መቐለ 70 እንደርታዎች የሦስት ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀቁ

መቐለ 70 እንደርታ ቀደም ብለው ወደ ቡድኑ የቀላቀላቸው አማካዮቹ ሙሳ ዳኦ እና ካሉሻ አልሀሰን እንዲሁም ተከላካዩ ተስፋዬ በቀለን የግሉ ማድረጉ ተረጋግጧል።

በክረምት የቅድመ ውድድር ዝግጅት ወቅት ወደ ቡድኑ ተቀላቅለው በተለያየ ምክንያት ከክለቡ ጋር ሳይፈራረሙ የተለያዩት ሁለቱ አማካዮች የቡድኑን ዋነኛ ችግር ይቀርፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቀድሞ ቡድኑን ተቀላቅሎ በወረቀት ስራዎች ምክንያት ዝውውሩ ሳይጠናቀቅ የቆየው የቡርኪና ፏሳዊ አማካይ የዝውውር ሂደቱ የተጠናቀቀ ሲሆን ለቋሚነትም ከዳንኤል ደምሴ ጋር ይፎካከራል።

ሌላው ቡድኑ የተቀላቀለው ተከላካዩ ተስፋዬ በቀለ ነው። ከቀናት በፊት ከቡድኑ ጋር ልምምድ የጀመረው ይህ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ እና አዳማ ከተማ ተጫዋች ወደ ቡድኑ የሚያደርገውን ዝውውር ማጠናቀቁን ተከትሎ ለሳሳው የቡድኑ ተከላካይ መስመር ጥሩ ግብዓት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ከመቐለ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ቀደም ብሎ የታዳጊ ቡድን ለማቋቋም የተጫዋቾች ምርጫ እና ሌሎች ስራዎች ሲሰራ የቆየው ክለቡ የታዳጊ ቡድኑን የማቋቋም ሒደቱን በመጨረስ ላይ ሲገኝ የትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን የታዳጊዎችን ሊግ ካቋቋመ በኋላም በሊጉ እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።

ከወራት በፊት የትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን ውቅሮ ላይ ባደርገው ስብሰባ የክልሉ የታዳጊዎች ሊግ ለማቋቋም መወሰኑ ይታወሳል።

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ