ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ሲሳይ ቶሌ የት ይገኛል ?

በቅርብ ዓመታት ከታዩ ባለተሰጥኦ የግራ እግር ተጫዋቾች አንዱ በመሆን በተለያዩ ክለቦች ያለፉትን ስድስት ዓመታት በጥሩ ብቃት ተጫውቷል። በሒደት በእግርኳሱ ደምቀው ይታያሉ ተብለው ከተገመቱ ተጫዋቾች አንዱም ነበር። ሆኖም በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጪያዊ ችግሮች ምክንያት በታሰበው ልክ ዕድገቱ የተጠበቀውን ያህል ሳይሆን ቀርቷል። በኢትዮጵያ መድን ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ አዳማ ከተማ ፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ተጫውቷል። ያለፈውን አንድ ዓመት ከሜዳ የራቀው ሲሳይ ቶሌ ስላሳለፈው አስቸጋሪ የእግርኳስ ህይወት እና አሁን ስላለበት ሁኔታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
የእግርኳስ መነሻህ እንዴት ነው ?

እግርኳስ መጫወት የጀመርኩት በተወለድኩበት አካባቢ በሠፈሬ አቃቂ በቅርብ ርቀት ለሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በመጫወት ነው። ከታችኛው ታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በመድን ቤት መጫወት ችያለው። በዋናው ቡድን አንድ ዓመት ቆይቼ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ጥሪ ወደ ንግድ ባንክ አምርቻለው።

እስካሁን በአምስት ክለቦች የመጫወት ዕድል አግኝተሀል ፤ ጥሩ የእግርኳስ ዓመት ያሳለፍከው በየትኛው ክለብ ነው ?

አዳማ እያለው ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ። በተለይ ግን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነበረኝ የሁለት ዓመት ቆይታ በጣም ጥሩ ነበር። እኔ ማን እንደሆንኩ እና ምን ዓይነት አቅም እንዳለኝ አሳይቼያለው። ንግድ ባንክ ከመፍረሱ በፊት ነበር በጥሩ ዝውውር ወደ አዳማ ለማምራት የቻልኩት።

የእግርኳስ ዕድገትህ አጭር ቢሆንም እንደ አለህ አምቅም እና ችሎታ መድረስ የሚገባኝ ቦታ ደርሻለው ትላለህ ?

ኧረ በጭራሽ! የሚገባኝ ቦታ አልደረስኩም። በ2006 ነው በትልቅ ደረጃ መጫወት የጀመርኩት እንደ አነሳሳሴ በተለይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዳሳየሁት መልካም እንቅስቃሴ አሁን ያለሁበት በሚገባኝ ደረጃ አይደለም።

ምንድነው ምክንያቱ ትላለህ ?

ምክንያቱ የሚወጡ ስሞች አሉ። ‘እከሌ እንዲህ ነው’ የሚሉ አላስፈላጊ ስሞች ይወጡልሀል። ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር ሳትግባባ ስትቆይ ሌላ ስም ይሰጡሀል። ለእኔም ይሄ ስም ተሰጥቶኝ ሳላስበው ሌላ ነገር ውስጥ ገባሁኝ እንጂ እንደነበረኝ ችሎታ አልተጫወትኩም። የመጫወት አቅሙም አለኝ።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ብዙ ጊዜ ከሜዳ ውጪ ያሉ ግለ ባህሪዎች ፣ ለሚዲያ የማይመጥኑ መጠላለፎች አሉ። ይህ ምክንያት ሜዳ ውስጥ የተጫዋቾችን ዕድገት እየጎተተው ይገኛል። በዚህ ረገድ እኔ ተጎጂ ነኝ ትላለህ ?

በጣም ! ቅድም እንደገለፅኩልህ በጣም በተረጋጋ ሁኔታ ያለኝን አቅም አውጥቼ በንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ እየተጫወትኩኝ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ ከገባው በኋላ ነገሮች ሳላስባቸው ቀስ በቀስ እየተበላሹ መጡ። ወልቂጤም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲገባ ከቡድኑ አባላት አንዱ ነበርኩኝ። ሆኖም በአንድ ነገር አለመስማማት ቁጭ ብዬ ነበር። ብቻ ብዙ መጥቀስ ቢቻልም አላስፈላጊ ስለሆኑ እንለፋቸው።

በክህሎታቸው የተሻሉ ተጫዋቾች ከአሰልጣኞች የአጨዋወት አቀራረብ ይሁን በሌላ ጉዳይ ከእግርኳሱ በቶሎ ይወጣሉ ፤ አንተም የዚህ ሰለባ ሆነሀል?

የኔ ከአሰልጣኞች የጨዋታ ፍልስፍና ወይም ኳስ በመቻሌ ለእነርሱ አጨዋወት ባለመመቸቴ አይደለም ከእግርኳሱ የወጣሁት በማላቀው ነገር ነው። እንዲህ እንዲህ ነው ብዬ ስም ጠቅሼ መናገር ለጊዜው አልፈልግም። ሆኖም ስድስት ዓመት እንኳን አልተጫወትኩም። በፕሪሚየር ሊጉ ባንክ እና አዳማ አራት ዓመት ነው የተጫወትኩት። ሆኖም ብዙ መጫወት እየቻልኩ የሌለ ስም ተሰጥቶኝ በማላቀው ነገር ነው ከሲስተሙ ልወጣ የቻልኩት።

ካለፈው ህይወትህ ብዙ ተምሬያለው ትላለህ ?

በጣም ፤ አሁን ሁሉም ነገር ገብቶኛል። ራሴንም በአዲስ መልክ ይዤ ለመምጣት በአዕምሮውም በአካል ብቃቱም እያዘጋጀው ነው። ትዳርም መሥርቼ ባለቤቴ ከቀናት በኃላ የልጅ አባት ልታደርገኝ ነው። አሁን የቤተሰብ ኃላፊነት አለብኝ። ስለዚህ የበለጠ ጠንክሬ እመጣለው።

ለተወሰኑ ወራቶች ከሜዳ ርቀሀል ወደ ቀድሞ አቋምህ ለመመለስ በምን እየሰራህ ትገኛለህ ?

ካሳለፍኩት አስቸጋሪ ጊዜ አኳያ ራሴን በፊት ወደ ነበረኝ ጥሩ የእግርኳስ ህይወት ለመመለስ በቀን በቀን ልምምዴን እየሰራው ነው። አቃቂ ሠላሳ አምስት ሜዳ እየሰራሁ ነው። ወደ ነበረኝ ነገር ለመመለስ በጣም ከፍተኛ ጉጉት ላይ እገኛለው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!