የደጋፊዎች ገጽ | ክለባቸውን ብለው የሚወዱትን መለያ ለብሰው ላይመለሱ በዛው የቀሩ የልብ ደጋፊዎች

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ እስከ ዛሬ ድርስ ባለው የሰማንያ ዓመት ጊዜ ውስጥ በደጋፊዎች ላይ የደረሱ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል። በዛሬው የደጋፊዎች ገፅ በተለያዩ ክለቦች ደጋፊዎች ላይ የደረሱ አሳዛኝ የሞት ገጠመኞችን እናነሳለን።

ጥቁር ቀን! ሀብታሙ ቪቫ ሳንጃው (የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ)

ጊዜው ሰኔ 29 ቀን 2005 ነበር። ደደቢት የውድድር ዓመቱ ቻምፒዮን መሆኑን ቀደም ብሎ ቢያረጋግጥም ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን የመርሐ ግብር ማሟያውን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሀዋሳ አቅንቷል። ፈረሰኞቹ ቢሸነፉም ቢያሸንፉም ቀደም ተብሎ ቻምፒዮኑ ስለታወቀ ምንም የሚያመጣው ለውጥ ባይኖርም የክብር ጉዳይ ነውና አምስት ወጣቶች ክለባቸውን ብለው ወደ ሀዋሳ መሄድ ምርጫቸው አርገው ተነሱ፡፡ ነገር ግን ሀዋሳ ሳይደርሱ በየሳምንቱ የሚናፍቁት መለያውን ለማየት ሳይታደሉ የመኪና አደጋ አጋጠማቸው፡፡ በጉዞው ላይ ከነበሩት ከአምስቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተሰቦች ሁለቱ ብርሀን ኃይለሥላሴ እና አብዱልከሪም ደምስስ በህይወት ሲተርፉ መሀሪ እስጢፋኖስ ፣ ሲሳይ ንጉሱ (ቤቢ) እና ዘላዓለም አንዱዓለም ላይመለሱ ዳግመኛም የሚወዱትን ክለብ አርማ ላይለብሱ በድሉ ጊዜ በካምቦሎጆ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጋር አብረው ላይዘምሩና ላይጨፍሩ እስከ ወዲያኛው አሸለቡ፡፡ ‘እስከ ሞት ነው ኪዳኔ’ ብለው ዘምረው ለቃላቸው የታመኑ የእውነተኛ ደጋፊ ተምሳሌቶች ናቸው። በዚህ ጉዞ ውስጥ አብረው ከነበሩ እና ከአደጋው በህይወት ከተረፉት አንዱ የሆነው አብዱልከሪም ደምስስ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይናገራል።

“አመሻሽ አንድ ሰዓት አካባቢ ነው። ከምኖርበት ሳሪስ አቦ ሰፈር ደውለውልኝ ወደ ሀዋሳ ጉዞ ጀመርን። በመሐል ላይ ለእራት ዝዋይ አርፈን ጉዞ ቀጠለ። ይገርምሀል የምቀመጥበትን የወንበር ቦታ ሁለቴ ቀይሬ በሦስተኛው ከኃላው ባለው መሐል ወንበር ነበር የተቀመጥኩት። ለውሃ ሽንት ወርደን አስር ደቂቃ እንደተጓዝን ይመስለኛል። ቁራኔን ቀርቼ ሰውነቴን አብሼ እንቅልፍ ወሰደኝ። ነቅቼ አይኔን ስገልጥ ሹፌሩ ደም ሲተፋ አየሁ ፤ ይህ ማለት ዘለዓለም ነው። ከዘለዓለም አጠገብ የነበረው መሐሪ ደግሞ አይኑ ላይ አንቴና የመሰለ ሽቦ ገብቶ አይቻለው። ከዚህ በኃላ የማቀው ምንም ነገር የለም። ለብዙ ጊዜ ሆስፒታል ገብቼ ተኝቼ ነበር። ሆስፒታል ሆኜ እናቴን ሁልጊዜ ‘ጓደኞቼ የት አሉ ?’ብዬ ስጠይቃት ‘ኧረ አሉ አጠገብህ ናቸው’ ትለኛለች። አንድ ቀን ጓደኛዬ ያሬድ ሊጠይቀኝ ሲመጣ ‘ነፍሳችሁን በገነት ያኑራት’ የሚል ቲሸርት ለብሶ አየሁት። የተፃፈውን ላረጋግጥ ቀና ስል ያሬድ እንዳላየው ብሎ ወድያውኑ ሮጦ ወጣ። ‘የት ሄደ ?’ ብዬ ስጠይቅ ‘ይመጣል’ አሉኝ። እንደ አጋጣሚ ራጅ ልነሳ ስሄድ አንዷ ዶክተር ታማ ነበር እና ‘እንዴ ዶክተር ይታመማል እንዴ ? ‘ ብዬ ስጠይቃት ‘አዎ’ አለችኝ እና ‘አንተ ምን ሆነህ ነው ?’ ስትለኝ ‘ሀዋሳ በመኪና አደጋ’ ስላት ገና ከአፌ ሳልጨርስ ‘ሦስቱ ሞተው ሁለቱ በተረፉበት አደጋ የተረፍከው ልጅ ነህ ?’ ስትለኝ መቆም አቃተኝ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ እስከዚህ ጊዜ ድረስ መሞታቸውን አላቅም ነበር። በጣም አዘንኩኝ ስታዲየም ሆኜ ጨዋታ በምመለከትበት ወቅት ሁሌም አስባቸዋለው። በፊት ከላይ ነበር የማየው አሁን ቦታ ሁሉ ቀይሬ እታች ነው የምቀመጠው ፤ በማንኛውም ሰዓት ስለማስታውሳቸው እንዳልረበሽ። ሁሌም ሰኔ 29 ሲመጣ የመሐሪ እናት እኔን ማየት ይፈልጋሉ። እኔን ሲያየ በህይወት ያሉ ስለሚመስላቸው ሁሌም እንሄዳለን ዘንድሮ ባለው ሁኔታ የተነሳ አንሄድም እንጂ።”

“የኢትዮጵያ እግርኳስ ህይወት ተከፍሎለታል” በክፍሌ ወልዴ የተዘጋጀ

በኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያው ሞት የተስተናገደው በአዳማ በተደረገው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ላይ ያሉ ደጋፊዎች የመኪና መገልበጥ አደጋ አጋጣሟቸው ስለክለብ ፍቅር ሞትን ሲቀበሉ ነበር። የዛሬው ዋናው ጉዳዬ ግን ከሞትም በላይ ሞት አለ ወይ የሚያስብለው በቀጣይ የምገልፀው ታሪክ ነው። መቼም ቢሆን በቡና ታሪክ ውስጥ የማይዘነጋው ሟች እንጂ ገዳይ ያልታወቀበት ስለክለብ ፍቅር ተብሎ ተወጥቶ ፤ በአንድ ክለብ አርማ በአንድ ክለብ ዜማ ተቀኝቶ ፤ እናት እና አባትን ተሰናብቶ ወዳጅ ቤተሰብ በሠላም ያገናኘን ተብሎ በወጡበት መቅረት ተራምደው በኩራት የሚወዱትን ክለብ መለያ ለብሰው መመለሻው ግን በአስክሬን ሳጥን ከላይ ተጭኖ ሲሆን ልብን በሀዘን ያደማል። ዘነበ አራት ኪሎ የተወለደ በኋለም በግቢ ገብርኤልና አካባቢው የኖረ የቡና ደጋፊ ነው። በአሁኑ አጠራራችን ንጋት ኮከብ በቀድሞው ዳፍ አካባቢ በካታንጋ ስድስት ቁጥር በር ጠርዝና አምስት ቁጥር የስታዲየም መቀመጫ የኢትዮጵያ ቡናን አርማ ለብሶ የአሮጌው ቄራ ፣ የአራት ኪሎ ፣ የአዋሬ ልጆችን በሳቅ እያዋዛ ስለቡና እያዘመረ የኖረ አስራ ሁለት ቁጥር ለባሽ የልብ ደጋፊ ነው።

ዘነበ በላይ ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ያደረጉትን ጨዋታ ለመመልከት ከአዲስ አበባ ሲነሳ በሰላም ቤተሰቡን ተሰናብቶ ከቡና ቤተሰቡ ጋር ሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ጨዋታው ከተመለከተ በኃላ እዛው ሀዋሳ እንደሚያድር ነግሮን ተለያየን። ዘነበ ትንሽ አመም ያደርገው ነበረና ወደ መኝታው እንዲገባ ያደረጉት የኛው ደጋፊዎች ነበሩ። ነገር ግን ደጋፊዎች በማግስቱ ሲመለሱ ዘነበ በዛው ቀረ ፤ ቀናቶችም ተቆጠሩ። ካዛንቺዝ እና አራትኪሎ የዘነበ ቤተሰቦች ዘንድም ‘ዘነበ የት ገባ ?ምንስ ዋጠው?’ የሚለው ጥያቄ እየጨመረ መጣ።

የክልሉ ወረዳ ፖሊስም የዘነበ ስልክ መወሰዱ አሟሟቱም ከድብደባ ጋር የተያያዘ እንደሆነ እና በጊዜውም በኪሱ የመታወቂያ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ አስክሬኑን መቅበራቸውን ነገሩን። ለ25 ቀናት በመቃብር ውስጥ ያለውን አስክሬን ማን ያውጣው ? መቼም የማልረሳው ቡናዊ በመሆኔ የምኮራበት የቡናማ እና ሀዘናቹ ሀዘናችን ነው ያሉ በሐዋሳ ያሉ የቡና ደጋፊዎች እንዲሁም የሐዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በመሆን አስክሬኑን አውጥተን ወደ አዲስ አበባ ተመለስን።

ብዙዎች አነቡ። ዘነበ በላይ ሞቱ እንጂ አሟሟቱ ሳይታወቅ በቀጨኔ መድሐኒዓለም ቤተክርስቲያን የቀብር ሥነ ስርዓቱ ተፈፀመ። የተለያዩ ክለብ ደጋፊዎችም በዘነበ ሞት ሀዘናቸውን ገለፁ። የሐዋሳ ፖሊስም ሆነ የደቡብ ክልል ፖሊስ እስካሁን የዘነበን ገዳዮች ሳይገልፁ መላው ቤተሰብ እና የቡና ደጋፊ በዘነበ ሞት ሲብሰለሰሉ ይኖራሉ። ይህ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ለቡናማው መለያና ክብር የተከፈለ የህይወት መስዋዕትነት ነው። ለወደዱት ለታመኑለት መለያ ክብር ወጥቶ መቅረት የዕድሜ ባለፀጋ እናት እና አባትን እህህ እንዳሉ ማስቀረት፤ ዘኔ ሁሌም በህይወት እስካለን አንረሳህም። ሞት ያንተን ህይወት ለተራ ሌብነት ብለው ለነጠቁ !!

ፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በመኪና አደጋ ህይወታቸው ያለፈበት አጋጣሚ

ዕለቱ ጥር 05 2011 ነው። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ባህር ዳር ከነማ ከፋሲል ከነማ ያደረጉትን ጨዋታ ባህርዳር ላይ ታድመው የሚወዱትን ክለባቸውን ደግፈው ወደ ጎንደር ሲመለሱ በተፈጠረው የመኪና አደጋ በርካታ ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸው የሚታወስ ነው። በዚህ ከፍተኛ አደጋ ሁለት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ህይወታቸው ማለፉ ሌላኛው አሳዛኝ አጋጣሚ ነበር ። ህይወታቸው ያለፉት ወጣቶች ካህሌ ታደሰ እና ፈንታሁን ኪዴ ይባላሉ። የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች እና የቡድኑ አባላት ወደ ጎንደር በሚመለሱበት ወቅት አደጋው የደረሰበት ቦታ ላይ ወርደው ሀዘናቸውን መግለፃቸው የሚታወስ ነው። የወጣቶቹ የቀብር ሥነ ስርዓት ካህሌ ታደሰ በጎንደር ገብርኤል ቤተክርስቲያን ፈንታሁን ኪዴ በአድርቃይ ከተማ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች እና ደጋፊዎች በተገኙበት በክብር ተፈፅሟል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም በመኪና አደጋ ህወታቸውን ላጡት ቤተሰቦች ፋሲል ከነማ ከስሑል ሽረ በዳረጉት የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አማካኝነት ለእያንዳንዳቸው ቤተሰቦች የ50 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።

“በጣም ነው ያዘንነው ልባችን ተነክቷል” ጋሻው አስማረ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝደንት

” ማስታወስ የማትፈልገው ከአዕምሮ እንዲጠፋ የምትፈልገው ነገር አለ አይደል ? ያ ስሜት ነው የሚሰማኝ ፤ አሁንም ሀዘን ነው የሚሰማን። ባለፈው ቀኑን አስታውሰነው አስበናቸዋል። ሁሌም ስናስባቸው እንኖራለን። ሁኔታውም እንድትረሳቸውም አያደርገህም። በጣም ነው የሚያሳዝኑት ፤ በተለይ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ስትመለከት። ይልቁንም አንደኛው ቤተሰቦቹን የሚረዳ እና ልጅ ያለው ነበር። ይህንን ስታውቅ ደግሞ የበለጠ ፀፀት ይሰማሀል።”

የሀላባ ከነማ ደጋፊዎች ሕልፈት

በ2007 ነሐሴ ወር ላይ ነው። በቀድሞ አጠራሩ የብሔራዊ ሊግ የማጠቃልያ ውድድር ድሬደዋ ከተማ ላይ ይካሄድ ነበር። ሀላባ ከተማ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ ወሳኝ ጨዋታ በግማሽ ፍፃሜው ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያደርጋል። ይህን ጨዋታ ለመከታተል እና ቡድናቸውን ለመደገፍ ከ30 በላይ ሰዎችን የመጫን አቅም ባለው የህዝብ ማመላለሻ የሀላባ ደጋፊዎች ጉዞ ወደ ድሬደዋ ጀመሩ። መተሐራን እንዳለፉ የሚጓዙበት መኪና ተገልብጦ ብዙዎች ለከፋ አደጋ ሲዳረጉ አምስት ደጋፊዎች ህይወታቸው ያለፈበት ጊዜ ሌላኛው አሳዛኝ የደጋፊዎች ሞት ነበር።

“እጅግ ከባድ ነበር ጨዋታውንም ማድረግ አልነበረብንም” የሀላባ ከተማ ቡድን መሪ አቶ አፈወርቅ ታምራት

“በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው ያጋጠመን። እንደምታቀው ጨዋታው ባልተለመደ ሁኔታ ጠዋት አራት ሰዓት ስለነበረ በሌሊት እና በዝናብ አስቸጋሪ መንገድ ሲጓዙ ነው ይህ አደጋ ያጋጠማቸው። ይህን ስንሰማ በጣም ነው የደነገጥነው። እኛ ቡድን ውስጥ የተጎዱባቸው ተጫዋቾች ስለነበሩ ይህን ሲሰሙ ተደናግጠው ተረብሸው ስለነበር ጨዋታውን ማድረግ አልነበረብንም ፤ ያው ህግ ስለሆነ ተጫውተናል። አሸንፈን መታሰቢያነቱን ለእነርሱ ለማድረግ ነበር አልተሳካም። የድሬደዋ ህዝብ ድንኳን ጥሎ አብሮን አዝኗል። ክለባቸውን ለማየት ወጥተው በዛው መቅረታቸው ሁሌም ይታወሳል።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ