የሰማንያዎቹ… | የእርሻ ሠብሉ ኮከብ ጸጋዬ ኪዳነማርያም የእግርኳስ ሕይወት

አስር ቁጥር ለባሽ ነው። የግራ እግር ጥሩ አጥቂ እንደሆነ ይነገርለታል። በእርሻ ሠብል አይረሴ አስራ ሦስት ዓመታትን ያሳለፈው የሰማንያዎቹ ኮከብ የወቅቱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የዛሬው እንግዳችን ነው።

ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን አቅጣጫ መቐለ ከተማ ልዩ ስሙ ባሎኒ አካባቢ የዛሬው የሰማንያዎቹ ኮከብ እንግዳ ተወለደ። ከመኖርያ ቤቱ ሃያ ሜትር ርቀት አንድ ሜዳ መገኘቱ ከልጅነት እስከ ጉልምስና በእግርኳስ ተስቦ ከተጫዋችነት እስከ አሰልጣኝነት አሻግሮታል። እግርኳስን በጣም ከመውደዱ የተነሳ ጠዋት ወጥቶ ሲጫወት ውሎ ማታ ወደ ቤቱ ይገባ ነበር። በተለይ አብሮ አደጉ ከሆነው ገብረመድኅን ኃይሌ ጋር በዚህ ሜዳ ሲጫወቱ ማደጋቸው ይነገራል። ይህ በርካታ ወርቃማ ትውልዶችን ማፍራት የቻለው ሜዳ በአሁኑ ወቅት የማሻሽያ ሥራዎች እየተሰራበት ይገኛል። ለከፍተኛ አንድ ለሦስት ዓምት ከተጫወተ በኃላ ወደ ባህርዳር በመምጣት ለከፍተኛ ሲጫወት ያደገው ፀጋዬ ኪዳነማርያም ወደ ባህር ዳር በማቅናት ከጨርቃጨርቅ ቡድን እስከ ጎጃም ምርጥ ድረስ መጫወት ችሏል። በወቅቱ ከፍተኛ ወርሐዊ ደሞዝ እና የመንግስት ሠራተኝነት ተጨምሮ በ1977 እርሻ ሠብልን ተቀላቅሏል። ምንም እንኳን እርሻ ሠብል እስከ ፈረሰበት ጊዜ ድረስ በዋንጫ የታጀበ ታሪክ ባይኖረውም በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ክለቦች በጠንካራ ተፎካካሪነቱ፣ በማራኪ የጨዋታ ዘይቤው እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን በማስመረጥ ይታወቃል። አስራ ሦስት ዓመት በእርሻ ሠብል የቆየው ፀጋዬ አንበል በመሆን ጭምርም ክለቡን አገልግሏል።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ብዙ ጊዜ እየተመላለስ የተጫወተው ጸጋዬ ለተከታታይ ዓመት በቋሚነት ብሔራዊ ቡድኑን ማገልገል ባይችልም በተለይ በወጣት ቡድን የተሻለ ተሳትፎ እንዳደረገ ይነገራል። በዋና ብሔራዊ ቡድን ደረጃ በልዩ በሚታወሰው የ1980 ሴካፋ አሸናፊ ቡድን ውስጥ ከውድድሩ በፊት እስከ መጨረሻው ሰዓት በስብስቡ የነበረ ቢሆንም ጉዳት ማስተናገዱ ከስብስቡ ውጭ መሆኑ ሀገሩን በታሪክ አጋጣሚ ስሙን ለመፃፍ የነበረው ዕድል ሳይሳካ ቀርቷል።

አስራ ስድስት ዓመት በእግርኳስ ተጫዋችነት ቆይቶ እግርኳስን ካቆመ በኋላ ወደ አሰልጣኝነቱ መግባት ችሏል። በኢትዮጵያ እግርኳስ ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጎበት፣ ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት ብዙ እግርኳሰኛ እንደሚያፈራ በታመነበት ሀገር አቀፍ የታዳጊ ፕሮጀክት ውስጥ አርባ አሰልጣኞች ተመርጠው የአሰልጣኝነት ኮርስ ሲሰጥ በመውሰድ እና የአዲስ አበባ ፕሮጀክትን በማሰልጠን አሰልጣኝነቱ ጎራ በመቀላቀል የማሰልጠን ስራውን ሲጀምር በጎን ደግሞ በአሰልጣኝ ሰብስቤ ይበስ ጉትጎታ እና ድጋፍ በምክትል አሰልጣኝነት በከፍተኛ ዲቪዚዮን ይሳተፍ የነበረውን የታክሲ ቡድንን በመቀላቀል የአሰልጣኝነት ህይወቱን በ1990 ጀምሯል። ለሦስት ዓመት በታዳጊ ፕሮጀክት እና በታክሲ ቡድን ከሰራ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚገኙ ክለቦች የመሥራት ጉዞውን በ1993 የአብሮ አደጉ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ምክትል በመሆን በትራንስ ኢትዮጵያ ማሰልጠን ጀምሯል። በረዳት አሰልጣኝነት በቆየባቸው አራት ዓመታት ከፍተኛ ልምድ ካገኘ በኃላ ከ1997 ጀምሮ ወደ ዋና አሰልጣኝነት በመዞር ትራንስ ኢትዮጵያን፣ ሐረር ቢራን፣ ኢትዮጵያ ቡናን፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ፣ አርባምንጭ ከተማን፣ ወልዋሎን እና በቅርቡ ሀዲያ ሆሳዕናን ማሰልጠኑ ይታሰጥቶናል

በተጫዋችነቱ ዘመን ጸጋዬን የሚያውቁት እና ወደ አሰልጣኝነቱ እንዲገባ ከፍተኛውን አስተዋፆኦ ያበረከቱት አንጋፋው የስፖርት ሰው አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ ስለ ፀጋዬ ተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ሁኔታ ይሄን ይናገራሉ ” ፀጋዬ በተጫዋችነቱ አስር ቁጥር ማልያ በመልበስ ይታወቃል። በጣም ጥሩ የአጥቂ ሥፍራ ተጫዋች እና ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው እርሻ ሠብልን ለአስራ ሦስት ዓመት ያገለገለ ነው። ከእርሻ ሠብል ሲወጣ አሰልጣኝ እንዲሆን ከኔ ጋር ምክትል በመሆን ከታክሲ ቡድን ጋር ሠርቷል። ፀጋዬን አሰልጣኝ እንዲሆን የፈለኩበት ምክንያት ጎበዝ ተጫዋች ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ከተጫዋቾች ጥሩ የመናገር ችሎታ የነበረው፣ ከአንደበቱ የሚወጡ ቃላቶች አስተዋይ መሆኑን አንዳንድ ነገሮችን የሚገልፅበት መንገድ ጥሩ ስለሆነ ይህ ልጅ ወደ አሰልጣኝነቱ ቢገባ የበለጠ ጥሩ ነገር ሊሰራ ይችላል እርሱም ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለነበረ በዚህ መልኩ እንዲሰራ አበረታታው የነበረ። አሁንም ትልቅ ደረጃ ደርሶ ማየቴ በጣም ያስደስተኛል ብለዋል”።
በሚሌኒየሙ መጀመርያ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ በመሆን የሠራው የቀድሞ የሰማንያዎቹ ኮከብ ተጫዋች የወቅቱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ላቀረብነው ጥያቄዎች ተከታዮን ምላሽ ሰጥቶናል

“ለእኔ በእግርኳስ ህይወቴ ከዋንጫ ጋር ወይም በኮከብ ተጫዋችነት ይህ ነው የምለው ስኬት ባይኖረኝም ጥሩ የእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወት አሳልፌለው። በጎጃም ምርጥ፣ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከእርሻ ሠብል ጋር ሁለተኛ ደረጃ ይዘን የጠናቀቅንበት ዘመን ነበር። ብዙዎች በዚህ ዘመን የሚገኙ ትውልዶች በአሰልጣኝነት ቆይታዬ ቢያቁኝም ተጫዋች በነበርኩበት ዘመን ለትላልቅ ቡድኖች ፈተና የሆነ ቡድን ውስጥ ተጫውቻለው። በአሰልጣኝነት ህይወቴም በትልልቅ ቡድኖች አሰልጥኛለው። በፕሪምየር ሊግ ከዋንጫ ጋር የተያያዘ ታሪክ ባይኖረኝም ከንግድ ባንክ ጋር የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ያሳካሁበት ሐረር ቢራን ጠንካራ የሆነ ቡድን የሰራሁበት ጊዜ አስደሳች ነበር።

“የምቆጭበት ነገር የለም። ዕድሜዬን ሙሉ በምወደው እግርኳስ ውስጥ ቆይቻለው። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት በተጫዋችነትም በአሰልጣኝነትም በምችለው አቅም የራሴን አስተዋፆኦ አድርጌያለው። ስለዚህ ይሄን አላደረኩም ብዬ የምቆጭበት ምንም ነገር የለም።

“እርሻ ሰብል ጠንካራ ተፎካካሪ ነበር። ክለቡ ምንም እንኳ በርካታ ዋንጫዎች ባያነሳም በተፎካካሪነት ደረጃ ግን ጠንካራ ተፎካካሪ ነበር። በክለቡ ብዙ ትላልቅ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ነበሩ። ይህ ታሪካዊው ክለብ እርሻ ሰብል መፍረሱ በጣም ይሰማኛል። አስራ ሥስት ዓመት የተጫወትኩበት ብዙ ጥሩ ጊዜያት ያሳለፍኩበት ክለብ እንዲህ ደብዛው ሲጠፋ ያሳዝናል። እርሻ ሰብል የተጫወትን ተጫዋቾች በየጊዜው እንገናኛለን። በህይወታችን ትልቅ ቦታ ያለው ህይወታችን የቀየረ ክለብ ስለሆነ በመፍረሱ ሁላችንም እናዝናለን።

“ወደ አሰልጣኝነቱ የገባሁበት አጋጣሚ…
እግር ኳስ መጫወት በ1990 ነው ያቆምኩት። በወቅቱ መጫወት ያቆምኩበት ምክንያት ወደ ስልጠናው ለመግባት ነው። በጊዜው ሃገራዊ የታዳጊ አሰልጣኞች ስልጠና ነበር። እኔም ዕድሉን ተጠቅሜ ከሌሎች አርባ አሰልጣኞች ጋር በመሆን ሰልጥኜ ወደ ስልጠናው ገብቻለው። በዛ ዓመት በታዳጊዎች ስራ ብጀምርም ጎን ለጎን ደግሞ ከአሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ ጋር የታክሲ ቡድን ውስጥ እሰራ ነበር። አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስም ወደ አሰልጣኝነት በደምብ እንድገፋበት ከረዱኝ አንዱ ነው። በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለው።

“የዋና አሰልጣኝነት ግዜ በ1993 በፕሪምየር ሊግ ደረጃ በረዳትነት ሰርቻለው። በትራንስ ኢትዮጵያ የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ምክትል ነበርኩ። ከዛ ለዓመታት በረዳትነት ልምድ ካገኘሁ በኃላ ከ1997 ጀምሮ በዋና አሰልጣኝነት ማሰልጠን ጀመርኩ። ወደ ሐረር ቢራ አመራሁና ከ1999 እስከ 2004 የሐረር ቆይታ በኃላ 2005 ለትምህርት እስከሄድኩበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ቡና አሰልጥኛለው። ከዛ በኃላ ንግድ ባንክ አራት ዓመታት ቆይቻለው። በ2011 አርባምንጭ ለጥቂት ጊዜ ቆይታ ነበረኝ ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ ደግሞ ወልዋሎ እስከ ቀጣይ ዓመት አጋማሽ አሰልጥኛለሁ። በተቋረጠው የውድድር ጊዜም ከሀዲያ ሆሳዕና ቆይታ አድርግያለሁ።

“ያገኛቸው የአሰልጣኝነት ኮርሶች ብዙ ናቸው። ከታዳጊ እግርኳስ ስልጠና እስከ ፊፋ ከፍተኛ ደረጃ ስልጠናዎች ወስጃለው። ከ C B A ላይሰስ ድረስ አለኝ በፖላንድ ሀገር የሦስት ወር እንዲሁም በሞሮኮ የወሰድኳቸው ስልጠናዎች አሉ። ከዚህ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በውጭ ሀገር በሚመጡ አሰልጣኞች የተሰጡ የተለያዩ ኮርሶችን ወስጃለው።

“የንግድ ባንክ መፍረስ ምክንያቱ የክለቡ አመራሮች ናቸው። የመጀመርያዎቹ ሦስት ዓመታት የመውረድ ሥጋት የሌለበት በጣም ጥሩ ጠንካራ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቅ ቡድን ሰርቻለው። ሆኖም ግን የመጨረሻው ዓመት ላይ የክለቡ ኃላፊዎቸ ቡድኑ በታዳጊ ማዘጋጀት እንዳለብኝ ተነገረኝ እንደምታቁት በታችኛ ቡድን በመጡ ወጣቶች እንደ አዲስ ቡድኑን አዘጋጅቼ ወደ ውድድር እንድገባ ተደረገ። ሊጉን አያቁትም እስኪዋህዱ ድረስ ጊዜ ይፈልጋል። ያም ቢሆን የሚያስከፋ ውጤት አልነበረንም ከመሪዎቹ የነበረን ርቀት የሁለት ነጥብ ነበር። አስራ አምስት ጨዋታ እንደተጫወትኩ ገና ብዙ ጨዋታ እየቀረ ጊዜ ሊሰጡኝ እና ቡድኑን አጠናክሮ በሁለተኛው ዙር መቅረብ ሲገባ በስሜታዊነት ከእኔ ጋር ሊለያዩ በመቻላቸው በቀሪው ጨዋታ እንደምታቁት ቡድኑ ሊወርድ ችሏል። ይሄን ያህል የሚያስከፋ ውጤት አላስመዘገብኩም ነበር። ሆኖም የመጀመርያው ስህተት በአንዴ ቡድኑን በታዳጊዎች የመቀየር ሥራው ዋጋ ያስከፈለ ይመስለኛል። በታዳጊዎች ቡድኑን ማዋቀር ተገቢ ቢሆንም በሒደት ቀስ በቀስ ማድረግ እየተሻለ ሁሉም ነገር ባአንዴ መጀመርግን አይገባም ነበር። በእርግጠኝነት ብቆይ ኖሮ ቡድኑን ካለኝ ልምድ የተነሳ እንዳይወርድ ማድረግ የምችልበት ጊዜ ነበር። ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ሊወርድ ችሏል።

“እንደ አሰልጣኝ መሥራት የምፈልገው እና የምከተለው አጨዋወት በጠም ጠንካራ ዘጠና ደቂቃ መጫወት የሚችል፣ በፍጥነት የሚያጠቃ፣ ለተቃራኒ ቡድን ክፍት የማይሰጥ ፣ በቀላሉ ጎል የማይቆጠርበት እና በተደራጀ መከላከል (በጥብቅ የሚከላከል) ቡድን መስራት ነው።

” በተደጋጋሚ በሄድኩባቸው ክለቦች አብረውኝ የሚሄዱ ተጫዋቾችን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ጥያቄ ይነሳል። ይህ መሆኑ በየትኛውም ዓለም የተለመደ ነው። እኔ ቡድን አፍርሼ ቡድን የመገንባት ስትራቴጂ አይደለም ያለኝ። አራት አምስት የማይሞሉ ልጆች እኔ በሄድኩበት ክለብ አብረውኝ ሄደዋል። ይህን የማደርገው ልጆቹ አቅም ያላቸው፣ ዲሲፒሊንድ ስለሆኑ እና ከእኔ ፍላጎት እና አጨዋወት ጋር ስለሚሄዱ ብቻ ነው ይዣቸው የምሄደው።

“ከንግድ ባንክ እና ከሐረር ቢራ በኃላ በአንድ ክለብ ረዘም ላለ ጊዜ ተረጋግቼ ያለመሥራቴ ምክንያት ክለቦች በጊዜያዊ ውጤት ተፅዕኖ መግባት እና ጊዜ አለመስጠት ነው። ይህ እኔ ብቻ ሳልሆን በዚህ ዘመን የምንገኝ አሰልጣኞች ፈተና ነው። አንድ ቡድን ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ለአሰልጣኝ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል። ሮም ባንዴ አልተገነባችም። አሁን አሁን በአመራሮች በኩል ውጤትን (ማሸነፍን) ብቻ ፈልገው አሰልጣኝ ያመጣሉ። ይሄ ካልተሳካ ማሰናበትን ተለማምደውታል። ስለዚህ በቂ የሆነ ጊዜ ለአሰልጣኞች ሊሰጥ ይገባል።

“በቤተሰብ ህይወቴ ባለ ትዳር እና ሦስት ልጆች አሉኝ። የመጀመርያ ወንድ ልጄ ናትናኤል አንተም እንደምታቀው ከፍተኛ የእግርኳስ ፍቅር አለው። በጣምም ጎበዝ ተጫዋች ነው። ወደ ፊት ትልቅ ተጫዋች እንደሚሆን አስባለው። እኔም በደንብ እየተከታተልኩት እና እያገዝኩት ነው። ሁለተኛው ወንድ ልጄ ዳግም መጀመርያ አካባቢ ብዙም የእግርኳስ ፍቅር ያልነበረው ቢሆንም አሁን ግን እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን ከወንድሙ ጋር እየሠራ ነው። ወደ ፊት የሚሆነውን አብረን እናያለን። የመጨረሻዋ ሴት ልጄ ማርያማዊት ትባላለች። ባለቤቴም ቃልኪዳን ተስፋዬ ትባላለች። ለሥራዬ ትልቅ እገዛ የምታደርግልኝ አጋሬ ናት። አሁንም በወር አንዴ ቢሆንም የቀድሞ የእርሻ ሠብል ተጫዋቾች ማህበር አለ በዚህ ቡድን ውስጥ አልፎ አልፎ የጤና ጨዋታ እናደርጋለን።

“በቀጣይ ወደ አሰልጣኝነቱ መመለሴ አይቀርም ለተለያዮ ክለቦች ሲቪዬን አስገብቻለው። በቅርቡ በፕሪምየር ሊግ ክለብ ወደ አሰልጣኝነቱ እመለሳለው ብዬ አስባለሁ።

“በመጨረሻም በኢትዮጵያ እግርኳስ እንዲያድግ ከመጠላለፍ ፣ ከትችት እየወጣን በመከባበር በተባበር፣ በፍቅር መፍትሔው ላይ በማተኮር መስራት አለብን። ትችትም ቢሆን በእውቀት ቢሆን መልካም ነው። ክለቦችም በቂ የሆነ ጊዜ ለአሰልጣኞች ሊሰጡ ይገባል። ትግስት አልባ ያሰልጣኝ ቅጥር ቢቆም መልካም ነው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!