“የዛሬዎቹን ግቦች ሁሌም ከጎኔ ለማይለዩኝ ቤተሰቦቼ መታሰቢያ ማድረግ እፈልጋለሁ” ኦኪኪ አፎላቢ

በ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ የጨዋታ ቀን ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱት መቐለ 70 እንደርታዎች ሀዋሳ ከተማ በትግራይ ዓለምአቀፍ ስታዲየም አስተናግደው የግብ ናዳ በማዝነብ ማሸነፍ ችለዋል። በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለው የ2010 ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ኦኪኪ አፎላቢም ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል።

በክረምቱ ወደ መቐለ ካመራ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በሚጠበቅበት ደረጃ ግቦችን ማስቆጠር ባለመቻሉ ጫና ውስጥ የነበረው ኦኪኪ ቡድኑ ሰበታን ያሸነፈባቸውን ወሳኝ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በመቐለ የግብ አካውንቱን የከፈተ ሲሆን በመቀጠል ስሑል ሸረን በረቱበት ጨዋታ ጎል ቢያስቆጥርም በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ የሚታወስ ነው። ነገር ግን ዛሬ በ14ኛ ሳምንት ጨዋታ ሐት-ትሪክ በመስራት ደጋፊዎቹን ማስፈንደቅ ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ተጫዋቹ ስለግቦቹና አጠቃላይ የመቐለ እስካሁን ቆይታውን በተከታይ መልኩ አጋርቶናል።

” በመቐለ የእስካሁን ቆይታ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ውስጤም ጥሩ ነገር ይሰማኛል። ወደ መቐለ ከመጣሁ በኋላ እስካሁን በሚጠበቀው ደረጃ ግብ አላስቆጠርኩ ይሆናል። ነገርግን በእግርኳስ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ማጋጠሙ አይቀርም። ይህ ደግሞ ምንም አይደለም። አጥቂ ስትሆን አንዳንዴ ታስቆጥራለህ፤ አንዳንዴ መቸገርህ ደግሞ የማይቀር ነው። እግርኳስ የቡድን ሥራ ነው፤ ስናሸንፍም ስንሸነፍም በጋራ ነው። ነገሮች አሁን ላይ ተቀይረዋል። ዛሬ በጣም ደስተኛ ነኝ።

” ይህ ለመጀመሪያ ጊዜዬ አይደለም ሐት-ትሪክ ስሰራ፤ በቀድሞ ክለቤም በተመሳሳይ አስቆጥሬ አውቃለሁ። የዛሬው ግን ለአዲሱ ክለቤ በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል። የዛሬዎቹን ግቦች ሁሌም ከጎኔ ለማይለዩኝ ቤተሰቦቼ መታሰቢያ ማድረግ አፈልጋለሁ። ይህ ፈጣሪ ስራ ነው፤ ፈጣሪ የሚፈቅድ ከሆነ ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ለመፎካከር እና ክለቤንሞ ለመርዳት አስባለሁ።”

©ሶከር ኢትዮጵያ