ከመከላከያ ጋር አወዛጋቢ ዓመት ያሳለፈው ዓለምነህ ግርማ በምን ሁኔታ ይገኛል ?

በግራ መስመር ተከላካይነት ጥሩ የማጥቃት ባህሪ ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው። ከመስመር የሚያሻግራቸው የተሳኩ ክሮሶች እና በማጥቃት ላይ በተመሰረተው አጨዋወቱ ብዙዎች ያውቁታል። በእግር ኳስ ሕይወቱ ለባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ንግድ ባንክ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ እና መከላከያ የተጫወተው ይህ ተጫዋች በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ከክለቡ መከላከያ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ መነጋገርያ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል።

ተጫዋቹ በዋነኝነት ከመከላከያ ጋር ከነበረው አስቸጋሪ ዓመት በኃላ አሁን ስላለበት ሁኔታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ስለ እግርኳስ ሕይወቱ

እግር ኳስ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሰፈር ነው የጀመርኩት። ከዛ በኃላ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ከተማ፣ ኤሌክትሪክ፣ ንግድ ባንክ ፣ መቐለ፣ ወልዋሎ እና መከላከያ ተጫውቻለው። በአብዛኞቹ የተጫወትኩባቸው ክለቦች ጥሩ ቆይታ ነበረኝ። ባህር ዳር ዩንቨርስቲ ጥሩ ቆይታ ነበረኝ። በግልም ጥሩ ብቃት ላይ ነበርኩ። ከዛ በኃላም በአዳማ ጥሩ ቆይታ ነበረኝ ብዙ ልምድ ያገኘሁበት ክለብ ነው። ከዛ በኃላ በነበሩት ክለቦችም ጥሩ ነበርኩ፤ በተለይም ከወልዋሎ ጋር ምርጥ ቆይታ ነበረኝ። ቡድኑ ላለመውረድ ሲጫወት ሙሉ ጨዋታዎች ተሰልፌ ተጫውቻለው በጣም አሪፍ የቡድን መንፈስ ነበረ ክለቡ ላይ። ከዛ በኃላ ግን በአስገዳጅ የቤተሰብ ጉዳይ ክለቡን ለቅቄ ለመከላከያ ፈረምኩ።

ከወልዋሎ ጋር ስለተለያየበት ያልተጠበቀ ውሳኔ

ከወልዋሎ ጋር በጣም አሪፍ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ጥሩ ብቃት ላይ ነበርኩ ቡድኑም በጣም አሪፍ ቡድን ነበር። የተለያየሁበት ምክንያት ግን በቤተሰብ ችግር ነው። ባለቤቴ ነፍሰ-ጡር ነበረች፤ የኔም የሚስቴም እናት በአገር ውስጥ አልነበሩም። በዛ ምክንያት ከሷ ጎን መሆን ስለነበረብኝ የግድ በአዲስ አበባ መሆን ነበረብኝ። በዛ ምክንያት ነው ወልዋሎን የለቀቅኩት እንጂ ከወልዋሎ ጋር ለዓመታት መጫወት እመኝ ነበር ፤ የሚገርም ክለብ ነው በጣም ጥሩ ቆይታ ነበረኝ። ህፃናት እና እናቶች ሳይቀሩ መጥተው ይደግፉን ነበር። በክለቡ የነበረኝ ቆይታ መቼም አልረሳውም።

አነጋጋሪ ስለነበረው የመከላከያ ቆይታው እና ስለተፈጠሩት ነገሮች

በቤተሰብ ችግር ወልዋሎን ለቅቄ መከላከያ ከተቀላቀልኩ በኃላ በመከላከያ የመጀመርያው ዓመቴ ጥሩ ቆይታ ነበረኝ ስለ ሁለተኛው ዓመት ጉዳይ ግን በእኔና በፈጣሪ ብቻ ይቆይ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። ጊዜው ሲደርስ ነገሮቹን ይፈ አደርጋለው። በልምምድ ሜዳ ጠንክሬ እየሰራሁ ነበር በክለቡ የተደረገልኝ ነገር ግን ለእኔ የሚመጥን አልነበረም። ከክለቡ ጋር ውል ስለነበረኝ አምኖ ላስፈረመኝ ክለብ ታማኝ ነበርኩ። ግን ምንም እድል ሳይሰጠኝ ክለቡ አቋምህ ወርዷል ብሎ ማስጠንቀቅያ ሰጠኝ። ምንም አቋሜ ሳይታይ ማስጠንቀቅያ መስጠታቸው ሳያንስ ለልምምድ እንኳ አንድ ማልያ ነበር የተሰጠኝ። ቡድኑ ልምምድ እየሰራ እኔ ሜዳውን እንድዞር ነበር የሚደረገው። ይህ ሁሉ ሲፈጠር ግን እኔ የማስበው አስር ደቂቃ እንኳ ዕድል ተሰጥቶች አቅሜን ለማሳየት ነበር። መከላከያ በጣም ትልቅ አንጋፋ ክለብ ነው፤ በጣም ነው የምወደው። የተደረገልኝ ነገር ለመግለፅ ግን ቃላት የለኝም፤ ለኔ አይመጥንም። ክለቡም ትልቅ ስለሆነ አንድ ቀን ቀን ይወጣልኛል ብዬ ጠንክሬ ስሰራ ነበር። ከስብስብ ውጭ ለምን ሆንኩ ብዬ ምንም ቅሬታ አላቀረብኩም እስከ መጨረሻው ሰዓት ከቡድኑ ጎን ነበርኩ። በልምምድ አለምዬ ሜዳ ዙር ስባል እዞራለው፤ ቁጭ በል ስባልም ቁጭ እላለሁ። በክለቡ የታየሁበት አንግል ግን በጣም ያሳዝናል። በስርዓት ልምምድ እንድሰራ ሳይፈቀድልኝ በአቋም መውረድ ማስጠንቀቅያ ሲደርሰኝም በጣም ነው ያዘንኩት። በብቃት ምክንያት ቢሆን ምንም አልነበርም የሆነው ሁሉ ግን አይገባኝም።

ስለ ወቅታዊ ሁኔታው

አሁን ከዛ ሁሉ ነገር በኃላ በጣም ጥሩ ነው ያለሁት። ፈጣሪ ይመስገን በስነ ልቦና ይሁን በአካል ብቃት ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለሁት። ምንም እንኳ በወረርሺኙ ምክንያት የስፖርት እንቅስቃሴዎች ቢቆሙም በግል ልምምድ እየሰራሁ ለቀጣይ ክለቤ ጥሩ ዝግጅት እያደረግኩ ነው።

በመጨረሻ ..

በመጨረሻ በእግር ኳስ ሕይወቴ ላገዙኝ፤ ከጎኔ ለተጫወቱ የቡድን ጓደኞቼ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። በተለይም በአዳማ ቆይታዬ ላገዙኝ ለጋሽ ግርማ እና ለፕሬዝዳንቱ ዓለማየሁ ቱሉ ፤ በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታዬ ለልባርጋቸው ምህረቱ እና ለተኽለ እያሱ እንዲሁም ለወልዋሎው ቡድን መሪ ማሩ ገብረፃዲቅ ምስጋና ላቀርብ እፈልጋለሁ። ለእግርኳሱ ፍቅር ያላቸው ለተጫዋች ወግነው የሚከራከሩ ሰዎች ናቸው። ከዛ በተጨማሪም በሁሉም ክለቦች ለደገፉኝ ደጋፊዎች ማመስገን እፈልጋለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ