የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 3-1 ወላይታ ድቻ

በ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተከታታይ ጨዋታዎች ሙሉ ሶስት ነጥብ ማስመዝገብ ተስኖት የቆየው ኢትዮጵያ ቡና ከመመራት ተነስቶ ወላይታ ድቻን 3-1 ካሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።


“ሰዎችን ይዘን መሄድ ስለቻልን የተገኙ ግቦች ናቸው”- ካሳዬ አራጌ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለጨዋታው

” ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ ሁሌም እንደምለው የመጀመሪያ አላማችን የነበረው ጨዋታውን መቆጣጠር ነበር ምንም እንኳን ከስህተት የፀዳ ነው ባይባልም ያንን ማድረግ ተችሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ከእኛ ቀድመው ግብ ማስቆጠር ቢችሉም እኛ ከእነሱ በተሻለ እድሎችን መፍጠር ችለን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያው የነበረን ነገር ወደ ጎል ስላደረሰን ያንን ነገር አጠናክረን ለመቀጠል አስበን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። በሁለተኛው አጋማሽ እድሎችን መፍጠር ችለናል ፤ የተወሰኑትንም ወደ ግብነት መቀየር ችለናል።”

ስለተጫዋቾች ጫና

“ጫናዎች አሉ ፤ ከባዱ ነገር እሱ ነው። በተወሰነ ደረጃ ጫናው መኖሩ አስፈላጊ ነው። ግን መጠኑ እየበዛ ሲመጣ የተጫዋቾቹን ማስተዋላቸውን እያጠፋ ይመጣል። እንድናሸንፍ ይፈለጋል ፤ እንደአሰልጣኝ ደግሞ ለማሸነፍና ወደ ጎል እንድንሄድበት የምንፈልገው መንገድ አለ። በጣም ጫና ውስጥ ሲገቡ ያንን ይረሱና ቶሎ ወደ ጎል መድረሳቸውን ብቻ ነው የሚያዩት። ነፃ ሰው መኖሩ ፣ እንቅስቃሴ ከአእምሯቸው ይወጣል። በተወሰነ መልኩ ይህ ነገር አሁንም አለ። እንደ አሰልጣኝ ተጫዋቾችን ከጫና መጠበቅ የእኛ ስራ ቢሆንም በተወሰነ መልኩ ውጤት እየመጣ ሲሄድ እየቀነሰ የሚመጣ ነገር ነው።”

ግቦቹ ስለተቆጠሩበት መንገድ

” ጎሎቹ የተቆጠሩት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ቀርበን በመጫወታችን ነው። ተጋጣሚ ጎል አካባቢ ተጠግቶ መጫወት በጣም አስቸጋሪ ነው። አንደኛ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ክምችት አለ፤ ሁለተኛ በተጋጣሚ ጎል አካባቢ ቁጥርህን ለማብዛት አካሄድህም ወሳኝነት አለው። ሰዎችን ይዘን መሄድ ስለቻልን የተገኙ ግቦች ናቸው። ለምሳሌ ሁለተኛ ግብ ሲቆጠር ኳሱ የተነሳው ከአህመድ ነው። አህመድ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ነው። ነገር ግን እንቅስቃሴው እሱን እዛ ድረስ ይዞት እንዲሄድ በመቻሉ ግቡ ተቆጥሯል።”

“በሁለተኛው አጋማሽ ተነጋግረን የገባነውን ነገር በተለይ ከኃላ ያሉ ልጆች ሊፈፅሙልኝ አልቻሉም”- ደለለኝ ደቻሳ (ወላይታ ድቻ)

ከተከታታይ ድል በኃላ ስለመሸነፋቸውና ስለጨዋታው

” ይህ እግር ኳስ ነው፤ በእግርኳስ መሰል ነገሮች ይከሰታሉ። በተከታታይ ማሸነፋችን ለጨዋታዎች ዋስትና አይሆንም። ይልቁን በየቀኑ በየጨዋታው የምስተራቸው ነገሮች ጨዋታዎችን ይወስናሉ። ጨዋታውን እንደጠበቅነው ነው ያገኘነው ፤ ይህ ሊገጥመን እንደሚችል አስበን ተዘጋጅተን ነበር የመጣነው። በመከላከሉ ረገድ ብዙ ስህተቶችን ስንሰራ ነበር፤ ይህም ዋጋ አስከፍሎናል።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስለመዳከማቸው

በመጀመሪያው አጋማሽ ቡና በራሱ አጨዋወት ነበር የገባው፤ ረጃጅም ኳሶችን ይጠቀማሉ ብለን አልገመትንም ነበር። እኛ ካገባን በኋላ ክፍት ቦታዎች ላይ ረጃጅም ኳሶችን መጠቀም ጀምረው ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ተነጋግረን የገባነውን ነገር በተለይ ከኋላ ያሉ ልጆች ሊፈፅሙልኝ አልቻሉም። በዚህም የእኛ ስህተቶች እነሱን አነሳስተዋል ብዬ አስባለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ