የስሑል ሽረ ሥራ አስኪያጅ እና አሰልጣኝ ስለ ወቅታዊ የክለቡ ሁኔታ ይናገራሉ

በዚህ ሁለት ቀን አነጋጋሪ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ በስሑል ሽረ እና በዋና አሰልጣኙ ሳምሶን አየለ የተፈጠረው ጉዳይ ነው። በትናንትናው ዕለት የጉዳዩ ዝርዝር ሁኔታ ይዘን እንቀርባለን ባልነው መሰረት ከክለቡ ስራ አስከያጅ አቶ ተስፋይ ዓለም እና አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አሰልጣኙ ያነሱት ጥያቄ ተገቢ መሆኑ የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ ሰሞኑ የተፈጠረው ነገር በቅርበት ካለመነጋገር የመነጨ መሆኑን ይናገራሉ። “እንደሚታወቀው ቡድናችን የፋይናንስ ችግር አለበት፤ ባለፈው ሳምንት መጀመርያም ክለባችን ከአጋር ድርጅቶች የሚጠብቀው ገንዘብ ነበር። ሆኖም ይህ ገንዘብ ገቢ ከሆነ በኋላ የአሰልጣኙን ደሞዝ ገቢ ለማድረግ በሒደት ላይ እያለን ነው ይህ ጥያቄ የተነሳው።” ብለዋል።

አሰልጣኙ የደሞዝ ጥያቄ ቢኖራቸውም ከልምምድ የቀሩበት ምክንያት ግን የጤና እክል መሆኑን የገለፁት አቶ ተስፋይ ዓለም እስከ ሰኞ ባሉት ቀናት የአሰልጣኙ የደሞዝ ጥያቄ እንደሚመልሱ ገልፀዋል።

“ልክ ነው ዋና አሰልጣኛችን የደሞዝ ጥያቄ አለው። ከልምምድ የቀረበት ምክንያት ግን መጠነኛ የጤና እክል ስለገጠመው ነው። የደሞዝ ጥያቄውም ቅድም እንዳልኩት ክለቡ ደሞዙን ገቢ ለማድረግ በሒደት እያለ ነው” ብለዋል።

“መረጃው የሰማነው ከሚድያ ነው። አሰልጣኙ በጉዳዩ ላይ ያላቸው ሀሳብ ለቡድን መሪያችን ቢገልፁም ከቡድን መሪው በቅርበት ባለመነጋገራችን ይህ ሊሆን ችሏል። ” ያሉት ስራ አስከያጁ ከቡድናቸው የገንዘብ ችግር ባሻገር በቅርበት ከመነጋገር የመነጫ ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ።

“አሁን ችግሩ በመነጋገር ተፈቷል። በዚህ ሦስት ቀን ደሞዙን እንከፍላለን። ከዚ ጉዳይ በስተጀርባ ሌላ ነገር እንዳለ የሚወራው ነገርም ከእውነት የራቀ እንደሆነ ደጋፊያችን እንዲረዳልን እንፈልጋለን። ሁኔታው በነበረው የገንዘብ ችግር የተፈጠረ ብቻ ነው።” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የነበረው ችግር በንግግር ተፈቶ ቡድኑ በጥሩ መንፈስ እንደሚገኝ አቶ ተስፋይ ዓለም ገልፀዋል።

በጉዳዩ ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ አጭር ቆይታ ያደረጉት ዋና አሰልጣኙ ሳምሶን አየለም ጉዳዩ በንግግር ተፈቶ ለነገው ጨዋታ በጥሩ ዝግጅት እንዳሉ ገልፀዋል። “ልክ ነው የደሞዝ ጥያቄ አለኝ ከልምምድ የቀረሁበት ምክንያት አንዱ በደሞዝ ጥያቄ ቢሆንም ትንሽ ስላመመኝም ነው። አሁን ግን ቁጭ ብለን በመነጋገር ፈተነዋል። ደሞዜም በጥቂት ቀናት ውስጥ ገቢ እንደሚደረግልኝ ክለቡ ነግሮኛል።” ብለዋል

አሰልጣኙ አክለውም ክለቡ ያለው የገንዘብ ችግር እንደሚረዱ ገልፀው ቡድኑ ባለው ጥሩ ወቅታዊ ብቃት እንዲቀጥል ጠንክረው እንደሚሰሩ እና አሁን በጥሩ ጤንነት እንደሚገኙ ገልፀዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ