አራት ተጫዋቾች ድጋፍ አድርገዋል

ክብሮም ብርሀነ እና ክፍሎም ሐጎስ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ሰይድ ሐሰን እና ካርሎስ ዳምጠው ለሁለተኛ ግዜ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ አድርገዋል።

የእግር ኳስ ቤተሰቡ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ እና በወረርሺኙ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የንፅህና መጠበቂያ እና ተያያዥ ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል። አሁን ደግሞ የስሑል ሽረዎቹ ክብሮም ብርሀነ እና ሰይድ ሐሰን፣ የደደቢቱ ክፍሎም ሐጎስ እና ከሳምንታት በፊት ድጋፍ አድርጎ የነበረው ካርሎስ ዳምጠው የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል። ሰይድ ሐሰን በትውልድ ከተማው ሰለክለካ የሚገኙ አስራ ሁለት አባወራዎች ድጋፍ ሲያደርግ ድጋፉም ከከተማው የሚመለከታቸው አካላት በመተባበር እንዳከናወነው ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በፊትም ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው ይህ አጥቂ ስሑል ሽረዎች ወደ ከፍተኛ ሊግ እና ፕሪምየር ሊግ ሲያድጉ ወሳኝ ሚና እንደነበረው ይታወቃል። ሌላው ለሁለተኛ ግዜ ድጋፍ ያደረገው ካርሎስ ዳምጠው ነው። ከሳምንታት በፊት ለሜሪ ጆይ ድጋፍ ያደረገው ተጫዋቹ ለበርካታ አቅመ ደካሞች ድጋፍ ሲያደርግ በአንድ አከባቢም ሕብረተሰቡ እጁን የሚታጠብበት ታንከር አስቀምጧል። ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት ደግሞ የስሑል ሽረው ተከላካይ ክብሮም ብርሀነ እና የደደቢቱ አማካይ ክፍሎም ሐጎስ ናቸው።

ከዚህ በፊት በቁጥር በርካታ የሆኑ ተጫዋቾች ለወረርሺኙ መከላከያ ድጋፍ ማድረጋቸው የሚያታወስ ሲሆን በክለብ ደረጃም ድጋፎች መደረግ ጀምረዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ