ስለ አንተነህ ፈለቀ ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

ያመኑበትን ነገር በግልፅ ፣ በዕውቀትና በምክንያታዊነት ከሚናገሩ ተጫዋቾች በግንባር ቀደምትነት ይመደባል። ብዙዎች ባላሰኩት መንገድ ለሁለቱ የሸገር ደርቢ ቡድኖች በአምበልነት ተጫውቷል። በቀለም ትምህርቱ ማስተርሱን የያዘው በዘጠናዎቹ ከተፈጠሩ ድንቅ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ግዙፉ አንተነህ ፈለቀ ማነው ?

በተወለደበት አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በሠፈር ውስጥ በመጫወት ጅማሮውን በማድረግ በኃላም በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጫወት ችሏል። እርሱ ለትምህርቱ ቅድሚያ ትኩረት ቢሰጥም መምህራኖቹ ከትምህርቱ ይልቅ እግርኳስ ተጫዋች እንዲሆን ከፍተኛ ግፊት አድርገውበታል። ይልቁንም ትምህርት ቤቱን ወክሎ መጫወት ካልቻለ ውጤት እስከ መሰረዝ የሚያደርስ ጫና ያሳድሩበት እንደነበር ይነገራል። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከሰሜን አፍሪካዊቷ ግብፅ ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ ሊያደርጉ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል። ታዲያ ከዚህ የአስር ሰዓት ጨዋታ አስቀድሞ በስምንት ሰዓት ወደፊት ተስፋ የሚጣልባቸው ሁለት የታዳጊ ቡድኖች የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ተመልካቹን እንዲያዝናኑም በተመልካች ፊት በመጫወታቸው እንዲነቃቁም በማሰብ የተዘጋጀ ጨዋታ ነበር። ታዲያ ይህን ጨዋታ በክቡር ትሪቡን ቁጭ ብሎ የሚከታተል አንድ ታላቅ የእግርኳስ ሰው ነበር ፤ ጋሽ መንግስቱ ወርቁ ነበር። አንድ ቁመቱ ረዘም ያለ በሰውነቱ ገዘፍ ብሎ የሚታይ ልጅ በጨዋታው ላይ አስደናቂ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተመለከተው ጋሽ መንግስቱ ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ከተቀመጡበት ወንበር ተነስተው ወደ መልበሻ ክፍል በማምራት ይህን ታዳጊ ጠርተው ያናግሩታል ” ከዕሩቅ ሰውነትህ ገዝፎ ሲያዩህ ትልቅ ትመስላለህ ፤ ገና ልጅ ነህ፡፡ በል ነገ ጠዋት የንግድ ባንክ ሜዳ መጥተህ ልምምድ መስራት ትችላለህ፡፡” ይሉታል። በጣም ያልጠበቀው ያላሰበውን ይህን ጥሪ ተቀብሎ ባልተለመደ በሚገርም ሁኔታ ገና በአስራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ የሚገኘው ይህ ተስፈኛ ወጣት እንደማንኛውም እግርኳሰኛ ‘ሲ’ ‘ቢ’ ቡድን አልፎ ሳይጫወት በቀጥታ በ1988 ለንግድ ባንክ መጫወት ችሏል። ጋሽ መንግስቱ ወርቁ ከወራት ቆይታ በኃላ ከንግድ ባንክ ጋር ሲለያዩ አሰልጣኝ አስመላሽ ቡድኑን ሲረከብ ” አንተነህ ዋናው ቡድን መሆን የለበትም ፤ ብዙም ልምድ የለውም ገናም ልጅ ነው፡፡” በማለት ወደ ‘ቢ’ ቡድን ወርዶ መጫወት አለበት በሚል የተለያዩ ጭቅጭቆች ቢፈጠሩም ከጨዋታ ጨዋታ ዕድገቱ እየጨመረ ወደ ፊት በትልቅ ደረጃ መጫወት የሚያስችለው አቅም እንዳለው እያስመሰከረ መምጣት ቻለ። የመጀመርያ የጎል አካውንቱን ንግድ ባንክ በገባበት ዓመት ቡና ላይ በማስቆጠር ለዓመታት በጥሩ ብቃት መዝለቅ ቻለ። የዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ አምዳችን እንግዳ በአጥቂ ፣ አማካይ እና ተከላካይ ቦታዎች ላይ ሁለገብ ተጫዋች በመሆን የሚታወቀው አንተነህ ፈለቀ ነው።

በንግድ ባንክ በአጥቂ ቦታ ለሦስት ዓመት ያገለገለው ግዙፉ አጥቂ አንተነህ ፈለቀ ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ ቦትስዎና ጋቦሮኒ ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ላይ ተመርጦ መጫወት መቻሉም ይታወሳል።

በጣም ግልፅ ፣ ያመነበትን በመሰለው መንገድ እና ብዙዎችን ማሳመን በሚችል መልኩ የመናገር ክህሎት እንዳለው የሚነገርለት አንተነህ ለዓመታት በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ እይታ ውስጥ ገብቶ ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ በመጨረሻም በ1991 ታላቁን ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስን መቀላቀል ቻለ። ለዘመናት ህልሙ የሆነው እና ከልጅነቱ ጀምሮ ሲደግፈው የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተቀላቀለበት ዓመት የሊጉን ዋንጫ ከማንሳቱ በተጨማሪ ሌሎች ስኬቶችን ቢጎናፀፍም በተለይ የ1995ቱ የፕሪሚየር ሊግ ድል ውስጥ የአንተነህ አስተዋፆኦ ከፍተኛ ነበር። ከ1991–1997 በነበረው የፈረሰኞቹ ቤት ቆይታው በመሀል ከሀገር ውጪ የመጫወት ዕድል አግኝቶ ለሱዳኑ ጠንካራ ቡድን ኤል ሜሪክ ለሁለት ዓመታት በመጫወት አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት የሊጉ ዋንጫ ከማንሳት ጀምሮ ክለቡን ወክሎ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ መሳተፍ ችሎ ነበር። በዚህ ብቻ ያላበቃው አንተነህ ጉዞ ከፍ ወደ አለ ምዕራፍ ተሻግሮ ወደ ጀርመን በማቅናት ለስድስት ወራት የተሳካ የሙከራ ጊዜ ቢያደርግም በከተማው አስተዳደር ውስጥ በተፈጠረ የክለብ አደረጃጀት ውሳኔ ምክንያት ሳይሳካለት ወደ ሀገሩ ተመልሶ በድጋሚ ለፈረሰኞቹ መጫወት ችሏል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተው እና የቅርብ ጓደኛው እንደሆነ የሚነገርለት ቴዎድሮስ በቀለ ቦካንዴ አንተነህ ፈለቀን እንዲህ ይገልፀዋል ” አንተነህ በጣም የቅርብ ጓደኛዬ ነው። ከጊዮርጊስ ጀምሮ ነው የምንተዋወቀው ፡፡ ጊዮርጊስ ሲመጣ አስራት ተከላካይ ነው ያደረገው፡፡ በኃላ ተጫዋቾች ፊት ላይ ሲጎዱ አጥቂ በመሆን ምርጥ ብቃቱን በማሳየት የተጫወተ ሁለገብ ተጫዋች ነው። በካንፕ የማይኖር እግርኳስን እየተጫወተ የወደፊት ህይወቱን ያስተካክል ነበር፡፡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ መነሻውም የሆነው ይህ ይመስለኛል። አንተነህ በጣም ግልፅ ፣ ተናጋሪ እና የመሰለውን የሚያደርግ እጅግ ጥሩ ሰው ነው፡፡” በማለት ይናገራል።

ቅዱስ ጊዮርጊስን በተለያዩ ቦታዎች በመጫወት ትልቅ ዋጋ የከፈለው ሁለገቡ ተጨዋች በስተመጨረሻም ለፈረሰኞቹ ለረጅም ዓመት የማገልገል ፍላጎት ቢኖረው በተለያዩ ምክንያቶች ከክለቡ አመራሮች ጋር ሳይስማማ በመቅረቱ በ1997 ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቷል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በዋንጫ የታጀበ ስኬት ባይኖረውም ከቡድኑ ጋር በፍጥነት ተላምዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ አምበል እስከ መሆን ደርሷል። በሁለቱም የሸገር ቡድኖች አምበል በመሆን በታሪክ አጋጣሚ በስንት አንዴ የሚገኘውን ትልቅ ኃላፊነት ካገኙ ተጫዋቾች ብቸኛ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል።

በኢትዮጵያ ቡና እና በብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተው እና የእርሱ የምንግዜም አድናቂ እንደሆነ የሚናገረው ዕድሉ ደረጄ ስለ አንተነህ ፈለቀ ይሄን ምስክርነት ይሰጣል ” አንተነህ የሚገርም ጭንቅላት ያለው ፣ እኔ በህይወቴ ካጋጠሙኝ ትልቅ ስብዕና ካላቸው ተጫዋቾች በጣም ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው። በጣም ሥነ ስርዓት ያለው ፣ የቡድን መንፈስ አንድ በማድረግ መናገር የሚችል ፣ አቋሙን በትክክል የሚገልፅ ፣ ወዴት መሄድ እንደሚፈልግ የሚያውቅ ፣ በጥሩ ሁኔታ ሰዎችን ማሳመን የሚችል ፣ የሚያምንባቸው ነገሮች ሁሉ ምክንያታዊ የሆኑ የሚገርም ሰው ነው። ከኢትዮጵያ ተጫዋቾች ቁጥር አንድ ስብዕና ያለው ሰው ነው። በሥርዓት ነው የተማረው ፣ የቤተሰብ አስተዳደጉ በጣም ጥሩ የነበረ በጣም ሲበዛ አድናቂው የሆንኩ ሰው ነው፡፡” በማለት ይናገራል።

ከወጣት ቡድን እስከ ዋነው ብሔራዊ ቡድን ድረስ ሀገሩን በተለያዩ ቦታዎች በመጫወት ያገለገለው አንተነህ ኢትዮጵያ የሴካፋን ዋንጫ ከዘጠናዎቹ መጀመርያ አንስቶ በአነሳችባቸው ሦሰት አጋጣሚዎች የቡድኑ አባል በመሆን የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። አጭር በሆነው የእግርኳስ ህይወቱ በሦስት ክለቦች ብቻ አሳልፎ በስተመጨረሻ ሳይታሰብ እና ሳይጠበቅ ብዙ ቀሪ ዓመታትን የመጫወት አቅሙ እያለው ድንገት ከ1998ቱ ኢትዮጵያ ሩዋንዳ ላይ ካስመዘገበችው የሴካፋ ድል ማግስት ወደ ሀገሩ ለመመለስ አውሮፕላን ላይ እያለ እግርኳስን ለማቆም ወስኖ ጫማውን ሰቅሏል።

ከእግርኳስ በኃላ ባለው ህይወቱ አስቀድሞ በእግርኳሱ ውስጥ እያለ በጎን ያስኬዳቸው የነበሩ ስራዎችን በመቀጠል በንግዱ እና በትምህርቱ ዓለም የተሳኩ ዓመታትን እያሳለፈ ይገኛል። ከእርሱ ጋር ቁጭ ብለው ቢያወሩ የማይሰለቸውና በስብዕናው ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችለው አንደበተ ርዕቱው አንተነህ ፈለቀ በእግርኳሰ ህይወቱ እና ስላሳለፋቸው ውጣ ውረዶች እና ስለወደፊት ራዕዮቹ በዛሬው የዘጠናዎቹ ከዋክብት አምዳችን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቶናል።

“በወቅቱ በደርግ ጊዜ ለትምህርት ቤቶች ውድድር ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ ስለነበረ በትምህርት ቤቶች መካከል በሚደረጉ ውድድሮች አብዝቼ መጫወት መቻሌ ለእኔ የእግርኳስ ዕድገት ትልቁን ቦታ ይይዛል። እኔ እግርኳስ ተጫዋች የመሆን ዓላማው አልነበረኝም፡፡ ይልቁንም በቀለም ትምህርቴ ላይ ማተኮር እፈልግ ነበር። እንዲያውም ከ10ኛ ክፍል በኃላ ቦሌ ትምህርት ቤት የስፖርት መምህሬ ጋሽ ታደሰ እንድጫወት ከመፈለጉ የተነሳ አልጫወትም ስው ለመምህራኖቹ ነግሬ ውጤት እንደሚቀንሱብኝ ይነግረኝ ነበር። ተደራድረን ሌሎቹ በሳምንት አምስቴ እኔ ደግሞ በሳምንት ሁለቴ እንድሰራ የተስማማንበት አጋጣሚ ነበር። በአንድ ጋጣሚ ደግሞ በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገ ጨዋታ ነፍሱን ይማረውና ታለቁ የእግርኳስ ሰው ጋሽ መንግስቱ ወረቁ ለታዳጊ ተጫዋቾች ከፍተኛ ትኩረጥ ይሰጥ ስለነበረ በቀጥታ በ’ሲ’ እና ‘ቢ’ ቡድን ሳላልፍ ገና በታዳጊ ዕድሜዬ በወቅቱ ጠንካራ የነበረውን ንግድ ባንክን መቀላቀል ችያለው። እግርኳስን ለስሜት እንጂ ትኩረት ሰጥቼው በክለብ ደረጃ እጫወታለው የሚል ሀሳቡ አልነበረኝም። ሆኖም በዚህ አጋጣሚ የተከበረውን የእግርኳስ ሰው ጋሽ መንግስቱን በጣም አመሰግነዋለው። እርሱ ነው ትንሽም ቢሆን ስኬታማ የእግርኳስ ሰው እንድሆን ያደረገኝ፡፡”

“ከልጅነቴ ጀምሮ ለምን እንደሆነ አላውቅም የቅዱስ ጊዮርጊስን መለያ ሳየው የሆነ ስሜት ይሰማኝ ነበር። በጣም የምወደው ከልጅነቴ ጀምሮ የምከታተለው ከልቤ የምደግፈው የዘላዓለም ክለቤ ነው። አባቴ የቡና ደጋፊ ሆኖ እኔ ጊዮርጊስን እየደገፍኩ ገና በልጅነቴ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ክርክሮች ነበሩ። ወደ እግርኳሱ ከገባሁበት ካልቀረ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት አለብኝ ብዬ መወሰን የጀመርኩት ገና ባንክ እያለው ነበር። አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ገና ሲጠይቀኝ ያለ ምንም ማቅማማት ለመጫወት ወሰንኩኝ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በገባሁበት ተከታታይ ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን አንስቻለው። በመሐል ወደ ሱዳን ብሔድም ስመለስም በእግርኳስ ህይወቴ መቼም የማረሳውን ትልቁን ስኬት በ1995 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አሳክቻለወ። ኮከብ ተጫዋች የመሆን ዕድሉም ነበረኝ፡፡ በኃላ በምን እንደቀረ አከራካሪ ቢሆንም በአጠቃላይ በጊዮርጊስ የነበረኝ ቆይታ በጣም አስደሳች እና ጥሩ የሚባል ነበር፡፡”

“ሱዳን ከኤልሜሪክ ጋር የነበረኝ ጊዜ ጥሩ ነው። ቡድኑን ከረጅም ዓመት በኃላ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ከማስቻላችን በተጓዳኝ ለኮከብ ጎል አግቢነትም እፎካከር ነበር። ሁለት ዓመት ቆይቼ በኃላ ላይ ክለቡ በባለሀብቶች የገንዘብ ድጎማ የሚንቀሳቀስ ስለነበር የአመራር ለውጥ ሲመጣ ከክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች አጋጥሞት ለስድስት ወር ደመወዝ ሊከፍለን ባለመቻሉ ጥዬ በመምጣት ተመልሼ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት ችያለው፡፡”

“ሱዳን ኤልሜሪክ እያለው አሰልጣኜ ዩጎዝላቪያዊ ነበር። የእርሱ ጓደኛ ጀርመን ካይዘርስ ስላውተር እና ማንሀዬ የሚባሉ በአንድ ከተማ የሚገኙ ቡድኖች ውስጥ አሰልጣኝ ስለነበር በዚህ ምክንያት ወደ ጀመርመን ሄድ፡፡ በጀርመን ስድስት ወር ያህል ቆይቼ ነበር። የሄድኩበት ክለብ ማንሀዬ የኢንዱስትሪ ከተማ ነው። ሁለት upper እና lower class የሚባሉ ክለቦች ውስጥ የሙከራ ልምምዴን እየሰራው ባለሁበት ሁኔታ የከተማው መንግስት በአንድ ከተማ ሁለት ቡድን ከሚኖር ሁለቱን ጨፈለቀን አንድ ክለብ ከተማውን መወከል አለበት ብለው በመወሰናቸው ሙከራውን በጥሩ ሁኔታ አልፈን የስራ ፍቃድ ለማውጣት ሁሉ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። በኃላ በበጀት እጥርት እና በሌሎች ነገሮችም ሲወሳሰቡ እዚህ ደግሞ የ1995 ውድድር ሊጀመር ምዝገባው ሊያልፈኝ ስለሆነ ጥዬ ወደ ጊዮርጊስ መጥቻለው፡፡”

“ከቅዱስ ጊዮርጊስ የወጣሁበት ምክንያት በግለሰቦች ፍላጎት ነው። በወቅቱ የነበሩ የክለቡ አመራሮች እና በተለያዩ ጉዳዮች ጣልቃ እየገቡ ከነበሩ ሰዎች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት እኔን እስከ ማስወጣት የሚደርስ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ሆኗል። ያው ዞሮዞሮ ሦስት የማይሞሉ ሰዎች ክለቡን እንደፈለጉ እንደሚያተራምሱ ሁሉም ተጫዋች የሚገልፀው ነው። እስካሁንም ድረስ እነርሱን የሚያስደስት ወይም እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ካልሄድክ ከጊዮርጊስ ትወገዳለህ። ምንም ዓይነት ተጫዋች ብትሆን ትወገዳለህ፡፡ ከሙሉጌታ ከበደ ጀምሮ እስካሁን የምናየው እውነታ ይሄ ነው። ከጊዮርጊስ እንደወጣው እኔን ለመውሰድ ፍላጎት ያሳየው ቡና ስለነበረ ወደ ቡና አምርቻለው። አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል በቡና ተጫውቼ ጥሩ ቆይታ አድርጊያለሁ። አምበልም በመሆን ቡድኑን መርቻለው ፤ አልፎም ተርፎ ነፍሱን ይማረው እና በአሰልጣኝ ሦዩም አባተ ስር ከአምበልነት በላይ ከአሰልጠኝነት ያልተነሰነሰ ሚና ይሰጠኝ ነበር። ብዙ ጊዜ ቡና ጥሩ ጥሩ ልጆች ይኖሩት ነበር። ሆኖም የዲሲፒሊንድ ችግር ጎልቶ ይወጣ ስለነበር ይህን ችግር ማስተካከል ከቻልን ውጤታማ ማድረግ እንችላለን የሚል ዕምነት አድሮብን እንሰራ ነበር። ብቻ እነርሱ አብሬያቸው እንድቆይ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም እኔ ግን እግርኳስን ለማቆም በመወሰኔ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ለመለያየት በቅቻለው።”

“በፍጥነት ብዙም መጫወት እየቻልኩ እግርኳስን ለማቆም የወሰንኩት ምክንያት ባቃ ብዙም የሚያስደስት ነገር ስላልነበር ነው። በዚህ ላይ የእግርኳሱ ኢንዱስትሪ እየደከመ ፣ ውድድሩ ተቀባይነቱን እያጣ ፣ ፉክክሩም ግልፅ ወይም ሚዛናዊ ያልሆነ ብዙ ሸፍጥ አሻጥር የበዛበት ሲሆን በዚህ ሙያ ውስጥ መቀጠል ብክነት (ጊዜ ማቃጠል) ነው ብዬ ከሩዋንዳ የሴካፋ ዋንጫ ድል መልስ አውሮፕላን ውስጥ ሆኜ ነው። ለቴዎድሮስ በቀለ (ቦካንዴ) ‘ከአሁን በኃላ ወደ ሜዳ አልመጣም እግርኳስ ላቆም ነው’ አልኩት እርሱም ‘ለምን ?’ አለኝ:: ‘አይ ከዚህ በኃላ የሚፈጠር ነገር አይኖርም’ አልኩት:: ‘እንዴት ? ምን ሆነሀል ?’ ሲለኝ ‘በቃ ለእግርኳስ ያለኝ ፍላጎት ወርዷል ጨረስኩ:: ለእግርኳስ ብዬ ጠዋት ተነስቼ ቁምጣ አድርጌ የምሰራበት ፍላጎት የለም’ አልኩት:: ‘አይ ዝም ብለህ አንድ ሳምንት ምክንያት ፈጥረህ እረፍት አድርገህ አስብበት‘ አለኝ፡፡ ‘አይ የሚሆን አይመስለኝም‘ ብዬ የቡናን ትጥቅ ሳላስረክብ ቤቴ ገባው ፤ ስልኬን አጠፋው ቀረው ቀረው አለቀ አበቃ። በነገራችን ላይ እግርኳስን ያቆምኩት ገና በ27 ዓመቴ ነው። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በፍጥነት እግርኳስን ጀምሬ በፍጥነት እግርኳስን ማቆሜ ውሳኔዬ ትክክል ነው። ለምን ከዚህ በኃላ በእግርኳሱ ምንድነው የማሳካው ብዬ ሳስብ ሁሉን አሳክቻለው። ብሔራዊ ቡድን ተጫውቻለው ፣ ትልቅ ዋንጫ አንስቻለው። በሀገሪቱ ትልቅ ክለቦች አምበል ሆኖ እስከ መጫወት ደርሻለው ፣ ከሀገር ውጪም ተጫውቻለው፡፡ ስለዚህ ምንም የቀረኝ ነገር የለም። ከዚህ በኃላ እየሰለቸኝ እየወረድኩ ነበር የምመጣው ስለሆነም እግርኳስ ማቆሜ ትክክለኛ ውሳኔ ነው። በጎን ደግሞ ሌሎች ስራዎችን ቁጭ ብለው የማይጠብቁኝን እያጣው ልሄድ ነው። በዚህ ምክንያት እግኳስን ለማቆም ወስኛለው።”

“በእግርኳስ ብዙ የምቆጭበት ነገር የለም። አብዛኛውን ስኬት አሳክቻለው። ምንአልባት አውሮፓ ውስጥ ነበረኝ። ይህን አለማሳካቴ ይቆጨኝ ይሆናል። አሰልጣኝ ጋርዝያቶ ምንም እንኳን ወደ አርጀንቲና ይዞኝ ባይሄድም እኔን ፣ ዮርዳኖስ አባይ ፣ ጌቱ ተሾመን እና አንዋር ሲራጅ(ትንሹን) ሁልጊዜም ባገኘው አጋጣሚ ‘እናንተ ከኢትዮጵያ ውጭ በአውሮፓ መጫወት አለባችሁ’ ይለን ነበር። ‘በዋናው ሊግ በአንደኛ ዲቪዚዮን መጫወት ካልቻላችሁ እንኳን በታችኛው ዲቪዚዮን መጫወት የምትችሉበት አቅም አላችሁ‘ ይል ነበር። ይሄን አለማሳካቴ ሊቆጨኝ ይችላል እንጂ ብዙም የምቆጭበት ነገር የለም፡፡”

“እግርኳስን እንዳቆምኩ ወድያውኑ ወደ ትምህርት ገብቼ በአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በማናጅመንት እና ዓለም አቀፍ የቢዝነስ አስተዳደር ማስተርስ ድግሪ ያዝኩኝ። ከትምህርት ውጪ ለመቶ ሃይ አምስት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ የወረቀት ፋብሪካ ነበረኝ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ፋብሪካውን ሸጬ አሁን የተለየ በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ አዲስ ሥራ ከፍቼ እየተንቀሳቀስኩ ሲሆን በተጨማሪም “እንደራስ” የተሰኘ ኮንክስትራክሽን ድርጅት በመክፈት በሁለቱ ድርጅቶች ላይ ትኩረቴ አድርጌ እየሰራው ነው፡፡”

“ከፈረንሳዩ ኮከብ ተጫዋች ጆርካዬፍ ጋር አንዳንድ አለመግባባቱች ሊፈጠሩ የቻሉት ጀርመን እያለው ነው። ምክንያቱ ለሙከራ ጀርመን እያለው የርሱ ቡድን ካዘይርስላውተር ነበር። እርሱ እና እነታሪምቦ ዌስት እንዲሁም ሌሎች ትልልቅ ተጫዋቾች የነበሩበት ትልቅ ክለብ ነው። እኔ የነበርኩበት ማናዬሄ ክለብ እና ካዘይርስላውተር ልምምድ የሚሰሩት አንድ ላይ የነበረ በመሆኑ መኪና የምናቆምበት ፓርኪንግ አጠገብ ለአጠገብ ነው። እኔ ከተቀመጥኩበት ሆቴል ወደ ሜዳ ስመጣ ሁሌም የምነዳውን መኪና የማቆምበት ቦታ ላይ ጆርካዬፍ ተሳስቶ ይመስለኛል መኪናውን ያቆማል፡፡ በዚህ መሀል መኪና የሚያቆምበት ቦታ ትክክል እንዳልሆነ ነግሬው እርሱም ባለማወቅ ያደረገው መሆኑን ገልፆልኝ ተለያይተናል። በጣም ቀላል የሆነ አጋጣሚ ነው ብዙም አለመግባባት የተፈጠረበት አይደለም፡፡”

“የፌዴሬሽን ፕሬዝደንትነት ለመወዳደር የመጣሁት አንድም ከቁጭት ነው። በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ ብዙ ያየኋቸው ችግሮች ነበሩ። የችግሮቹ የሚመነጩት ብዬ የገመገምኩት ደግሞ ከአመራሩ የአቅም ውስንነት ነው። ይሄን ማንም የሚያምንበት የሚቀበለው ነገር ነው። ከእግርኳሱ የወሰድኩት ነገር አለ ፤ እውቅና አግኝቻለው። ሰው ሆኖ ደግሞ ሁልጊዜ መውሰድ የለበትም የተቀበልከውን መመለስ (መስጠት) መቻል አለበት። ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህ የእግርኳሱ ሙያ ሰው እያጣ ፣ የሰው ድርቅ እየመታው እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል። የስፖርት ቤተሰቡ በጠቅላላ ትኩረቱ በጊዛዊነት ያሉት ውድድሮች ላይ ብቻ ሆኗል። እንዲሁም በፌዴሬሽኑ ውስጥ በአስተዳደር ቦታ ያለው የአቅም ውስንነት ሲታይ ፣ የክለቦችን ሮሮ ስትሰማ የኢትዮጵያ እግርኳስ ችግር ምንጩ መዋቅር ላይ ስለሆነ ይህን መቀየር አለበት በማለት ይህን መቀየር የምንችል ሰዎች ደግሞ በስፖርት ውስጥ ያለፍን ሰዎች ያገባናል ይመለከተናል ብዬ በቁጭት ለሀገሬ አንድ አስተዋፆኦ ካደረኩ በሚል ነበር። የኦሮምያ ክልልን በመወከል በፕሬዝደንትነት ለመወዳደር መምጣት የቻልኩት፡፡”

“ሆኖም ይህ ቁጭቴ ያልወጣለኝ በዋናነት የቅዱስ ጊዮርጊስ አንዳንድ አመራሮች ከአንዳንድ ጥገኛ አመራሮች ጋር በነበራቸው ቁርኝት ውክልናዬ እንዲነሳ ለማድረግ ብዙ ርቀት ነው የሄዱት። ይሄን ደግሞ በድብቅ አልሰሩትም። በግልፅ ደብዳቤ ነው አንተነህ መወከል አይችልም የሚል ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ያስገቡት። ግልባጩም ለእኔ ደርሶኛል። ያው እንደሚታወቀው አመራሮቹ እጃቸው ረጅም ነው። ብዙ ነገር ትክክለኛ በሆነ መንገድ መፈፀም አይችሉም። ስለዚህ አንዳንድ ነገሮችን የሚያስተጓጉሉት ወይም ተፅኖ የሚፈጥሩት በእጅ አዙር ከእንዲህ ያሉ ሰዎች ጋር በመመሳጠር እንዲሁም ስልጣን ላይ ካሉ ሠዎች ጋር በመወዳጀት የማይሆን ምክንያት ሰጥተው እንድነሳ አድርገውኛል። እኔም አሁን ፕሬዝደንት ለሆነው ሰው አስረክቤ ወጥቻለው።”

“በወቅቱ የፈጠረብኝ ስሜት ቀላል አይደለም። ግን ምን አለ መሰለህ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የአመራርነት እውቀት የሌላቸው እና ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ከህግ በላይ እንዲሁም ከአሰራር በላይ የሚሆኑበት እና በእግርኳስ ውስጥ ትልቁን ምስል ለማየት የማይችሉ ውስን የሆነ አቅምና ራዕይ ያላቸው ሰዎች ናቸው። እንዲህ ያሉ ሰዎች ደግሞ ያለ ቦታ ተቀምጠው እግርኳሱን ሲበጠብጡ ስታይ ትገረማለህ። በነገራችን ላይ በእግርኳሱ ብቻ አይደለም በሌላም አካባቢ ሲበጠብጡ ማየት እንደ አንድ ተራ ዜጋ የሚያስቆጭ ነው። በእግርኳሱ እንዳለፈ ሰው ደግሞ ጉዳዩ የባሰ ያሳዝንሀል። ብዙ ነገር ማድረግ እየቻልክ አለማድረግህ ደግሞ የበለጠ ያስቆጭሀል። እነዚህ ሰዎች በእግርኳስ ውስጥ እየፈጠሩ ያሉት አላስፈላጊ ተፅዕኖ የስፖርት ቤተሰቡ ቢያቀው እና መንግስትም ይሄን ነገር ቢገነዘብ በእርግጠኝነት እግርኳሱ መለወጥ ይችላል። በየቦታው አንቀው የያዙት በሁለት ጉዳይ ነው። አንደኛ የግል ጥቅም ለማግኘት ነው። ሁለተኛው ለመታወቅ ነው። ገንዘብ ካላቸው መታወቅ ስለሚፈልጉ ገንዘብ ከሌላቸው ደግሞ ገንዘብ ስለሚፈልጉ ነው። በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ነው እግርኳሱ የተሞላው። ደግሞ ቦታውን ይዘው አይለቁም፣ ተራማጅ አስተሳሰብ የላቸውም፣ አዲስ አሰራር፣ አዲስ አስተሳሰብ አይፈልጉም እንዲሁም እድገት የላቸውም። እድገት ስለሌላቸው ብቻ ሌላውን ሀሳብ የሚያፈልቅ ሰው እንደ ጠላት ነው የሚያዮት። ከቀረብክ ወዲያው ቀንድህን ተመተህ እንድትወጣ ይፈለጋል። በተወሳሰበ ነገሮች ያለፉ ሰዎች ስለሆኑ ማሰብም መስራትም የሚችሉት ሴራ ብቻ ነው። ይህ ስለሆነም በጊዜው ከፕሬዝደንትነት እጩ እንድወጣ ተሰምቶኝ ወሰንኩ።”

“ወደ ፊት ወደዚሁ ዘርፍ የመመለስ እቅድ አለኝ እስካለው ድረስ መታገሌ ይቀጥላል። ያው የተፈጥሮ ሂደት ስለሆነ እኛ ቀድመን አናረጅም (እየሳቀ)። በተፈጥሮ ሂደት ቀድሞ የሚያረጁ ስለሆነ ከዛ በኋላ እንሞክራለን። የዛን ጊዜ ምን አልባት በመሐል እግርኳሱን ለመለወጥ ከቻሉ እሰየው ነው። ካልሆነ ደግሞ ያው የተፈጥሮ ህግን መጠበቅ ነው። ከዛ በታች ያለውን ነገር ሁሉ ሞክረናል አልተሳካም።”

“የኢትዮጵያ እግርኳስ መሠረታዊ ችግር የአመራር ክሎት ነው። ጠቅላላ ጉባኤው ራሱ እግርኳስን በማያቁ ሰዎች ድምፅ ለመስጠት የተሞላ ነው። ይህም በመሆኑ ድምፅ የሚሰጡበትን ካርድ ይሸጡታል። ወደ አመራርነት ለመምጣት የሚፈልግ ሰው ወደዚህ ቦታ ሲመጣ ገንዘብ ያለው መሆን ይጠበቅበታል። ካርዱን የሚገዛ መሆን አለበት። ይህን የሚያስፈፅሙ ደግሞ ደላሎች አሉ። እነዚህን ደላሎች ደግሞ እናቃቸዋለን። ሚዲያ ውስጥ አሉ ሌሎች ቦታዎችም ይገኛሉ። ይገዛል ይመረጣል። ይህ አሰራር ካልተወገደ እንዴት እግርኳሱ ይለወጣል። ምርጫው የሚደረግበት አሰራር መቀየር አለበት። ዘጠና ዘጠኝ ፕርሰት ለህሊና ቦታ በሌላቸው ሰዎች የተሞላ ቦታ ነው። ስልጣን አግኝተው አገልግለው ምንም ሳይሰሩ ወርደው በድጋሚ ሄደው ውክልና ይዘው የሚመጡ አሉ። ይህን ምን ትለዋለህ የሆነ ነገር ቢኖር ነው እንጂ። እግርኳስ በየጊዜው የሚለወጥ የሚሻሻል ነገር ነው። ስለ እግርኳስ ልማት የምታወራበት ቦታ ነው። የአንድ ሰው ፍላጎት መሆን የለበትም። የሚወክሉት ክልሎችስ እንዴት አያፍሩም፣ እንዴት ያልተሳካለትን ሰው መልሰው ወደ አመራርነት ያመጣሉ። ይህ ህዝብ ላይ መቀለድ ነው። ዞሮ ዞሮ ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል። ይህን ስል አላስፈላጊ የሆነ ጣልቃ ገብነት መንግስት ይግባ እያልኩ አይደለም። ግን በተቀመጠው አሰራር ትክክለኛ ሥራ መሰራቱን መከታተል መቆጣጠር አለበት። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሌሎች ባንኮችን ይቆጣጠራል። ትክክለኛውን ስራ መስራታቸውን ይከታተላል ሆኖም እሱ ከተዳከመ ሌሎቹም ባንኮች ይዳከማሉ። ብሔራዊው ባንክ ከደከመ ደግሞ ኢኮኖሚው ይዳከማል። ስለዚህ የብሔራዊ ባንክ ጥንካሬ ለሌሎች ባንኮች መጠንከር አስተዋፆኦ አለው። ልክ እንደዚህ ሁሉ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ትክክለኛው ሰው ጠንካራ አመራር ካልመጣ ክለቦቹ ጠንካራ ሊሆኑ አይችሉም። ብቻ ትንንሽ አጀንዳ ያላቸው አበላቸውን ቆርጠው የሚሄዱ ሰዎቹ ከእግርኳሱ መራቅ አለባቸው። ቦታው ላይ ትክክለኛ የእግርኳስ ሙያተኞች ሊመጡበት የሚችልበት መንገድ መመቻቸት አለበት።”

“የቤተሰብ ህይወቴ ባለ ትዳር እና የአንድ ሴት እንዲሁም የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነኝ። የመጀመርያዋ ልጄ አስራ ስድስት ዓመቷ ነው። ሁለቱ ወንድ ልጆቼ የሦስት ዓመት እና የአንድ ዓመት ልጆች ናቸው። ሴቷ ስለ እግርኳስ ምንም ፍላጎት የላትም። ወንዶቹ ደግሞ ገና ናቸው፤ ወደ ፊት ነው የሚታወቀው።”

“በእግርኳስ ለእኔ ስኬቴ የምለው በኢትዮጵያ ታላላቅ ክለቦች መጫወት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት፣ ብዙ ያደገ ሊግ ባይሆንም የሱዳን ሊግ ላይ መጫወት እና የተለያዮ ዋንጫዎች ማንሳት የሚሉት ናቸው። ግን ይሄ እንደ ስኬት አላያቸውም። ከእኔ የግል ስኬት ይልቅ የሀገሬ እግርኳስ ተለውጦ አድጎ፣ ተወዳጅ ሆኖ ባየው በጣም በግሌ ደስ ይለኛል። የእኔ ድርሻ በእግርኳስ ውስጥ ኖሮ ቢለወጥ እና ባይ ደስ ይለኛል። ለምሳሌ ነፍሳቸውን ይማር እና እንደ ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ ከባድ ቢሆንም እንደርሳቸው አንድ አሻራ ባሳርፍ ደስ ይለኛል። ከተጫዋችነት ይልቅ በአመራርነት የሰሩት ስራ ትልቅ ስኬት ነው። በዛ ደረጃ እና ራዕይ ነው የማስበው።”

“በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሰባት ወር የታገድኩት 1990 ላይ ነው። በዚህ ጊዜ ለአንድ የወዳጅነት ጨዋታ ደብረዘይት ሄደን በፍፁም ለተጫዋች ክብር እና ለብሔራዊ ቡድን በማይመጥን አልጋ ቤት አሳርፈውን ነው። ምንም የተጋነነ ነገር እንዲኖር አስበን አይደለም ግን ኢትዮጵያ ባለት የኢኮኖሚ አቅም አንፃር ለብሔራዊ ቡድኑ የሚመጥን ሆቴል ማሳረፍ ይቻላል ነበር። ሆኖም ከምግብ፣ ከንፅህና፣ ከፀጥታው አንፃር የማይመጥን እና ለተጫዋቾች ያልተሟላ ቦታ ተቀምጠን ነበር። በቡድን ውስጥ ነፍሱን ይማረው አሰግድ ተስፋዬ፣ ኤልያስ ጁሀር ሌሎቹም ትልልቅ ተጫዋቾች ነበሩ። ተጫዋቾቹ በሙሉ ባለው ነገር ደስተኛ ሳይሆኑ አኩርፈዋል። ስብሰባ አድርገን ይህ ችግር መቀረፍ አለበት፣ እንዴት ብዙ ነገር ባልተሟላለት እና ለብሔራዊ ቡድን በማይመጥን ሆቴል እንቀመጣለን። መቀመጥ የለብንም በማለት አምስት ጥያቄዎችን ለፌዴሬሽኑ አመራሮች የሚያቀርቡ አምስት ተጫዋቾች ተወክለን የፌዴሬሽኖቹን አመራሮች እንዲያናግሩን ጠራናቸው። ሁለት የፌዴሬሽኑ ተወካዮች መጥተው ሲያናግሩን የተመረጡት አራት ሰዎች ዝም አሉ። ፈርተው እንደሆነ እኔጃ ግን ይህ በእግርኳሱ የተለመደ ነው። አንተ ጋር ያወራሉ፣ ይጮሀሉ መድረኩ ሲመቻች ግን ዝም ይላሉ። ባይ ባይ ዝም ሲሉ እኔ ተነስቼ አምስቱን ጥያቄ ይሄ ይሄ ችግር አለ ብዬ ተናገርኩኝ መጨረሻ ይህ የማይስተካከል ከሆነ ጥለን እንሄዳለን ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ እኔ ዝግጁ ነኝ ብዬ ተናገርኩኝ። በንጋታው ከሆቴል እንድወጣ እና ፌዴሬሽን ቢሮ ሪፖርት እንዳደርግ ተደርጎ ይህን በመናገሬ ብቻ ጠዋት ስመጣ ደብዳቤ ተፅፎ ተሰጠኝ ከማንኛውም እግርኳሳዊ እንቅስቃሴ ለሰባት ወር ታግደሀል የሚል ለነገሩ ጨዋታው ከኤርትራ ጋር ነበር በኋላ ግን አልተከናወነም። ከሦስት ወር በኃላ ግን ውድድር ሊጀምር አካባቢ ቅጣቱ ተነስቶልኝ ወደ ጨዋታ ተመልሻለው።”

“በመጨረሻ ማለት የምፈልገው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ነው። በአንዳንድ ነገሮች እራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል ብዬ አስባለው። እኛ በወቅቱ የተለዩ ጥያቄዎችን አላነሳንም ነበር። ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ ይካሄድ፣ የጊዮርጊስ የራሱ የገቢ ምንጭ ይኑረው፣ በህጋዊ መንገድ ኦዲት ይደረግ፣ ጊዮርጊስ ውስጥ ያለ አመራር ጊዮርጊስን እየጠቀመ ነው ወይስ እየተጠቀመ ነው፣ የራሱ የልምምድ ሜዳ ይኑረው፣ እስከ መቼ ይሄን የሚያክል ክለብ ሜዳ እየዞረ እየተከራየ ይቆያል፣ ይህ ክለብ ከግለሰብ ጥገኝነት ሊወጣ ይገባል የሚሉ እና ክለቡን ለዘመናት ሊያሻግሩ የሚችሉ ሀሳቦችን ነው ያነሳነው። ከዚህ ሀሳብ ውጭ በጠቅላላ ጉባኤም፣ በመገናኛ ብዙሀንም ሆነ በተለያዮ መድረኮች የተለየ ነገር አላነሳንም፣ አልተናገርንም። በቅርቡ የክለቡ ፕሬዝደንት ጊዮርጊስ ውስጥ እንደ ዳንቴል ሊተረትሩን ነበር። ግን በየድናቸው የሚል በጣም የሚገርም ቃለመጠይቅ ሰጥተው ነበር። እንደሚገባኝ ከሆነ ተርታሪው እና መበየድ የሚሉ ቋንቋዎች ብዙ ጊዜ ከሙያ፣ ከሳይንስ ጋር የሚያያዙ ቋንቋዎች ናቸው። እንጂ ይሄን ያህል ገላጭ የሆኑ ቋንቋዎች አይደሉም። እኛ ክለቡን እንደማንወድ ለክለቡ መጥፎ ተመኚዎች ወይም መጥፎ አድራጊዎች ሆነን አይደለም። ዝም ብሎ በአደባባይ መናገር ሳይሆን የተናገርናቸውን ሰምቶ መፍረድ ያስፈልጋል። የሀሳብ ልዮነቶችን ተቀብሎ ማስተናገድ የማይችል ሰው ምን አይነት ሰው እንደሆነ አይገባኝም። አይደለም እግርኳስ ውስጥ ፖለቲካው ውስጥም የሀሳብ ነፃነት የማይቀበል መወገዝ ያለበት ጉዳይ ነው። ስፖርት ውስጥ ዲሞክራቲክ ካልሆንክ ሌላ ምንም አይነት ተቋም ውስጥ ዲሞክራቲክ ልትሆን አትችልም። እግርኳስ ሌላ አጀንዳ የለውም ክለቡን እንዴት አድርገን ወደ ላቀ ምዕራፍ እናሻግረው፣ እንለውጠው፣ ውጤታማ እናድርገው ነው ያልነው ሌላ አጀንዳ የለም። በዚህ ምክንያት ነው ኢ-ዲሞክራሲያዊ ውሳኔ የተወሰነብን። ለዚህም አራት አይነት ደጋፊዎች አሉ። አንደኞቹ ቀጥታ አመራሩ የሚናገረውን የሚያስተጋቡ በሆነ ጥቅም የተሳሰሩ በየቦታው፣ በየመሐሉ የተቀመጡ ውዥንብር የሚፈጥሩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው። ሁለተኞቹ በስሜት የሚመሩ ናቸው። አንዳንዴ በሞቀበት የሚሄዱ ናቸው። እነዚህ በነገራችን ላይ ብዙ ናቸው። ነገሮችን በማስረጃ በትክለኛ መንገድ አያዮም። ምክንያታዊነት ይጎላቸዋል፣ ድምፃቸውን የት ጋር እንደሆነ ራሱ ልታቅ አትችልም። ሦስተኛዎቹ እንደ እኛ አይነቶቹ ናቸው። ይህ ትክክል አይደለም ስህተት ነው። መታረም አለበት ብለው እስከ መጨረሻው ጥግ ድረስ እየገፉ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርጉ ናቸው። እነዚህ በቁጥር ጥቂቶች ናቸው። አራተኞቹ ይህን ክለብ ከያዙት አመራሮች ውጭ ይህን ክለብ ቢለቁት፣ ጥለው ቢሄዱ የት እንወድቃለን ምን ይመጣል በሚል ፍራቻ ተሸብበው ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው። እነዚህ ደጋፊዎች ይህንን የሚያደርጉት አማራጭ ስላጡ ወይም ስለፈሩ ነው። የእነዚህን ሀሳብ በተወሰነ መልኩ እጋራለው። ነገር ግን መገንዘብ ያለባቸው ክለቡ ታሪካዊ ነው። ምንም ባልነበረበት ደሀ በነበረበት ወቅት መኖር የቻለ ክለብ ነው። ስለዚህ ከግለሰቦች በፊት መኖር የቻለ ክለብ መሆኑን ከታሪኩ ጋር ማወቅ ያስፈልጋል። ክለቡ ምንም ሊሆን አይችልም። እንኳንስ በዚህ ጊዜ ብዙ ደጋፊ ባለው እና ብዙ የኢኮኖሚ አቅም በተፈጠረበት ወቅት ከመኖር ካለመኖር ጋር ማያያዝ ከጊዜው ጋር የሚሄድ አይደለም። ይህን ፍራቻ ማስወገድ አለባቸው። እኔም ተስፋ ያለኝ እነዚህ ላይ ነው። እውነቱን ስለሚያውቁ ጊዮርጊስ ትክክለኛ መንገድ ውስጥ እንዲገባ መጋፈጥ አለባቸው። በአጠቃላይ ሁሉም ደጋፊዎች መሰራት ያለባቸው ነገሮች ባለመሰራታቸው ብዙ ነገር ክለቡ እያጣ ነው። ደጋፊው ይሄን ተገንዝቦ በሚሰጠው ትንንሽ አጀንዳ አጨብጭቦ፣ ጮሆ በዛ ላይ እንዲሄድ የሚደረግበት ሴራ የማያዛልቅ የትም የማያደርሰው መሆኑን በማወቅ መንቃት መቻል አለበት። ሁልጊዜ መሸወድ የለበትም። አስራ ዘጠኝ ዓመት የተለያዮ አጀንዳዎች ተሰጥተውታል። ሁሉም ግን በተጨባጭ በተግባር ምንድነው ሲባል ምንም ነው መልሱ። ከዓመት ዓመት ውድድር ማድረግ ከሆነ ስራ ይሄን ማድረግ ማንም ይችላል። ትንንሽ ክለቦችም እያደረጉት ነው። በጊዮርጊስ ደረጃ ግን ይህ አይመጥንም። ቢረፍድም ለአመራሮቹ ልቦና ሰጥቷቸው ከዚህ በኋላ ክለቡ በትክክለኛ መንገድ የሚሄድበት መንገድ ቢፈጠር መልካም ነው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!