ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ነገ ከሚደረጉ የ15ኛ ሳምንት ጨተታዎች መካከል ብርቱካናማዎቹ ምዓም አናብስትን የሚያስተናግዱበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በውጤት ማጣት ምክንያት ከአሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ጋር የተለያዩት ብርቱካናማዎቹ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት የግድ ይላቸዋል።

የድሬዳዋ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

ከሌሎች የቡድኑ ክፍሎች የተሻለ ጥንካሬ ያለው የአጥቂ ክፍል ያላቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ነገም እንደባለፉት ጨዋታዎች በሙህዲን ሙሳ እና ሬችሞንድ አዶንጎ መሰረት ያደረገ የረጃጅም ኳስ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም በጉዳት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ የሆነው ሙህዲን ሙሳ ለጨዋታው የማይደርስ ከሆነ ቡድኑ ተለዋጭ አቀራረቡን ይዞ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

በአጨዋወቱ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የማይቸገሩት ድሬዎች በአጨራረስ ያላቸው ትልቅ ክፍተት ግን ቡድኑ እንደሚፈለገው ግቦች እንዳያስቆጥር አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች የተከላካይ ክፍሉ ሳስቶ የተጋጣሚን የማጥቅያ መንገዶች ለመመከት ሲቸገር የተስተዋለው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ስህተቱን አርሞ ለተጋጣሚ ጠንካራ አጥቂዎች በቂ ዝግጅት ካላደረገ ሰለባ መሆኑ አይቀሬ ነው። በተለይም የነገው ተጋጣሚያቸው መቐለ ሁለት አይምሬ አጥቂዎች ጥምረት የሚጠቀም ቡድን እንደመሆኑ ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም።
ቡድኑ በረከት ሳሙኤልን በጉዳት የማያሰልፍ ከሆነም ለብርቱካናማዎቹ መጥፎ ዜና ነው።

ድሬዎች በነገው ጨዋታ ያሬድ ታደሰ እና ረመዳን ናስር በጉዳት አያሰልፉም ሙህዲን ሙሳ እና በረከት ሳሙኤልም የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው።

የመቐለ 70 እንደርታ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

ከተከታታይ ሽንፈቶች በኃላ አገግመው ሀዋሳ ከተማን በሰፊ ውጤት ያሸነፉት መቐለዎች ወደ መሪዎቹን ለመከተል ወይም ለመቅደም የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

ባለፈው ጨዋታ ከቀጥተኛው አጨዋወት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልክ ለውጥ አድርገው ኳስ ተቆጣጥረው እና በመስመር በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ቻምፒዮኖቹ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በነገው የሜዳ ውጭ ጨዋታ ግን ወደ ቀጥተኛው አጨዋወታቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይገመታል።

ቡድኑ በተጠቀሰው ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሶ በርካታ የግብ ዕድሎች መፍጠሩ በነገው ጨዋታ ውጤታማ ያደረገውን አጨዋወት አይቀይርም የሚል ቅድመ ግምት ሊያስነሳ ቢችልም አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች እንደመረጡት ቀጥተኛ አቀራረብ የራቀ አጨዋወት ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ለዚህ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰውም የአሰልጣኙ የሜዳ ውጭ አቀራረብ ነው።

መቐለዎች በነገው ጨዋታ ያሬድ ከበደ እና ሚካኤል ደስታን በጉዳት ሲያጡ ከጉዳት የተመለሰው ዮናስ ገረመውም ከቡድኑ ጋር ወደ ድሬ አልተጓዘም። ቅጣት ላይ የነበረው ዳንኤል ደምሴ ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።

እርስ በርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው መቐለ 3 በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ድሬዳዋ አንድ አሸንፏል። መቐለ 6፤ ድሬ 3 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ፍሬዘር ካሳ – በረከት ሳሙኤል – ዘሪሁን አንሼቦ – ያሲን ጀማል

ቢንያም ጥዑመልሳን – ፍሬድ ሙሸንዲ – አማኑኤል ተሾመ – ኤልያስ ማሞ

ሬችሞንድ አዶንጎ – ሙህዲን ሙሳ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – ላውረንስ ኤድዋርድ – አስናቀ ሞገስ

አሸናፊ ሀፍቱ – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ዳንኤል ደምሴ – ኤፍሬም አሻሞ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦኪኪ አፎላቢ

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ