ሰባት የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ክፍያ እስኪፈፅሙ ታግደዋል

ሰባት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ለውድድር የሚያስፈልገውን ገንዘብ መክፈል ባለመቻላቸው ከዛሬ ጀምሮ ከፕሪምየር ሊጉ ታግደዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር አመት የመጀመሪያው ዙር ግምገማ ዛሬ በጁፒተር ሆቴል እየተደረገ ይገኛል፡፡ በግምገማ እና ውይይቱ በርካታ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊግ ካምፓኒ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በመጨረሻ የጉባዔው ማጠቃለያ ላይ ሰባት የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ከፕሪምየር ሊጉ መታገዳቸውን ለክለቦቹ ይፋ አድርገዋል፡፡

ክለቦቹ የታገዱበትን ምክንያት ሰብሳቢው ሲያስረዱ በፕሪምየር ሊጉ ለመወዳደር የሚያስፈልገውን የስምንት መቶ ሰባ ሺህ ብር ክፍያ እንዲከፍሉ በተደጋጋሚ በቃልም ሆነ በደብዳቤ ቢገለፅም ሰበታ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር፣ ሲዳማ ቡና፣ ወልዋሎ፣ ስሑል ሽረ እና ሀዲያ ሆሳዕና መፈፀም ባለመቻላቸው ይህን ክፍያ እስኪፈፅሙ ከሊጉ ጋር የተያያዘ ግልጋሎት (ዝውውር ማከናወን ጨምሮ) ማግኘትም ሆነ ውድድር ማከናወን እንደማይችሉ ተገልጿል።

በስብሰባው ላይ እንደተገለፀው አዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ በሙሉ ክፍያ የፈፀሙ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና፣ ወላይታ ድቻ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ፋሲል ከተማ እና ባህር ዳር ቢከፍሉም ቀሪ ክፍያቸውን በቀጣይ ቀናት መፈፀም እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

ይህ ክፍያ ለዳኞች እና ኮሚሽነሮች እንዲሁም ለውድድሩ ማስኬጃ መከፈል የሚገባው ክፍያ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ