ሪፖርት | ፋሲል ከነማ አዳማን በማሸነፍ ሊጉን በጊዜያዊነት መምራት ጀምሯል

አንድ ጨዋታ በሜዳቸው እንዳይጫወቱ ቅጣት የተላለፈባቸው ፋሲል ከነማዎች አዳማ ከተማን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ጋብዘው 1-0 አሸንፈዋል።

ፋሲል ከነማዎች በአንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ከተረቱበት የሃዋሳ ከተማ ጨዋታ ሚካኤል ሳማኪ፣ ሰዒድ ሀሰን፣ ጅብሪል አህመድ እና ኢዙ አዙካን በ ቴዎድሮስ ጌትነት፣ እንየው ካሳሁን፣ ኪሩቤል ኃይሉ እና ዓ/ብርሀን ይግዛው በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል። 668 ኪሜ አቆራርጠው ባርህር ዳር የደረሱት አዳማዎች በበኩላቸው ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የዓመቱ አጋማሽ የመጨረሻ ጨዋታ ሱሌማን መሐመድ እና ዳዋ ሆቴሳን በቴዎድሮስ በቀለ እና ፉአድ ፈረጃ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በአዳማዎች የበላይነት የጀመረው ይህ ጨዋታ ገና በጅምሩ ያለቀለት የግብ ማግባት ሙከራ አስተናግዷል። በዚህም በረከት ደስታ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ አዳማዎች ከቅጣት ምት ሌላ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ በብልቻ ሹራ አማካኝነት አድርገው መክኖባቸዋል። በእነዚህ ሁለት ሙከራዎች ወደ ፋሲሎች የግብ ክልል መድረስ ያላቆሙት አዳማዎች በ9ኛው ደቂቃ በተገኘ የመዓዘን ምት በድጋሜ ወደ ግብ ቀርበው ነበር።

በተቀዛቀዘ ፍጥነት ጨዋታውን የጀመሩት ፋሲሎች ከ10ኛው ደቂቃ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል። በ11ኛው ደቂቃም አጥቂያቸው ሙጂብ ከግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘበትን ኳስ ከኪሩቤል ተቀብሎ ሳይጠቀምበት በቀረው እድል የአዳማዎችን ግብ መፈተሽ ጀምረዋል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ፋሲሎች በጥቂጥ ደቂቃ ውስጥ ያገኙትን የጨዋታ ብልጫ ወደ ጎልነት ቀይረዋል። በዚህ ደቂቃ አምሳሉ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ በዛብህ መለዮ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ ሆነዋል።

እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት አዳማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የቆሙ ኳሶችን እና የተከላካይ ጀርባ ሩጫዎችን በመጠቀም ግብ ለማግባት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ጨዋታው ቀጥሏል። በ19ኛው ደቂቃም ቡድኑ በረከት አሻምቶት ቴዎድሮስ በግንባሩ በሞከረው የግንባር ኳስ አቻ ለመሆን ጥሯል። ከደቂቃ በኋላም ብልቻ ከመስመር የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሯል። በተቀራኒው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የነበራቸው ፋሲሎች ጨዋታውን በማፍጠን እና በማቀዝቀዝ የሃይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው አድርገው ተንቀሳቀዋል። በተለይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሱራፌል መስመር ላይ በሚያደርጋቸው እንዲሁም ወደ መሃል እየገባ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ፋሲሎችን እጅግ ሲጠቅም ተስተውሏል።

አቻ ለመሆን ረጃጅም ኳሶችን አጠናክረው የቀጠሉት የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ተጨዋቾች በ24ኛ ደቂቃ በተሞከረ የከነዓን ማርክነህ ሙከራ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ገና በእዚህ አጋማሽ ሁለት የተጨዋች ለውጦችን ያደረጉት አዳማዎች የጨዋታ መንገዳቸውን በመለወጥ ጨዋታውን ማከናወን ቀጥለዋል። በተለይ ሱሌማንን ቀይሮ የገባው ተስፋዬ ነጋሽ በ32ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ ብቃት ወደ ግብነት ለመቀይር ጥሮ ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይም ሁለቱም ቡድኖች የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳይደርጉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ የግብ ሙከራዎችን ያላስተናገደው ይህ አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ለማስመልከት 10 ደቂቃዎች ወስደውበታል። በ55ኛው ደቂቃም ሀብታሙ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ሱራፌል ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂው ፔንዜ እንደምንም ይዞበታል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት አዳማዎች ከደቂቃ በኋላ ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ወስደው ሳይጠቀሙበት ተመልሰዋል።

እየተመሩ የሚገኙት አዳማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ፊት ተጠግተው ለማጥቃት ተጫውተዋል። በዚህም ቡልቻ በ65ኛ ደቂቃ ጥሩ የቅጣት ምት ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ አድኖበታል። ከዚህ በተጨማሪ በረከት በ70ኛው ደቂቃ ፍጥነቱን ተጠቅሞ መስመር በመስመር በመሮጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሮ በተመሳሳይ ቴዎድሮስ አምክኖበታል። በተቃራኒው ብልጫ የተወሰደባቸው ፋሲሎች በመጀመሪያው አጋማሽ በቁጥጥራቸው ስር የነበረው የጨዋታ የበላይነት ከእጃቸው ወጥቶ ታይቷል።

ፍሬያማ ባይሆኑም በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች የመጨረሻ እድላቸውን የሞከሩት አዳማዎች በ85ኛው ደቂቃ እጅግ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። በዚህ ደቂቃ በረጅሙ የተመታን ኳስ ያሬድ ባዬ በግንባሩ ለግብጠባቂው አቀብላለው ብሎ ወደ ኋላ የጨረፈው ኳስ ፈጣኑ የመስመር ተከላካይ ተስፋዬ ሮጦ በመድረስ የሞከረው ሙከራ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው የባከነ ደቂቃ ወርቃማ የግብ ማግባት እድል በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ያገኙት ፋሲሎች መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ የሚያደርጉበትን እድል ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በዚህ ደቂቃ ሙጂብ እና ማውሊ አንድ የአዳማ ተከላካይ ብቻ አግኝነተው ሙጂብ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች ነጥባቸውን ወደ 29 ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነትን ሲቆናጠጡ አዳማዎች ደግሞ ከነበሩት 9ኛ ደረጃ አንድ ደረጃን ተንሸራተው 10ኛ ደረጃን ይዘዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ