኋላ መስመር ሲያጋልጥ ይታያል። ነገም ቡድኑ በዚህ እንቅስቃሴ ዋጋ እንዳይከፍል አስግቷል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በሁለተኛ አጋማሽ እያሳየ ያለውን የደከመ እንቅስቃሴ ካላስተካከለ በስተመጨረሻ ሊቸገር ይችላል።

ባህር ዳር ከተማ ፈጣኑን የመስመር አጥቂ ወሰኑ ዓሊን እና የመስመር ተከላካዩን ሳለአምላክ ተገኝን በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ሙሉ ለሙሉ ውጪ አድርጓል። ከሁለት ቀናት በፊት ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ አምርቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም በቋሚነት ወደ ሜዳ ያልገባው ግዙፉ የመሃል ተከላካይ አዳማ ሲሶኮ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው ተብሏል። በዚሁ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ የቀይ ካርድ ያዩት ሃሪሰብ ሄሱ እና ሳሙኤል ተስፋዬ በቅጣት በነገው ጨዋታ እንደማይሰለፉ ተነግሯል። በተቃራኒው ደረቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከጨዋታ ርቆ የነበረው አቤል ውዱ ልምምዶችን በመጀመሩ ወደ ስብስቡ እንደተካተተ ተጠቁሟል።

የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ አቻ

ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ከአንድ ሳምንት በላይ ልምምድ አቁመው የነበሩት የአዳማ ከተማ ተጨዋቾች ከሁለት ቀን በፊት በሜዳቸው ያስመዘገቡትን የሀዲያ ሆሳዕና ድል ለመድገም እና የመጀመሪያ ከሜዳቸው ውጪ ድል ለማግኘት ዛሬ ማለዳ ባህር ዳር ገብተዋል።
በስብስብ ደረጃ የተሻሉ ነባር ተጨዋቾችን የያዘው ቡድኑ ከፍተኛ የመዋሃድ ችግር ይስተዋልበታል። ይህ ጉዳይ ደግሞ በይበልጥ ከወገብ በላይ ባሉት የቡድኑ ተጨዋቾች ላይ ይስተዋላል። ቡድኑ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የተለያዩ አማራጮችን ቢጠቀምም በተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ በሚፈጠሩ የውሳኔ እና የቅብብል ስህተቶች ግቦችን ለማስቆጠር ይቸገራል። ነገም ቡድኑ ይህንን ጥቃቅን የተናጥል እና የቡድን ስህተቶች አርሞ ወደ ሜዳ ካልገባ ሊቸገር ይችላል።

በሊጉ ብዙ የአቻ ውጤቶች(6) ያስመዘገበው አዳማ ከፍተኛ የአቋም መውጣት እና መውረድ በየጨዋታዎቹ ይስተዋልበታል። በተለይ ደግሞ ቡድኑ ግቦችን የማስቆጠር ችግር ተጠናውቶታል። ነገር ግን ባለ ክህሎቱ በረከት ደስታ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ነገ ባህር ዳሮችን ሊረብሽ እንደሚችል ቀድሞ ይታሰባል። ተጨዋቹ በመስመሮች መካከል በመገኘት ጥቃቶችን ሲሰነዝር እና ለቡድን ጎደኞቹ አጋጣሚዎችን ሲፈጥር ስለሚታይ ነገ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን ይችላል።

ሌላው የአዳማ ከተማ ረጃጅሞቹ ተከላካዮች ለቡድኑ ሁለት አይነት ጥቅም እየሰጡ ይገኛሉ። ተጨዋቾቹ ዋነኛ ስራቸው የሆነውን የመከላከል ስራ እየሰሩ ግቦችን ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ ነው። ይህንን ተከትሎ ነገም ተጨዋቾቹ ከቆመ ኳስ ቡድናቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚጥሩ እሙን ነው። ነገር ግን እነዚህ ተጨዋቾች ካላቸው ግብ የማስቆጠር የበዛ ፍላጎት የተነሳ ቦታቸውን በእንቅስቃሴ ተስበው የሚለቁበት መንገድ ዋጋ እንዳያስከፍላቸው ያሰጋል። ከዚህ በተጨማሪም ምናልባት ቡድኑ በ3 ተከላካዮች የሚጫወት ከሆነ እና የመስመር ተመላላሾቹ (wing back) በአግባቡ ቦታቸውን የማያስከብሩ ከሆነ ከባድ ፈተናዎችን ከፈጣኖቹ የባህር ዳር የመስመር አጥቂዎች ሊቀበል ይችላል።

አዳማዎች ወሳኙ ተጨዋቻቸውን ከነዓን ማርክነህን ጨምሮ ብሩክ ቃልቦሬ እና ሚካኤል ጆርጅ በጉዳት ምክንያት ሳይዙ ወደ ባህር ዳር እንደተጓዙ ተሰምቷል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ዐምና ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያውን ጨዋታ ያለ ጎል ሲያጠናቅቁ ሁለተኛውን ባህር ዳር ከተማ አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ጽዮን መርዕድ

ሚኪያስ ግርማ – ሄኖክ አቻምየለህ – ሰለሞን ወዴሳ – ግርማ ዲሳሳ

ፍፁም ዓለሙ – ፍ/ሚካኤል ዓለሙ – ዳንኤል ኃይሉ

ፍቃዱ ወርቁ – ማማዱ ሲዲቤ – ዜናው ፈረደ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጃኮ ፔንዜ

ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱሌይማን መሐመድ

አዲስ ህንፃ – አማኑኤል ጎበና – ኢስማኤል ሳንጋሬ

በረከት ደስታ – ዳዋ ሆቴሳ – ቡልቻ ሹራ

© ሶከር ኢትዮጵያ