ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ

በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሠራተኞቹ የጣና ሞገዶቹን 2-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ ድል አስመዝግበው ደረጃቸውን አሻሽለዋል።

ባለሜዳዎቹ ወልቂጤዎች ከሜዳቸው ውጪ ሀዲያ ሆሳዕናን ካሸነፉበት ስብስብ አዳነ ግርማን በፍፁም ተፈሪ ብቻ በመለወጥ ወደ ሜዳ ሲገቡ እንግዶቹ ባህር ዳር ከተማዎች በበኩላቸው በ11ኛው ሳምንት አዳማን ካሸነፈው የመጀመርያ ተሰላፊዎች መካከል የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በአዳማ ሲሶኮ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ፣ ፍፁም ዓለሙ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና ዜናው ፈረደ ምትክ ዳንኤል ኃይሉ፣ ሳሙኤል ተስፋዬ፣ስንታየሁ መንግሥቱ፣ ደረጄ መንግሥቱ እና ፍቃዱ ወርቁን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።

በመጀመሪያዎቹ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ለመቆጣጠር ሲያደርጉት የነበረው ፍትጊያ ኳሱን በመሐል ሜዳ ከማንሸራሸር ባለፈ ብዙ የጠሩ የግብ ማግባት ሙከራዎች እንዳይስተናገዱ አድርጓል። በአንፃራዊነት ወልቂጤዎች የሚያገኙትን ኳስ በቶሎ ወደ መስመር በማውጣት የግብ ማግባት ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረዋል። ቡድኑ በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴ በ8ኛው ደቂቃ በጫላ ተሽታ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ሰንዝሮ መክኖበታል። ሠራተኞቹ በድጋሚ በቀኝ መስመር አጋድሎ ያገኙትን ቅጣት ምት ፍፁም ተፈሪ ሞክሮ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞበታል። ጥቂት ደቂቃ በኋላም በግራ መስመር ጫላ ላይ በተፈፀመ ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት ሳዲቅ ሴቾ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉትን ኳሶች ጽዮን መርዕድ ፈጥኖ በመውጣት ሲያመክንም ታይቷል።

አጀማመራቸው ብዙም ጥሩ ያልነበረው ባህር ዳሮች የጎል ሙከራዎች ለማድረግ ከግማሽ ሰዓት በላይ የጠበቁ ሲሆን በ35ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ክፍል የተሻገረውን ኳስ ፍቃዱ ወርቁ አፈትልኮ ወጥቶ ጥሩ እድል ቢያገኝም ይድነቃቸው ቀድሞ በመውጣት ከግብነት ታድጓታል። የመጀመሪያው አጋማሽም ካለ ጎል ተጠናቆ ተጫዋቾቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ተሻሽለው ለመቅረብ የሞከሩት ሠራተኞቹ ጥቃቶችን ከየአቅጣጫው መሰንዘር የጀመሩት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ነበር። በ47ኛው ደቂቃም አዳነ በላይነህ ያሻገረውን ኳስ ጫላ ተሽታ ሲሞክረው ተከላካዮች ባወጡት አጋጣሚ ወደ ግብ ቀርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ በ53ኛው ደቂቃ ወደ ሜዳ ተቀይሮ የገባው አህመድ ሁሴን ከጫላ ጋር አንድ ሁለት በመጫወት ያገኙትን የግብ እድል አህመድ ሁሴን በቀላሉ አባክኖታል።

በተቃራኒው በዚህ አጋማሽ ግብ እንዳይቆጠርባቸው ተጠንቅቀው ሲጫወቱ የነበሩት የጣና ሞገዱቹ ረጃጅም ኳሶችን እና የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ላይ በማተኮር ግቦችን ለማስቆጠር ሲታትሩ ታይቷል። በዚህ ሒደት 60ኛው ደቁቃ ላይ ወልቂጤዎች በጨዋታው መሪ የሚሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ በግራ መስመር በአግብቡ በመቆጣጠር የተቀነሰውን ኳስ አህመድ ሁሴን በመንሸራተት ለራሱ እና ለቡድኑ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። ዐምናው በከፍተኛ ሊጉ ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ሲፎካከር የነበረው አህመድ በፕሪምየር ሊጉ ጎል ሲያስቆጥር የመጀመርያው ነው።

ከጎሉ ሁለት ደቂቃዎች በኋላ በተመሳሳይ አጨዋወት በረጅም ኳስ ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል የቀረቡት ወልቂጤዎች በባህር ዳር ተከላካዮች ስህተት ታግዘው ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ወልቂጤዎች አብዱልከሪምን በማስገባት ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉ ሲሆን ባህር ዳሮችም ወደ ጨተታው የሚመልሳቸውን ጎል ፍለጋ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ውስጥ በ72ኛው ደቂቃ ስንታየው ከግርማ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ አታሎ ወደ ጎል የሞከረው ኳስ በቀላሉ ይድነቃቸው ሲያወጣበትከ3 ደቂቃዎች በኋላ ፍቃዱ ከሚኪያስ የደረሰውን ኳስ እየገፋ በመግባት ሲሞክረው ተከላካዮች ያወጡትን ኳስ ያገኘው ግርማ ግብ በቀጥታ መትቶ ኢላማውን የሳተበት የሚጠቀሱ ነበሩ።

በግራ መስመር አጋድለው ጥቃቶችን ሲያነጣጥሩ የነበሩት ሠራተኞቹ በ83ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ሊያሰፉበት የቀረቡበት እድል ፈጥረው ነበር። ጫላ ተሺታ ከተከላዋይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ በፍጥነት ወደ ግብ ቢደርስም ጽዮን መርዕድ ቀድሞ በመውጣት አድኖበታል። በ89ኛው ደቂቃ ደግሞ አህመድ ከተከላካዮች በቀጥታ የታሻገረውን ኳስ ከሁለቱ ተካላካዮች መሐል አፈትልኩ በመውጣት የፅዮን አቋቋም በማሳት ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን አስተማማኝ አድርጓል።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች ባህር ዳሮች ያላቸውን አቅም አሟጠው በመጠቀም ግቦችን ለማስቆጠር ጥረዋል። በ90+1ኛው ደቂቃም ከግራ መስመር የተገኘን የቅጣት ምት በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ሲቀር በ90+3ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ወርቁ ለስንታየው ጥሩ ኳስ ከመስመር አሻምቶለት ስንታየው አምክኖታል። ጨዋታውም በባለሜዳዎቹ 2- 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ድሉን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ ደረጃውን ወደ አምስተኛ ከፍ ሲያደርግ ባህር ዳር ከተማ ወደ 6ኛ ዝቅ ብሏል።

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ