በዛሬው ውይይት ስለሴቶች ውድድር ምንም አለመባሉ አስገራሚ ሆኗል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውድድሮች የሚጀመሩበትን መነሻ ሰነድ ለክለብ ተወካዮች አቅርቦ ውይይት መደረጉ ይታወቃል። ነገር ግን በውይይቱ ላይ ስለሴቶች ውድድር ሃሳቦች አለመነሳታቸው አግራሞትን ፈጥሯል።

በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የወንዶች እንዲሁም የሴቶች 1ኛ እና 2ኛ የሊግ እርከን ላይ የሚወዳደሩ ክለቦችን በካፍ የልህቀት ማዕከል ሰብስቦ ውድድሮች የሚጀመሩበትን የመነሻ ሰነድ ማቅረቡ ይታወቃል። ሰነዱ ከቀረበ በኋላም በጉዳዩ ዙርያ ገንቢ ሃሳቦች ከክለብ ተወካዮች ሲሰነዘር ቆይቷል። ይሁን እና በመርሃግብሩ ላይ እንዲሳተፉ የተደረጉት ነገርግን ስለእነሱ ውድድር በመድረኩ ምንም ሃሳብ ያልተሰነዘረላቸው የሴቶች ክለብ ተወካዮች በሁኔታው ግራ መጋባታቸውን ታዝበናል።

እንደ ዋናው የወንዶች ሊግ በስፍራው እንዲገኙ ጥሪ ቀርቦላቸው የነበረው የሴቶች ክለብ ተወካዮች መርሃግብሩን ወንዶች ሊግ ተወካዮች ጋር በመሆን እንዲከታተሉ ቢደረግም ከመድረኩ እነርሱን የሚመለከት ሃሳብ ሲሰነዘር አልተስተዋለም። በዚህም በስፍራው የተገኙ የክለቦቹ ተወካዮችም ሃሳብ እንደገባቸው ሲገልፁ አስተውለናል። በተለይ ተወካዮቹ ከወንዶች ፕሪምየር ሊግ አ/ማ ጋር ተደባልቀው ውይይት እንዲያደርጉ መደረጉ እና አክሲዮን ማኅበሩ ደግሞ ስለሴቶች ውድድር እንደማይመለከተው መግለፁ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጎታል። እነሱን አግላይ አቅጣጫ በመድረኩ ሲሰነዘር መቆየቱን ተከትሎም በስፍራው የተገኙ የሴቶች ክለብ ተወካዮች ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ለብቻቸው ውይይቶችን ሲያደርጉ ታይቷል። በውይይታቸውም ወቅት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ተገኝተው እነሱን የሚያገል ሰነድ እንዳልተዘጋጀ እና ሰነዱ እነርሱንም እንደሚያቅፍ ጠቁመዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም የሴቶችን ውድድሮች የሚመሩ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ አባላት ሴቶችም ውድድሮችን ለማከናወን የሚያስችላቸውን ቅድመ ሥራዎች እንዲከውኑ ገልፀዋል። በተጨማሪም ፌደሬሽኑ የሴቶችን ውድድር ለማስቀጠል ከካፍ እና ፊፋ እንዲሁም ከመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ