ከሦስት ቡድኖች ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ታሪክ ያለው ቢንያም ዳርሰማ (ብላክ) የት ይገኛል?

በእልህኝነቱ እና በከፍተኛ አቅም በቀኝ መስመር ሲመላለስ ይታወቃል። በመብራት ኃይል፣ መከላከያ፣ ንግድ ባንክ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ወልዲያ የተጫወተው ቢንያም ዳርሰማ (ብላክ) የት ይገኛል?

በመብራት ኃይል በ1994 “ሲ” ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኃላ በቆየበት ሁለት ዓመት ውስጥ በወቅቱ ከነበሩ የቡድኑ ጠንካራ ተጫዋቾች መሐል ሰብሮ በመግባት ቋሚ ተሰላፊ መሆን አዳጋች ሲሆንበት በውሰት በአሰልጣኝ ንጉሤ ደስታ መልማይነት ወደ መከላከያ በውሰት አምርቶ መከላከያን ወደ ፕሪምየር ሊግ ከማሳደጉ ባሻገር የ1998ቱ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን በማንሳት ስኬታማ የሆኑ ሰባት ዓመታትን በመከላከያ ቤት አሳልፏል። በመቀጠል ከአሰልጣኝ ንጉሤ ደስታ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁለት ዓመት ቆይታ አድርጎ ወደ ምሥራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ በመሄድ በ2007 በአሰልጣኝ መሠረት ማኒ ከሚመራው ቡድን ጋር በመሆን በጥሩ አቋም ወደ ፕሪምየር ሊግ አስገብቷል። በቀጣይ ዓመት በድሬዳዋ ይቆያል ቢባልም ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ለሦስተኛ ጊዜ ከአሰልጣኝ ንጉሤ ጋር ለመስራት ወልዲያን በመቀላቀል በከፍተኛ ሊግ በሁሉም ጨዋታዎች በመሳተፍ ወልዲያን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካሳደጉ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ መሆኑን አስመስክሯል። ለሁለት ዓመት ከወልዲያ ጋር ጥሩ ጊዜ ካሳለፈ በኃላ በ2010 መግቢያ ላይ ያልጠበቀው ድንገተኛ የሆነ የቤተሰብ ችግር አጋጥሞት በአሁኑ ሰዓት ክለብ አልባ ሆኖ ይገኛል። ይህ የቀኝ መስመር ታታሪ ተከላካይ በአሁኑ ወቅት የት ይገኛል ስትል ሶከር ኢትዮጵያ ካለበት አፈላልጋ አጭር ቆይታ አድርጋለች።

የእግርኳስ እድገትህ እንዴት ነው ?

ኤልፓ ከ ሲ ቡድን ነው በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን ያደኩት። እኛ ባደግንበት ጊዜ ደግሞ መብራት ኃይል ውስጥ በጣም ትላልቅ ስም ያላቸው የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ነበሩ። እነርሱን አስቀምጦ ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን በጣም አስቸጋሪ ነበር። ያም ቢሆን ግን በትዕግስት ብዙ ነገር እየተማርኩ ከዛሬ ነገ የመሰለፍ እድል አገኛለው ብዬ ባስብም ሊሆን ስላልቻለ ከሦስት ዓመት በኃላ ነፍሱን ይማረው በአሰልጣኝ ንጉሤ ደስታ ጠቋሚነት መከላከያ ገብቻለው። ከዛም በኃላ በንግድ ባንክ፣ በድሬዳዋ ከተማ እና ወልዲያ በጥሩ ሁኔታ ደስተኛ ሆኜ ተጫውቻለሁ።

ለአንተ በእግርኳስ ህይወትህ ስኬታማ የምትለው የት የተጫወትክበት ነው ?

በተጫወትኩባቸው ቡድኖች ሁሉ አሪፍ የእግርኳስ ቆይታ ነበረኝ። በተለይ የመከላከያ ቆይታዬ በጣም ጥሩ የሚባል ነበር። የእግርኳስ ህይወቴን ጀመርኩ የምለው፣ ብዙ መልካም ነገር ያገኘሁት በመከላከያ ነው። ሰባት ዓመት በመከላከያ ስቆይ ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድጌ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን በማንሳት አንድ ታሪክ ማስቀመጥ ችያለው። ጦሩ በወቅቱ ደስ የሚል ቡድን ነበር አንተነህ አላምረው፣ ፋሲል ተካልኝ፣ ሳሙኤል ደምሴ (ኩኩሻ) ሌሎችም ተጫዋቾች ነበሩ። መከላከያ የነበረኝ ጊዜ ፈጣሪ ይመስገን አቅሜን ያሳየሁበት ቡድን ነው።

ከአሰልጣኝ ንጉሤ ደስታ ጋር የነበራችሁ ትስስር እንዴት ነው? ከተለያዩ ቡድኖች ጋር መገናኘታችሁ ?

ነፍሱን ይማረው አሰልጣኝ ንጉሤ በእኔ እምነት ነበረው። አቅም እና ባህሪዬንም በሚገባ ነው የሚረዳው። ስለዚህ ከእርሱ ጋር መከላከያ ምክትል ሆኖ ከዛ ውጭ በንግድ ባንክ፣ በወልዲያ አብረን ሰርተናል። ወልዲያን በነበርኩበት ጊዜ በአነስተኛ የደሞዝ ክፍያ ሁሉንም ጨዋታ በመጫወት እየደማን፣ እየቆሰልን አንበል በመሆን ጭምር በከፍተኛ መስዋትነት በአስቸጋሪ ውጣ ውረድ ወልዲያን ፕሪሚየር ሊግ አሳድገናል። ከዛም በሊጉ የምንችለውን አድርገን አቆይተን በ2010 አሰልጣኝ ንጉሴ በገዛ ፍቃዱ ለቆ ወደ ደደቢት ሲሄድ እኔንም ከወልዲያ ልለቅ ችያለው። ደደቢትም ይዞኝ ሊሄድ ተነጋግረን ነበር። ግን ቤተሰቤ ላይ አሳዛኝ ነገር ተፈጠረ እና አብረን ሳንሰራ ቀርተናል።

ሦስት ቡድን ከታችኛው ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ አስገብተሀል። ምንድነው ወደ ሊጉ የማሳደግ ገድ አለክ ማለት ነው ?

ዕድለኛ ነኝ፤ ፈጣሪም ረድቶኝ በሄድኩባቸው ሦስት ቡድኖች (መከላከያ፣ ድሬዳዋ እና ወልዲያን) ወደ ፕሪምየር ሊግ አስገብቻለው። በተለይ በእግርኳስ ህይወቴ ሁሉንም ጨዋታ በመጫወት በጣም ለፋሁኝ፣ ደከምኩኝ የምለው እንደ ድሬደዋ እና ወልድያ ክለብ የለም። ምክንያቱም አንድ ጨዋታ ሳትወጣ መጫወት መታደል ነው። ያውም በታችኛው ዲቪዚዮን ከባድ ነው። ግን ከፕሪምየር ሊጉ ዝቅ ብዬ በመጫወቴ እየተዝናናው ደስ እያለኝ ነው፤ ፈጣሪ ይመስገን። ይህ ደግሞ የሆነው በእኔ ብቻ አይደለም። በሄድኩበት ቡድን ሁሉ የሚያጋጥሙኝ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ናቸው። ከእነርሱ ጋር በጋራ ተጋግዤ፣ ሰርቼ ያመጣሁት ውጤት ነው።

ያጋጠመህ አሳዛኝ ነገር ምድነው ?

ቅድም እንዳልኩህ ከወልዲያ ለቅቄ ንጉሴ ደደቢት እንደሚወስደኝ ነግሮኝ ዝግጅት እገባለው ባልኩበት ሰዓት በሚያሳዝን ሁኔታ ክምረት ላይ ታናሽ ወንድሜ መኪና እየነዳ ገደል ይገባል። ከዚህ በኃላ ነገሮች ሁሉ ተበለሻሹብኝ። ምንም ነገር ቢሆን ከቤተሰብ በላይ የሚበልጥ ነገር የለም ብዬ ሁለት ዓመታት ከሜዳ ልርቅ ችያለው።

በቀጣይ ምን ታስባለህ ?

እግርኳስን እጫወታለሁ አላቆምኩም። ራሴን ከምንም ነገር አርቄ ስለምጠብቅ መጫወት የምችልበት አቅሙ አለኝ። በቀጣይ ከፈጣሪ ጋር ከአንዳንድ ክለቦች ጋር እየተነጋገርኩ ነው። በቅርቡ ወደ ሜዳ እመለሳለሁ። ዋናው ሰውነት አይወፍር መጠጥ ምናምን አትቅመስ እንጂ በኢትዮጵያ እግርኳስን መጫወት ይቻላል። እኔ ደግሞ ራሴን በደንብ ስለምጠብቅ የመጫወት አቅሙ በጣም አለኝ።

በመጨረሻ…

ለእኔ በእግርኳስ ትልቁ ምሳሌዬ ሙሉዓለም ረጋሳ ነው። በቅርቤም ያለው እርሱ ስለሆነ አላውቅም ያስተማረኝ እርሱ ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ መክሮኝ ያሳደገኝ እርሱ ነው። የእርሱ ነገር ሁሉ ደስ ይለኛል። በየመጠጥ ቤቱ አታየውም መጫወት ብቻ ነው የሚያውቀው። ከህፃናት ጋር ከአዋቂዎች ጋር ይጫወታል። በቃ እርሱ ለኔ ትልቅ ምሳሌዬ ነው። የሚገርምህ እርሱ መክሮኝ ትልቅ ደረጃ ደርሼ በ1998 እኔ መከላከያ አንበል ሆኜ እርሱ ጊዮርጊስ አንበል ሆኖ ስንገናኝ የሳቀብኝን ሳቅ መቼም አረሳውም። መስዑድ መሐመድ እና ኤልያስ ማሞም ጓደኞቼ ናቸው። እነርሱ ጋር አብሬ አሁን እየሰራው ነው። ሌላው መብራት ኃይል እያለው ስናደግ ጫማ፣ ማልያ አልነበረንም። ዮርዳኖስ ዓባይ እና ዮናስ ገብረሚካኤል እየገዙ ጫማ ማልያ በመስጠት እንዲሁም እየመከሩ በርታ በማለት ያሳደገኝ እነርሱ ናቸው። በእኔ የእግርኳስ ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው፣ መቼም የማረሳቸው ወንድሞቼ ናቸው።

🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!