ሀዲያ ሆሳዕና በህክምና ባለሙያው እና ቴክኒክ ዳይሬክተሩ እየተመራ ወላይታ ድቻን ይገጥማል

ትናንት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ግርማ ታደሰን ጨምሮ ሁለቱን ረዳት አሰልጣኝ ከኃላፊነት ያገደው ሀዲያ ሆሳዕና በዚህ ሳምንት በሜዳው ወላይታ ድቻን ሲገጥም የህክምና ባለሙያው ከቴክኒክ ዳይሬክተሩ ጋር በመሆን ክለቡን እየመራ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

ክለቡ በዚህ ሳምንት በሜዳው የ13ኛውን ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ወላይታ ድቻን የሚገጥም ሲሆን ይህን ጨዋታ እየመራ ወደ ሜዳ የሚገባው ደግሞ የክለቡ የህክምና ባለሙያ (ወጌሻ) ቢኒያም ተፈራ መሆኑን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ የክለቡ የቴክኒክ ዳይሬክተር ፍቅረየሱስ ዳንኤል (ዶ/ር) ባለሙያውን እንዲረዱም ተወስኗል። 

ቢኒያም ተፈራ ከዚህ ቀደም ሰበታ ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ወልዋሎ በግብ ጠባቂነት የተጫወተባቸው ክለቦች ሲሆኑ በወልዋሎ እየተጫወተ ባለበት ወቅት በዛው በወሰደው ስልጠና መሠረት ወደ ህክምናው በመግባት በክለቡ በወጌሻነት ሰርቷል፡፡ ከዛም በተጨማሪ በስሑል ሽረም የሰራ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕና በመምጣት ክለቡን በህክምና ሙያው እያገለገለ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት ከወልቂጤ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ በተከሰተው ግርግር የተጎዱ የወልቀጤ ደጋፊዎችን የህክምና እርዳታ ሲሰጥ መስተዋሉን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ማድረጉም የሚታወስ ነው። አሁን ደግሞ አሰልጣኞቹን ከሥራ ያገደው ክለቡ ከህክምናው ባሻገር ከወላይታ ድቻ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ከዶ/ር ፍቅረየሱስ ጋር በጊዜያዊነት እንዲመራ መርጦታል፡፡

በፕሪምየር ሊጉ ደካማ ጉዞን በማድረግ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የተቀመጠው ሀዲያ ሆሳዕና ትናንት ባደረገው ስብሰባ ከውጤት ማጣት ጋር በተገናኘ ዋና አሰልጣኙ ግርማ ታደሰን ጨምሮ ረዳት አሰልጣኙ ኢዘዲን አብደላን እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የሆነውን ምንተስኖት መላኩ ላይ በእግድ ደብዳቤ መሠረት ውሳኔን ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ