ሰለሞን ገብረመድኅን የት ይገኛል ?

ባለፉት ዓመታት ከታዩ ጥቂት ባለክህሎት አማካዮች አንዱ የነበረውና ለአንድ ዓመት ከእግርኳስ የራቀው ሰለሞን ገብረመድኅን የት ይገኛል?

በሚሌኒየሙ መጀመርያ ብቅ ካሉ ምርጥ አማካዮች አንዱ ነው። የእግር ኳስ ሂወቱ በተወለደበት ከተማ መተሀራ መርቲ ለሚገኘው መተሀራ ስኳር እግርኳስን መጫወት ጀምሮ ድንቅ ጊዜያት ካሳለፈ በኋላ በመቀጠል በሰበታ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ንግድ ባንክ፣ ፋሲል ከነማ፣ ወልዲያ እና ስሑል ሽረ ተጫውቷል። ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው በተለያዩ ምክንያቶች እንደ አቅማቸው የሚፈለገውን ያህል ደረጃ ካልደረሱ አማካዮች አንዱ ነው።

ከፋሲል ከነማ ጋር ከተለያየ በኃላ የተረጋጋ የእግር ኳስ ጊዜ ያልነበረው ሰለሞን ምንም እንኳ በወልዲያ እና ስሑል ሽረ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ገደማ ቢጫወትም እንደተጠበቀው የተሳካ ጊዜያት አላሳለፈም። ባላፈው ዓመት አጋማሽ ከስሑል ሽረ ጋር ተለያይቶ ከእግር ኳስ ርቆ ያለው ይህ አማካይ ስለ ወቅታዊ ሁኔታው እና ተያያዥ ጉዳዮች ያደረገው አጭር ቆይታ እነሆ።

አሁን ስላለበት ሁኔታ

በዚ ወቅት በግሌ መደበኛ ልምምድ በመስራት እና አንዳንድ የግል ስራዎች በመስራት ላይ ነው የምገኘው። በሁሉም ረገድ ዝግጁ ነኝ ፤ ጤንነቴም ወደ ቀድሞው ተመልሷል። እግዚአብሔር ፈቅዶ ይህ በሽታ ሲጠፋና እግር ኳሱ ሲመለስ እኔም በጥሩ ብቃት ወደ ክለብ እግር ኳስ እመለሳለው። ለዚህም በቂ ዝግጅት እያደረግኩ ነው። ከጉዳት ሙሉ ለሙሉ አገግሜያለው። ሁኔታዎች ሲመቻቹ ወደ እግርኳስ እመለሳለሁ።

ከእግርኳስ የራቀበት ምክንያት

ከስሑል ሽረ ጋር በጉዳት ምክንያት ከተለያየው በኃላ ከጉዳቴ በደንብ ለማገገም ነው ላለፉት ጊዜያት ከእግር ኳሱ የራቅኩት። ጉዳቴ የታፋ መሰንጠቅ ነበር። የህክምና ክትትል ያስፈልገው ስለነበር ነው፤ በዚ ሰዓት ደግሞ ከጉዳት ሙሉ ለሙሉ ነፃ ነኝ እና ለትንሽ ጊዜያት የራቅኩበት ምክንያት ከጉዳቴ ሙሉ ለሙሉ ለማገገም ነው።

ስለ ንግድ ባንክ፣ ሰበታ እና ፋሲል ጥሩ ቆይታዎቹ

የሰበታ ቆይታዬ አሪፍ ነበር ብዙ ልምድ የወሰድኩበት ወቅት ነበር። ከነ ሙሉዓለም ረጋሳ፣ ዳዊት መብራቱ እና ቢንያም አሰፋ የመሳሰሉ ምርጥ ተጫዋቾች ተጫውቻለው በክለቡ ቆይታዬ። ባንክም አሪፍ ቆይታ ነበረኝ። በእግር ኳስ ሕይወቴ በጣም ምርጡ ጊዜዬ ባንክ እና ሰበታ የነበረኝ ቆይታ ነው። ከዛ በኃላ ፋሲል ከነማ ፣ ወልዲያ እና ስሑል ሽረ ነው የተጫወትኩት። በአጠቃላይ በፈለግኩት ደረጃ እግር ኳስ አልተጫወትኩም። ምክንያቱ ብዙ ነው፤ በቀጣይ በሰፊው እመለስበታለው። አሁን ማለት የምችለው ግን በእግርኳሳችን ኳስ ይዘው ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ምቹ ሁኔታ የለም።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ