ሶከር ታክቲክ | “በጥልቀት የሚከላከል ቡድን”ን ለመገዳደር…

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡

ጸሃፊ– ጄክ አስካም

ትርጉም
– ደስታ ታደሰ

አንድ ቡድን ወደ ራሱ የግብ ክልል እጅጉን ተጠግቶ በጥልቀት ሲከላከል የቡድኑ አብዛኞቹ ተጫዋቾች በጨዋታው የመከላከል ሒደት ወቅት ሊሸፍኑ የሚጥሩት በሜዳው ቁመት ያለውን የመሃል ክፍል ይሆናል፡፡ ይህ ውሳኔ ደግሞ ተጋጣሚ ቡድን በደንብ ሊጠቀምበት የሚችለውን ክፍት ቦታ በሜዳው ስፋት ስለሚያስገኝ ባላጋራን የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ባለፉት አሥርት ዓመታት ባርሴሎናዎች ስኬታማ ከሆኑባቸው ዓብይ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የተጋጣሚ ቡድኖችን ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት በቀላሉ ማስከፈት መቻላቸው ነው፡፡ይህንን የሚያደርጉበት አንዱና ዋነኛው መንገድ ደግሞ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል እና ዙሪያ ባሉ ቦታዎች ላይ በከፍተኛ ፍጥነት በሚያደርጓቸው የቅብብል ሽግግሮች ነው፡፡ እንደ ኤኒየሽታ፣ ሜሲ፣ ኔይማርና ሱዋሬዝ ያሉ የባርሴሎና ተጫዋቾች በከፍተኛ ጥድፈት ቅብብሎችን ስለሚከውኑ የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች በትክክለኛው ሰዓት ተገቢው የሜዳ ክፍል ላይ መገኘት አዳጋች ይሆንባቸዋል፡፡

ከላይ በምስሉ እንደሚታየው ኔይማር በአደገኛ ቦታ ላይ ኳስ በተቀበለበት ቅጽበት ጆርዲ አልባ ለቡድን አጋሩ የመቀባበያ አማራጭ ለመስጠት  የጎንዮሽ መስመሩን ታኮ ወደፊት በመደረብ እየሮጠ ስፋት (Width) ይፈጥራል፡፡

ጆርዲ አልባ በአደገኛ ቦታ ኳስ ይቀበላል፡፡ በዚህችኛዋ ቅጽበት ሜሲና ራኪቲች በርከት ባሉ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ቢከበቡም መጠነኛ ክፍተት በሚገኝበት የሳጥኑ ክልል ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ እዚህ ጋር በጥልቀት ማስተዋል የሚገባን ጉዳይ የአትሌቲኮ ማድሪድ ተጫዋቾች እይታና የትኩረት አቅጣጫ “የት” እንደሆነ ነው፡፡ ሁሉም ተጫዋቾች ትኩረታቸው ጆርዲ አልባ ላይ አርፎ ሜሲን ዘንግተውታል፡፡ በዚህች ጊዜ ሜሲ ኳሷ እግሩ ሥር ብትገባ  ወደ የግብ ሙከራ ከማድረግ ወደኋላ አይልም፡፡

ኳስ ከጆርዲ አልባ እግር ሥር ወጥታ በአደገኛ ቦታ ለቆመው ሜሲ ደረሰች፡፡ አይምሬው ሜሲም ኳሷን በቀጥታ ወደ ግብነት ቀየራት፡፡ እናስተውል፦ በዚህ ቦታ ላይ ግብ ጠባቂውን ጨምሮ ዘጠኝ የአትሌቲኮ በጨዋታው የመከላከል ሒደት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች በሳጥን ውስጥ ቢኖሩም ሜሲ ጥቂት ክፍተት ማግኘትና ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ይህ የጨዋታ ቅጽበታዊ ናሙና በጥልቀት ለመከላከል ወደ ራስ የግብ ክልል በጣሙን ቨተጠግቶ የሚከላከል ቡድን ላይ እንዴት ያለ የማጥቃት አማራጭ መውሰድ እንደሚቻል ምርጡ ማሳያ ነው፡፡

እንደ ማናቸውም የታክቲክ መርሆዎች ሁሉ በጥልቀት የመከላከል ሥልት ጠቃሚ ገጽታዎችም ሆኑ ጎጂ ጎኖች አሉት፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት የተለያዩ ቡድኖች ይህንኑ የመከላከል አጨዋወት እየተከተሉ ስኬታማ መሆን ችለዋል፡፡ የጨዋታው ዘይቤ ማራኪ ባይሆንም በጥንቃቄ ሲተገብሩት አዋጭ እንደሆነ ታይቷል፡፡ አትሌቲኮ ማድሪዶች በላሊጋው ከኃያላኑ ሪያል ማድሪዶች እና ባርሴሎናዎች ጋር ለመፎካከር ይኸው በጥልቀት የመከላከል ዘዴ በእጅጉ አግዟቸዋል፡፡


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡