የከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች

ከሰሞኑ የተሰሙ የከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎችን ሰብሰብ አድርገን እንዲህ አቅርበናቸዋል፡፡

የሀላባ ከተማ ቅጣት

የዲሲፕሊን ኮሚቴ በምድብ ለ ሀላባ ከተማ ከሀምበሪቾ ጋር በነበረው ጨዋታ ሀላባዎች ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ከሜዳ ጥለው ወጥተዋል በሚል ጠንከር ያለ ቅጣት አስተላልፏል። ቡድኑ 100 ሺ ብር ሲቀጣ ዋና አሰልጣኙ እና ቡድን መሪውም ቅጣት የተላለፈባቸው ሲሆን ጨዋታውን 1-0 እየመራ የነበረው ሀምበሪቾ ደግሞ 3 ግብ እና 3 ነጥብ በፎርፌ ማግኘት ችሏል።

የቡታጅራ ከተማ ቅሬታ

በዘጠነኛው ሳምንት ሺንሺቾ ላይ ከንባታ ሺንሺቾን ከቡታጅራ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በእንግዳው ቡድን ቡታጅራ 2-0 አሸናፊነት ቢጠናቀቅም በጨዋታው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሉን በመጥቀስ ያላቸውን ቅሬታ የቡታጅራ ከተማ ፕሬዝዳንት አቶ ነስሩራ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። “እግርኳሱ እንዲያድግ የምንፈልግ ከሆነ ውጤቱን በፀጋ መቀበል መቻል አለብን። በዘጠነኛው ሳምንት ሺንሺቾ ላይ የተደረገው ነገር በጣም አሳፋሪ ነው። በሁለቱ ከተሞች መልካም ግንኙነት እንዲኖር ነው የምንፈልገው። ይህን የበለጠ የሚያጠናክረው ደግሞ እግርኳሱ ነው። በሺንሺቾ ይህን አላየንም። እኛም አጥፍተን ቢሆን እንኳን እንዲ አይነት አፃፋዊ ነገር ማድረግ የለባቸውም።” በማለት ቅሬታቸውን ገልፀዋል። አቶ ነስሩራ አያይዘውም በ51ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ የተወገደባቸው ተጫዋች መኑሩን ገልፀው በተፈጠረ ሁከት ደጋፊዎቻቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰ ገልፀው አወዳዳሪው አካል ውሳኔውን በቶሎ እንዲሳውቅ ጠይቀዋል።

የተስተካካይ ጨዋታዎች ቀናት አለመታወቅ

ከፍተኛ ሊግ አንደኛውን ዙር ሊያገባድድ የአንድ ሳምንት መርሐ ግብር እና ተስተካካይ ጨዋታዎች ብቻ የቀረ ሲሆን ቅሬታዎች እዚህም እዚያም መስተናገድ እየጀመሩ ነው። ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰቶች፣ ውዝግቦች እና ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ቢኖሩም አወዳዳሪው አካል እስካሁን ምላሽ መስጠት ላይ እምብዛም መሆኑ አስገራሚ ሆኗል። ከውሳኔዎች መዘግየት ባሻገር ተስተካካይ ጨዋታዎች መቼ እንደሚደረጉ አለመታወቁ በተለይ ለመሪነት በሚደረግ ፉክክር ውስጥ ያሉ ቡድኖችን ቅሬታ እንዲያቀርቡ በር ከፍቷል።

የአርባምንጭ ከተማ ድጋፍ

ከሰሞኑ ድጋፍ የተደረገለት አርባምንጭ ከተማ ሌላ ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡ በአዲስ አበባ የጋሞ ልማት ማኅበር ለክለቡ የ25 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ዳግም ክለቡ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ደግሞ በቀጣይ ጊዜያት ከክለቡ ጎን እንደሚቆም ማኅበሩ ገልጿል፡፡
የካፋ ቡና ቅሬታ

ጥር 28 ዕለተ ሐሙስ የተደረገው የወላይታ ሶዶ እና ካፋ ቡና ጨዋታ የተቋረጠበትን ሁኔታ የሚገልፅ እና በዕለቱ ዳኛ ያላቸውን ቅሬታ የያዘ ደብዳቤ ለእግርኳስ ፌዴሬሽኑ በማስገባት ውሳኔን እየተጠባበቁ ይገኛል።

ከድር ሳልህ ቀዶ ጥገናው በተሳካ ሁኔታ አጠናቋል

በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ሰማያዊዎቹን ተቀላቅሎ ከቡድኑ ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው የመስመር ተጫዋቹ ከድር ሳልህ ቀዶ ጥገናው በተሳካ ሁኔታውን አጠናቋል። ከሳምንታት በፊት ትርፍ አንጀት እንዳለበት የተነገረው ተጫዋቹ ከቀናት በፊት ቀዶ ጥገናው በተሳካ ሁኔታ አድርጎ በአሁን ሰዓት በጥሩ ሁኔታ እያገገመ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በፊት ለወልዋሎ ፣ አውስኮድ እና አዲስ አበባ ከተማ መጫወት የቻለው ይህ የመስመር አማካይ በታሰበው ጊዜ የሚያገግም ከሆነ በቀጣይ ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ መድን ከአሰልጣኙ ጋር ተለያይቷል

በ2011 ዓ.ም ኢትዮጽያ መድን በምክትል አሰልጣኝነት የተቀላቀሉት ያሬድ ቶሌራ በያዝነው ውድድር ዓመት ከአሰልጣኝ በፀሎት ጋር የተለያየውን መድንን ቦታ በመቀበል ስራቸውን ቢጀምሩም ስኬታማ ጊዜ ማሳለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። አሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራም በገዛ ፍቃዳቸው ስራቸውን ለመልቀቅ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን በቀጣይ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ፍለጋ ላይ እንደሚሰራ ይጠበቃል።

ደሴ ከተማ ሊታገድ ተቃርቧል

ለአራት ጊዜያት ያክል አራት ተጫዋቾች ውል እያለባቸው በማሰናበቱ ተደጋጋሚ ደብዳቤ ከፌድሬሽኑ ሲደርሰው የነበረው ደሴ ከተማ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከፌዴሬሽኑ ደርሶታል፡፡ “ክለቡ ሚሊዮን በየነ፣ ዓለማየሁ ማሞ፣ ሊቁ አልታዬ እና ኃይለማርያም እሸቱን ውል እያለባቸው በማሰናበቱ የተላለፈበትን ውሳኔ በዚህ ሳምንት ተፈፃሚ ካላደረገ የዕግድ ውሳኔን አስተላልፋለሁ” ብሏል የዲሲፕሊን ኮሚቴው፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ