ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አዳጊዎቹ ወልቂጤ ከተማዎች ተፈትነው ነጥብ ለመጋራት ተገደዋል።

ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአዳማ ከተማ 3-0 ከተረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ የመስመር አጥቂውን ሀብታሙ ታደሰን በአቤል ከበደ ብቻ ተክተው ወደ ዛሬው ወሳኝ ጨዋታ ሲገቡ ወልቂጤ ደግሞ ባህርዳርን ከረታው ስብስብ ውስጥ 3 ተጫዋቾችን ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም መሠረት ኤፍሬም ዘካርያስ፣ አዳነ ግርማ እና አሕመድ ሁሴንን በዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።

ወልቂጤዎች ለወትሮው ኢትዮጵያ ቡና ይጠቀምባቸውን የነበሩ ሒደቶችን እንዳይጠቀም በማድረግ ውጤታማ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ ኳስ ለመመስረት የሚጠቀሙበት አማኑኤል ዮሐንስን በኤፍሬም ዘካርያስ በማስያዝ የተከተሉት መንገድ ለኢትዮጵያ ቡና ኳስን መመስረት እጅግ አዳጋች ያደረገባቸው ሲሆን በመስመር ለጥጠው ለማጥቃት የሚሞክሩት የመስመር አጥቂዎቻቸውን በሳዲቅ እና ጫላ ትጋት ይህን የሜዳ ስፋት ለመጠቀም የሚያደርጉትን ጥረት ፈታኝ አድርገውባቸው ተስተውሏል።

በ10ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር ተከላካይ አህመድ ረሺድ የሰራውን የማቀበል ስህተት ተጠቅሞ አሕመድ ሁሴን አግኝቶ ወደ ቡና ሳጥን በመግባት በተረጋጋ አጨራረስ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በጊዜ በተቆጠረችው ግብ የልባቸው የደረሰ የሚመስሉት የወልቂጤ ተጫዋቾች ጨዋታውን በጀመሩበት ሒደት ከመቀጠል ይልቅ ወደ ኃላ ሰብሰብ ብለው ለመከላከል ሲጥሩ ተስተውሏል። በ19ኛው ደቂቃ የግቧ ባለቤት አህመድ ሁሴን ቡድኑን መሪነት ከፍ ማድረግ የሚችልበትን ተጨማሪ እድል ከማእዘን ምት ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ወልቂጤዎች በማፈግፈጋቸው የተሻለ የመጫወቻ ሜዳ ያገኙት ቡናዎች በተለይ ከ20ኛው ደቂቃ በኃላ ይበልጥ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። በ24ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን ከቅጣት ምት ሞክሯት ከግቡ ከአናት በላይ ለጥቂት በወጣችበት ሙከራ የወልቂጤን ግብ መፈትሽ የጀመሩት ቡናዎች በ27ኛው ፈቱዲን ጀማል ከሳጥን ውጭ ከርቀት አክርሮ የመታውና የግቡ አግዳሚ በመለሰበት ኳስ ለግብ በቀረቡበት አጋጣሚ ጫናቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። በ29ኛው ደቂቃም ጥረታቸው ሰምሮ በወልቂጤ ሁለቱ የመከላከል መስመሮች መካከል በነፃነት ኳስን ያገኙት ቡናዎች ወደ ግብ በማምራት በሳጥኑ የግራ ጠርዝ ገባ ብሎ በተሻለ አቋቋም ላይ የነበረው ፍቅረየሱስ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።

በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት ወልቂጤዎች በ38ኛው ደቂቃ እጅግ ግሩም አጋጣሚ አግኝተው ነበር። አዳነ በላይነህ ከራሳቸው ሜዳ ያሳለፈተለትን ኳስ አህመድ ሁሴን በአስደናቂ ፍጥነት ከፈቱዲን ጀርባ ተነስቶ ኳሷ ላይ ደርሶ አህመድ አስቆጥረ ተብሎ ሲጠበቅ በረከት አማረ ያመከነበት ኳስ በጣም አስቆጭ አጋጣሚ ነበር። የመጀመርያው አጋማሽም 1-1 ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ኢትዮጵያ ቡናን ተጫዋቾች ከግብ ክልላቸው ኳስን እንዳይመሰርቱ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት እጅግ ውጤታማ ነበር። አማኑኤልን በኤፍሬም በመጠቀም ሙሉ ለሙሉ ከዚህ የምስረታ ሂደት የነጠሉበት መንገድና ሁለቱም የመሀል ተከላካዮችን ጫና በማሳደር ግብጠባቂው በረከት አማረ ኳሶችን ለማስጀመር ተቸግሮ ተስተውሏል። በዚህም ሂደት እስከ 60ኛው ደቂቃ ድረስ በ6 አጋጣሚዎች ከበረከት አማረ ለመስመር ተከላካዮች ታሳቢ የተደረጉ ኳሶች ሲበላሹ ለማስተዋል ችለናል።

ጫና በመፍጠር አልያም በመልሶ ማጥቃት እየተጫወቱ የነበሩት ወልቂጤዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን ማሸነፍ የሚችሉባቸውን ምርጥ ምርጥ የመልሶ ማጥቃት ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም አህመድ ሁሴን በሶስት አጋጣሚዎች እንዲሁም ጫላ ተሺታ ሁለት አጋጣሚዎች ያመከኗቸው ወርቃማ አጋጣሚዎችን መጠቀም ቢችሉ ኖሮ የጨዋታው ውጤት በወልቂጤዎች የበላይነት መጠናቀቅ በቻለ ነበር።

በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል በወልቂጤዎች ጫና የተነሳ በርከት ያሉ ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመጣል ለመጠቀም ቢሞክሩም የወልቂጤ የመከላከል አደረጃጀት በቀላሉ የሚቀመስ አልሆነም። በ66ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል አልፈው የሄዱትን ኳስ ሚኪያስ አሳልፎለት አቤል ከበደ ከወልቂጤ ጠርዝ ወደ ግብ የላካትና ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣችበት ኳስ ውጭ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ተስተውሏል። በዚህም ሁለተኛው አጋማሽ ጎል ሳይቆጠርበት 1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተገባዷል።

በዚህ ውጤት መሠረት ለተከታታይ 4ኛ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማስመዝገብ የተቸገሩት ቡናማዎቹ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአንፃሩ ወልቂጤዎች በመልካም ግስጋሴያቸው ገፍተውበት በነበሩበት 8ኛ ላይ ረግተዋል።

©ሶከር ኢትዮጵያ