ወልቂጤ ከተማ ከቶጓዊው አጥቂ ጋር ሲለያይ ጋናዊ አማካይ ለማስፈረም ተስማማ

ወልቂጤ ከተማ ከቶጓዊው የፊት አጥቂ ጃኮ አራፋት ጋር ሲለያይ ጋናዊውን አማካይ አልሀሰን ኑሁን ለማስፈረም ቅድመ ስምምነት ፈፀመ፡፡

ቡድኑ በክረምቱ ራሱን ለማጠናከር ያስፈረመው አንጋፋው አጥቂ ጃኮ አራፋት በክለቡ ታሪክ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጎል ማስቆጠር ቢችልም በክለቡ በተጠበቀው ልክ ማገልገል ባለመቻሉ ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ከስብስቡ ውጪ ሆኖ የቆየ ሲሆን በመጨረሻም ሊለያዩ ችለዋል፡፡ ተጫዋቹ በክለቡ ቀሪ ጥቅማጥቅሞቹ የሚቀሩት ሲሆን ይህ ከተፈፀመለት በኃላ በቅርቡ ወደ ሌላ ክለብ ሊዛወር እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በሌላ የክለቡ ዜና የ31 ዓመቱን ጋናዊ የመሐል አማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነውን አልሀሰን ኑሁን ለማስፈረም ቅድመ ስምምነትን ፈፅሟል። ለጋናዎቹ ሪል ስፖርቲቭ፣ አሻንቲ ጎልድ እና ከ2017 ጀምሮ ደግሞ ለኢዱቢያስ ዩናይትድ በመጫወት ላይ የነበረው ይህ ተጫዋች በ2011 በጥር የዝውውር መስኮት ሲዳማ ቡናን ለመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ከወረቀት ጉዳዮች በጊዜ ያለ መጠናቀቅ ጋር በተያያዘ ለክለቡ ለመፈረም ሳይችል የቀረ ሲሆን ከአንድ ሳምንት በኋላ በሚከፈተው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ወልቂጤ ከተማን ለመቀላቀል ቅድመ ስምምነት አድርጓል፡፡ ተጫዋቹ የቀድሞው የመቐለ እና በቅርቡ ከደደቢት ጋር የተለያየው ፈይሴኒ ኑሁ ታናሽ ወንድምም ነው፡፡

ክለቡ በተጨማሪ በቀጣዮቹ ቀናት አንድ ጋናዊ የግራ መስመር ተከላካይ እና ከሀገር ውስጥ ደግሞ በተመሳሳይ የግራ ተከላካይ ሊያስፈርም እንቅስቃሴ ላይ ስለመሆኑ ሰምተናል፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ