ኢትዮጵያዊው ተጫዋች ለሙከራ ወደ ሩማንያ ያቀናል

ያለፉትን ሦስት ዓመታት በኬንያ ቆይታ አድርጎ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ኢትዮጵያዊው ተጫዋች አቤኔዘር ንጉሴ ለሙከራ ወደ ሩማንያ የሚያቀና ይሆናል።

የእግርኳስ መጫወትን በ24 ሜዳ የጀመረው አቤኔዘር ከዚህ ቀደም የደደቢት ተስፋ ቡድን አባል ያልነበረ ቢሆንም ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ ለወራት ሲዘጋጅ ቆይቶ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ተጫዋቾችን ከየሀገሩ በመመልመል ወደ ተለያዩ ሀገራት በሚልከው ኪቢቪሮሃ በተባለ ወኪል አማካኝነት በውጪ ሀገራት የመጫወት ህልሙን ለማሳካት ለሁለት ዓመት በኬንያ ለመቆየት ችሎ ነበር። ሆኖም ለጊዜው በጉዳት ባይሳካለትም አሁን ግን በሩማንያ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ለሚገኘው Csikszereda ክለብ የ15 ቀናት የሙከራ ጊዜ አግኝቶ ዛሬ ማምሻውን ወደ ቦታው ያቀናል።

የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው አቤኔዜር በጉዞው ሙከራው የተሳካ እንደሚሆን ያለውን እምነት ተናግሮ ሆኖም በአውሮፓ የዝውውር መስኮቱ በመዘጋቱ ሙከራው የተሳካ ቢሆን እንኳ ለጊዜው እንደማይፈርም እና በቀጣይ በሚከፈተው የዝውውር ሂደት ውስጥ እንደሚገባ ተናግሮ አንድ ቀን በሀገሩ ሊግ የመጫወት ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።

© ሶከር ኢትዮጵያ