ነገ ኢትዮጵያን የሚገጥመው የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን በስህተት ወደ ሌላ ከተማ አምርቷል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ነገ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የብሩንዲ አቻውን የሚገጥም ሲሆን ተጋጣሚው ግን እስካሁን ባህር ዳር ከተማ አልገባም።

ፓናማ እና ኮስታሪካ በጥምረት ለሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ነገ የመልስ ጨዋታውን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ያከናውናል። ነገር ግን ብሩንዲሆች ዛሬ ጨዋታው ወደሚደረግበት ከተማ (ባህር ዳር) ይገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም በስህተት ወደ ድሬዳዋ እንዳመሩ ተሰምቷል።

ሶከር ኢትዮጵያ እንዳረጋገጠው ከሆነ ብሩንዲዎች ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቪዛ ማረጋገጫ ቀድመው ቢቀበሉም በፈጠሩት የትኬት አቆራረጥ ስህተት ቀጥር ላይ ወደ ድሬዳዋ አምርተዋል። ዘገባውን እስካጠናከርንበት ሰዓት ድረስ (10:30) ቡድኑ አሁንም በድሬዳዋ እንደሚገኝ ነገር ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድኑን በቀጥታ ወደ ባህር ዳር ለመውሰድ ጥረቶችን እያደረገ እንደሆነ ሰምተናል። የነገውን ጨዋታ አስመልክቶ በሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ከ1 ሰዓት በኋላ ይሰጣል ቢባልም የመሰጠቱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

© ሶከር ኢትዮጵያ