ሁለተኛው ዙር የባየር ሙኒክ ስልጠና ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከጀርመኑ ባየር ሙኒክ እግርኳስ ክለብ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የ2ኛ ዙር የጀማሪ እግርኳስ አሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ ተጠናቀቀ።

ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተግባር እና በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ለ60 ሰልጣኞች ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ዛሬ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ አቶ ሰለሞን ገ/ሥላሴ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የመዝግያ ሥነ ስርዓቱ ተካሂዷል።

ከ12-15 ዓመት በታች ታዳጊዎች አሰለጣጠን ላይ ትኩረቱን ባደረገው በዚህ የአምስት ቀን ቆይታ ውስጥ በመጀመርያው ዙር ስልጠናውን ከወሰዱ 60 ሰልጣኞች መካከል ሠላሳዎቹ ለሁለተኛው ዙር ሲያልፉ ከአንድ ዓመት በኃላ የሚሠጠውን ሦስተኛ ዙር ስልጠናን ጥቂት ሰልጣኞች ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸው ለማወቅ ችለናል። ስልጠናውን ከተከታተሉ ሰልጣኞች መካከል የጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚዋ አሰልጣኝ ወርቅነሽ ዘለሌ ብቸኛዋ እንስት አሰልጣኝ ነበረች።

በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ በንግግራቸው ” የአፍሪካ እግርኳስ መስራች ሀገር ሆነን ሳለ ወደ ኃላ ቀርተናል። ባለፈው ጁቡቲን ድሬዳዋ ላይ ለማሸነፍ በጣም ተቸግረን እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። እነርሱ እየሰሩ እኛ ጁቡቲን ጠብቀናታል ማለት ነው። አሁን መንቃት አለብን ልንቆጭ ይገባል። ዓለም ከደረሰበት ደረጃ መድረስ ይጠበቅብናል። እናንተ በጨርቅ ኳስ አልፋችኃል። በዚህ ዘመን ያሉ ታዳጊዎች ግን በዚህ መንገድ ማለፍ የለባቸውም። ዘመኑ ከሚጠይቀው ሳይንስ ጋር ሁሌም መሄድ ያስፈልጋል። በስልጠናው ጠቃሚ ነገር አግኝታችኃል። ሁሌም ራሳችሁን ማብቃት ማንበብ ያስፈልጋል። ይህ ስልጠና አዳራሽ ውስጥ መቅረት የለበትም። ልጆች ላይ መውረድ ይገባዋል። ስልጠናው የመጨረሻ አይደለም። በርቱ ጠንክሩ” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ