ከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች

ባለፉት ቀናት እና ዛሬ የተሰሙ የከፍተኛ ሊግ መረጃዎችን እንዲህ አቅርበናቸዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ እና የከፋ ቡና ጨዋታ ተቋርጧል

ዛሬ ሶዶ ላይ በተደረገው የከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ሶዶ ከተማ ከ ካፋ ቡና ጋር ሲያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሳይጠናቀቅ ተቋርጧል። በግብ ቀዳሚ የሆኑት ካፋዋች ሲሆኑ ባለሜዳዎቹ በፍፁም ቅጣት ምት አቻ መሆን ችለዋል። የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ደግሞ ባለሜዳዎቹ ተጨማሪ ግብ ሲያስቆጥሩ ግቡ የገባበት መንገድ ትክክል አይደለም በማለት በተፈጠረ እሰጣ ገባ ጨዋታው ሳይቀጥል ቀርቷል። ቀጣይ የአወዳዳሪው አካል ውሳኔም የሚጠበቅ ይሆናል።

በዚህ ጨዋታ ዙርያ ወደ ሶዶ ያመራው ከፋ ቡና ቀድሞ ጨዋታው በዚህ ቀን እንደሆነ አልተነገረንም በማለት ለአወዳዳሪው አካላት ቅሬታ ማቅረባቸው የተሰማ ሲሆን ጨዋታው በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነው እንደሚጫወቱም ቀደም ብለው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀው ነበር።

ደደቢት ከሁለቱ የውጭ ተጫዋቾች ጋር ተለያይቷል

ደደቢቶች ከፉሴይኒ ኑሁ እና አንቶንዮ አቡዋላ ጋር ተለይቷል። ሁለቱም ተጫዋቾች ባሳለፍነው ሳምንት ውላቸው አልቆ ክለቡ ውላቸውን ያራዝምላቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን ቡድኑ ግን የተጫዋቾቹን ውል ሳያራዝም ከተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቷል።

ፉሴይኒ ኑሁ ከዚ ቀደም በፕሪምየር ሊጉ ክለብ መቐለ 70 እንደርታ ቆይታ ማድረጉ ሲታወስ ኒው ኢዱብያሴ ፣ አሻንቲ ጎልድ እና ሸሪፍ ቲራስፖል ሌሎች የተጫወተባቸው ክለቦች ናቸው። ሌላው ከክለቡ ጋር የማይቀጥለው ናይጀርያዊው አንጋፋ ተከላካይ አንቶንዮ አቡዋላ ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ክለቡን የተቀላቀለው ይህ ግዙፍ ተከላካይ ቡድኑን ከተቀላቀለበት ግዜ አንስቶ ክለቡን በቋሚነት ያገለገለ ሲሆን ውሉ ባለመራዘሙም ከክለቡ ጋር ተለያይቷል።

ሀላባ ከተማ ከአሰልጣኙ ጋር ተለያየ

በ2011 የውድድር ዘመን በዋና አሰልጣኝነት ሀላባን ተረክበው የነበሩት አሰልጣኝ ካሊድ መሀመድ ከክለቡ ጋር ተለያዩ፡፡ የቀድሞው ኢትዮጵያ ቡና እና ዳሽን ቢራ አሰልጣኝ አምና ሀላባ ከተማን ከያዙ በኃላ ጠንካራ ጥሩ መሻሻል እንዲያሳይ ቢረዱም ዘንድሮ ግን ደካማ የውድድር አየዓመትን በማሳለፉ መነሻነት ለክለቡ ባስገቡት የመልቀቂያ ጥያቄ ቀሪ የሰባት ወር ኮንትራት እያላቸው ተለያይተዋል፡፡ ክለቡንም ከዚህ ቀደም ማሰልጠን የቻሉት አሰልጣኝ አላምረው መስቀሌ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ቀሪውን ጨዋታ እየመሩ ሀላባን ከወራጅ ስፍራ ለማውጣት ሀላፊነት ተረክበዋል፡፡

አንዋር ያሲን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተለያዩ

ክለቡን ከአምና ጀምሮ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመመለስ ሀላፊነት ተሰቷቸው ክለቡን የተረከቡት የቀድሞው የክለቡ አማካይ አንዋር ክለቡ ካሰበው ዳግም ወደ ሊጉ የመመለስ ዕቅድ አንፃር አምናም ሆነ ዘንድሮም መድገም እየቻሉ አይደለም በሚል ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ቀሪ የሰባት ወራት ውል እየቀራቸው አሰናብቷቸዋል። ክለቡን በተለያዩ ጊዜያት ያሰለጠኑት እና ዝነኛው የ1993 ቡድንን የመሩት ጉልላት ፍርዴ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆነው ቡድኑን የሚመሩ ይሆናል፡፡

አክሱም ከተማ ውሳኔ ተላለፈበት

ባለፈው የውድድር ዓመት በአክሱም ከተማ ሲጫወቱ የነበሩት ሙሉዓለም በየነ እና ሄኖክ በየነ የተባሉ ሁለት ተጫዋቾች በክለቡ ቀሪ የውል ጊዜ እየያላቸው ክለቡ እንዳሰናበታቸው በመለግፅ የቅሬታ ደብዳቤን ያስገቡ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ጉዳዩን በፍጥነት እንዲፈታው በተደጋጋሚ በክለቡ ላይ ቢወስንም ተግባራዊ ባለማድረጉ ፌዴሬሽኑ የመጨረሻ ያለውን ውሳኔ አክሱም ላይ አስተላልፏል፡፡ በዚህም መሠረት ክለቡ በአስር ቀናት ውስጥ ተጫዋቾቹ የጠየቁትን የሦስት እና የአራት ወራት ደመወዝ ተፈፃሚ ያድርግ ያለ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ፌዴሬሽኑ ከሚያዘጋጀው ማንኛውም ውድድር እንደሚታገዱ ውሳኔው አመላክቷል፡፡

አርባምንጭ ከተማ ድጋፍ ተደረገለት

በከፍተኛ ሊጉ እየተካፈለ ያለው አርባምንጭ ከተማ የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገለት፡፡ ለክለቡ ድጋፉ ያደረገው አሚባራ እርሻ ልማት ድርጅት የተሰኘ ሲሆን ከ120 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግም ነው ድጋፍ ያደረገው፡፡ ለክለቡ ሙሉ ተጫዋቾች አሰልጣኞች እና አመራሮች ደረጃውን የጠበቀ አልባሳት እና ጫማን ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በቀጣይም በወጥነት ክለቡን ስፖንሰር ለማድረግ እና በሚታየው ክፍተት ሁሉ ከክለቡ ጎን ለመቆም የገንዘብ የእርሻ ልማቱ ባለቤት አቶ መሐመድ አብዱለጢፍ ቃል ገብተዋል። የክለቡ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ማቲዮስ ድጋፍ በመደረጉ አመስግነው የቡድኑ ተጫዋቾችም ይህን አይተው በተነሳሽነት ውጤታማ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የክለቡ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እና ተጫዋቾችም ከዚህ ሽልማት በመነሳት አርባምንጭ ከተማን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ጠንክረው እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኘው ጅማ አባቡና

በመጣበት ዓመት ከፕሪምየር ሊጉ ከወረደ በኋላ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ የማይገኘው ጅማ አባ ቡና የፋይናንስ ችግሩን ከስር መሰረቱ መፍታት ተስኖታል። በዚህም ምክንያት ለቡድኑ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት “ቡድኑ አሁን ላይ በጣም ተቸግሯል። በቀጣይ የፋይናስ ችግሩን ካልፈታ ጨዋታዎች ማከናወን ያቅተዋል።” ሲሉ ገልፀዋል። በጉዳዩ ዙርያ በቀጣይ ቀናት ሰፋ ያለ ዘገባ ይዘን እንቀርባለን።

የቀድሞ ደሴ ተጫዋቾች ቅሬታ ውሳኔን አገኝቷል

በደሴ ከተማ ዐምና ሲጫወቱ የነበሩ ሦስት ተጫዋቾች ከፌዴሬሽኑ ውሳኔን አግኝተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በ2011 በክለቡ ሲጫወቱ የነበሩት ሊቁ አልታዬ፣ ዓለማየሁ ማሞ እና ሚሊዮን በየነ በክለቡ ከሦስት እስከ አራት ወር ደመወዝ ያልተከፈላቸው ሲሆን በውሳኔው መሠረት ለተጫዋቾቹ ክለቡ እንዲከፈል አልያም ወደ ስራ ገበታቸውም እንዲመለሱ ፌድሬሽኑ ወስኗል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ