የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 2-1 ቡሩንዲ

በባህር ዳር ስታዲየም ቡሩንዲን 2-1 በሆነ ውጤት (በድምሩ 7-1) ያሸነፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በዋና አሰልጣኙ አማካኝነት አስተያየት ሰጥቷል። የቡሩንዲ አሰልጣኝ ሃሳባቸው ባለመስጠታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም።

” ውጤቱ የሚያስከፋ አይደለም፤ ነገር ግን የጠበቅኩትን አላገሁም ” ፍሬው ኃይለገብርኤል
ጨዋታው እንዴት ነበር?

ውጤቱ የሚያስከፋ አደለም። ግን የጠበኩትን ያህል አልነበረም። በአጭርም ሆነ በረጅም ኳስ ለመጫወት ሞክረናል። የተጋጣሚም የግብ ክልል በደንብ ደርሰናል። ነገር ግን አጋጣሚዎችን የመጠቀም ችግር ነበረብን። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ብንጠቀም ኖሮ በርከት ያሉ ግቦችን እናስቆጥር ነበር። በመጀመሪያው ጨዋታ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ተጠቅመን ጨዋታውን ገና በመጀመሪያው አጋማሽ ጨርሰን ነበር። ነገር ግን በሜዳችን ይህንን መድገም አልቻልንም። 

ከመጀመሪያው ጨዋታ ይሄኛው የመልስ ጨዋታ ከብዷችሁ ነበር?

ሁለቱም ጨዋታ ለእኛ ቀላል ነበር። በእግር ኳስ ግን የገጠምከውን ቡድን አደለም ቀላል ነው የምትለው። በራስክ አጨዋወት ነው ጨዋታውን የምታቀለው። በዚህም በእኛ አጨዋወት ጨዋታውን አቅለነዋል። ነገር ግን ያገኘናቸውን እድል በአግባቡ አልተጠቀምንም። ይህ ደግሞ የመጣው ተጨዋቾቹ ላይ በተፈጠረ የበዛ የራስ መተማመን ስሜት ነው። 

የጠበከውን ነገር ከጨዋታው አግኝተካል?

እኔ ብዙ ጎሎችን እናስቆጥራለን የሚል ነገር ጠብቄ ነበር። ለዚህም ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት መርጠን ወደ ሜዳ ገብተናል። ነገር ግን ከላይ በጠቀስኩት ምክንያት ተጨማሪ ግብ ሳናስቆጥር ወተናል። 

በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ ስለታየበት የተቀዛቀዘ አቋም?

ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ተጋጣሚያችን ግጥግጥ ብሎ ለመከላከል ነው አስቦ የመጣው። ከምንም በላይ ግን እኛ ሃገራዊ ስራ እየሰራን ስለሆነ እና ለዋናው ቡድን ግብዓት የሚሆኑ ተጨዋቾችን ለማዘጋጀት እየጣርን ስለሆነ ተጨዋቾችን ቀያይረን ተጠቅመናል። በዚህም በመጀመሪያው ጨዋታ ያልተጫወቱ ተጨዋቾችን በማስገባት እየተመለከትን ነበር። ስለዚህ አዳዲስ ተጨዋቾችን ለማየት ስለፈለግን  ነው በሁለተኛው አጋማሽ ለውጦችን አድርገን የተጫወትነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ