አፈወርቅ ኪሮስ እና ኃይሉ አድማሱ ስለአሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ

ዛሬ እየዘከርናቸው የምንገኘው ሐጎስ ደስታን የአሰልጣኝነት ባህሪ፣ የተጫዋቾች አያያዝ እና የቡድን አገነባብ ሂደት አስመልክተን ካሰለጠኗቸው ተጫዋቾች መካከል አፈወርቅ ኪሮስ እና ኃይሉ አድማሱ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በዚህ መልኩ እናስነብባችኋለን።

የአሰልጣኞችን የግል ስብዕናም ሆነ የሥራ ባህል ለመመስከር ከተጫዋቾች በላይ እማኝ ማግኘት ይከብዳል። አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች በዕለት ተዕለት የሥራ ግንኙነታቸው የሚያዳብሩት የመቀራረብ መንፈስ ማንነታቸውን በአግባቡ ለመረዳት በቀላሉ ይረዳቸዋል። በልምምድ እና በጨዋታ ላይ በውጤት ማጣት እና በደስታ ወቅት በሁሉም ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ አብረው ሲያልፉ አንዳቸው የሌላኛቸው ስራ የቅርብ ታዛቢ ፣ ፈፃሚ እና አስፈፃሚም ናቸው። የዚህ የእርስ በእርስ ግንኙነት መልካም መሆን ደግሞ የቡድን ስራውን አሳምሮ ለተሻለ ውጤት ማብቃቱ የማይቀር ነው። በዚህ ረገድ ዛሬ እየዘከርናቸው የምንገኘው አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታን በተመለከተ በስራቸው ከሰለጠኑ ተጫዋቾች አንደበት ስለሙያዊ ክህሎታቸው እንሰማ ዘንድ አስበን የ90ዎቹ ኮከቦች አፈወርቅ ኪሮስ እና ኃይሉ አድማሱን (ቻይና) ጋብዘናል።

የመብራት ኃይል ታላቅ ተጫዋች እና አምበል የነበረው አፈወርቅ ኪሮስ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በሚወደው ክለቡ ሲያገለግል ቆይቷል። አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ 1989 ላይ ክለቡን በአሰልጣኝነት ሲረከቡም ከቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። በተቃራኒው ኃይሉ አድማሱ ደግሞ በ1991 ወደ ዋናው ቡድን ያደገ እና በእሳቸው አሰልጣኝነት ዘመን በፍጥነት ወደ ወሳኝ ተጫዋችነት የተሸጋገረ ኮከብ ነው ። ምንም እንኳን በተክለሰውነቱ ደቃቃነት ብዙዎች ጥርጣሬ ቢገባቸውም በጋሽ ሐጎስ በተጣለበት ዕምነት ወደ ከፍታ የመጣው ኃይሉም ሆነ ቡድኑን በአምበልነት የመምራት ኃላፊነት የነበረበት አፈወርቅ እካሁንም ድረስ ያያኔው አሰልጣኛቸው ስም ካፋቸው አይወጣም። ከአሰልጣኝ ሐጎስ ህልፈት በኋላ የ1993ቱን የመብራት ኃይል በድሎች ያሸበረቀ ድንቅ የውድድር ዓመት አብረው የተቋደሱት ሁለቱ ተጫዋቾች አሁን ላይ በሀገር እና ከሀገር ውጪ ተራርቀው ቢገኙም የሚወዷቸውን አሰልጣኝ ይገልፃሉ ባልናቸው ጥያቄዎች በሀሳብ አገናኝተን ቀጣዩን ቆይታ ይዘንላችሁ ቀርበናል።

አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ የሚከተሉት የጨዋታ ዘይቤ ምን ይመስል ነበር ?

አፈወርቅ:- ብዙ ጊዜ 3-5-2ን ይከተላሉ። ሜዳ ላይም ይህን አሰላለፍ ይተገብራሉ፤ ልምምድ ላይ ትኩረት አድርገን የምንሰራው እሱ ላይ ነው። ነገር ግን ጋሽ ሀጎስ ጨዋታ የማንበብ ልዩ ችሎታ ነበረው። እና ተጋጣሚዎችን በማየት ሜዳ ላይ ጨዋታ የመቀየር ልዩ ብቃት ነበረው። አንዳንዴ ቡድኖቹን በማየት በ4-4-2 የሚያጫውተን ጊዜም ነበር።

ኃይሉ:- በፈጣን አጨዋወት ከራሳችን ሜዳ ወጥተን በተቃራኒ ቡድን ሜዳ ላይ በቁጥር በዝተን እንድንገኝ የሚያደርግ አጨዋወትን ይከተል ነበር። ይህንን ደግሞ ከሜዳ ውጪ በክፍል ውስጥ በልምምድ ላይ ደግሞ በሜዳ ውስጥ በጣም ረጅም ጊዜ ወስዶ ትኩረት ሰጥቶ የሚያሰራ አሰልጣኝ ነበር። በማጥቃት ላይ በነፃነት የመጫወት ዕድሉን ይሰጠናል። ልክ ግን ቡድናችን ኳስ ሲነጠቅ ሁላችንም ከኳስ ጀርባ ሆነን በኅብረት እንድንነጥቅ ነበር የሚያደርገው። እኔ ስሮጥ እኔን ተከትሎ የሚመጣ ሰው አለ። እኔን ቢያልፈኝ ቀጣዩ ሰው ይቀማዋል። እነአንዋር እና ተክሌ ዓይነት ሲኒየሮች ቢኖሩንም ከአንድ ለአንድ ይልቅ እንደቡድን እንድንጫወት የሚጋብዝ አጨዋወት ነበር የሚከተለው። እኔ ስሮጥ ዓለማየሁ ይከተለኛል፣ ዓለማየሁ ሲሮጥ እኔ እከተለዋለሁ፣ ሲቀጥል ተክሌ ይመጣል። አጨዋወታችን ለተቃራኒ ቡድን መረጋጋትን የሚሰጥ አልነበረም።

የቅድመ ውድድር የዝግጅት ጊዜያቸው እንዴት ዓይነት ነበር ? ምን ምን ጉዳዮች ላይስ አተኩረው ይሰሩ ነበር ?

አፈወርቅ:- እሱ በነበረ ሰዓት መልካዋከና ነበር የምንሰራው። ቦታው ትክክለኛ የዝግጅት ቦታ ነው። ልምምድ ከመሥራት እና አንድ ላይ ተሰብስቦ ቲቪ ከማየት ውጪ የትም መሄድ የሚቻልበት አልነበረም። ታስቦበት የተዘጋጀ ቦታ ነው ማለት ይቻላል። በልምምዱ ወቅት የራሱ የሆነ ፕሮግራም ነበረው። በብዛት በቀን ሁለቴ ነበር የሚያሳራን። በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በተለይ ጠዋት ላይ ጠንከር ያሉ ልምምዶችን ያሰራን ነበር። አንድ የማስታውሰው ነገር ከበድ ያለ ልምምድ ያሰራን እና በቀጣዩ ቀንም ያንን ስራ ስንጠብቅ የሚቀይረው ነገር ነበር። የተጫዋችን ወቅታዊ ሁኔታ በሚገባ ያያል። ከጋሽ ሐጎስ ጋር ልምምድ ስትሰራ በፍላጎት ነው የምትሰራው። አብረን በሰራንባቸው ጊዜያት ሁሉም ተጫዋች በፍቅር ሲሰራ ነው የማስታውሰው። ማንም ሲያማርር አይሰማም ነበር። አሰልጣኝ ሀጎስ ቡድኑን የሚሰራው መጀመሪያ ነበር። በልምምድ ወቅት ሜዳ ላይ ቀድሞ ነው የሚገኘው። ልምምዱንም በሥነ-ስርዓት ነው ያሚያሰራው። 7 እና 14 ኪ.ሜ ዓይነት ረጃጅም የሩጫ ልምምዶች እንኳን ሲኖሩ ሁሉም በፍላጎት እና በብቃት ነው የሚወጣው። በአጨዋወት ቦታችንም ጠዋት ተከላካዩን ለብቻ ከሰዓት ደግሞ አጥቂውን ለብቻ በነጋታው አማኮዮቹን ለብቻ አድርጎ የሚያሰራበትም ጊዜ አለ። ከዛ ደግሞ አቀላቅሎም ያሰራል። የሚያሰራበት መንገድ በጣም ደስ ይለኝ እና ሁሌ ይገርመኝ ነበር።

ኃይሉ:- ከጋሽ ሐጎስ ጋር ቅድመ ውድድር ዝግጅት የምንወጣው የመብራት ኃይል ግድቦች ያሉበት ቦታ መልካዋከና አካባቢ ነበር። ከአንድ ወር እስከ አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ድረስ እንቆይ ነበር። ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ከዕረፍት መልስ የሚገናኙበት ወቅት እንደመሆኑ በአግባቡ ለመጠቀም ይሞክር ነበር። አንድ ተጫዋች በአዕምሮ ፣ በቴክኒክ፣ በታክቲክ በአጠቃላይ በአጨዋወቱ በስሎ እንዲወጣ ክትትል ይደረግ ነበር። ስንገባ ሜዳ ላይ እንዳንቸገር መጀመሪያ የብርታት (Endurance) ሥራዎች ላይ ትኩረት ይደረግ ነበር። ከዚያ በኋላ ነበር ወደ ቴክኒክ እና ታኪቲካዊ ሥራዎች የምንገባው። በዚህ ውስጥ በቀን ሁለቴ የምንሰራባቸው ወቅቶች ነበሩ። አንድ ተጫዋች ሜዳ ላይ ብቁ እንዲሆን የሚያስችሉትን ነገሮች ካገኘ በኋላ የቡድን ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሁም በወዳጅነት ጨዋታዎች በማዳበር እሱ ቡድኑ ዝግጁ ነው ብሎ የሚያስብበት ጊዜ ላይ ዝግጅታችንን ጨርሰን ወደ አዲስ አበባ እንመለሳለን። ውድድሩ እስኪጀምርም በቡድን ሥራዎች እና በጨዋታዎች ላይ እንቆያለን።

የአንድ ለአንድ የተጫዋቾች አያያዛቸው ምን ይመስል ነበር ?

አፈወርቅ:- ይሄ ይመስለኛል ሥራውን ቀላል ያሚያደርግለት። እያንዳንዱን ተጫዋች ከሌላው አያስበልጥም። ለሁሉም እኩል አክብሮት ነበረው። ሁሉንም በፍቅር ይቀርባል። በዚህ መንገድ ሁሉም ደስ ብሎት ወደ ልምምድ እንዲመጣ ስለሚያደርግ የፈለገውን አይነት ነገር ማሰራት ይችላል። በዚህ ሁኔታ ከባዱን ነገር ቀላል ያደርገዋል። ይሄ በራሱ ተሰጥኦ ነው የሚመስለኝ። ይህ ችሎታው ለሚወስነው ውሳኔ እና ለአጠቃላይ ሥልጠናው ብዙ ነገር ቀላል አድርጎለታል። ምንም የተደበቀ ነገር የለውም ሁሉም ነገር ፊት ለፊት ነው። ሁሉም ነገር እዛው ጋር ነው በንግግር ነው የሚያልቀው። በዚህ ረገድ ማንም ሰው የሌለው ተሰጥኦ እሱ ጋር እንዳለ አስባለሁ። ወደተጠባባቂነት የሚወርድ ተጫዋች እንኳን ሲያማርር አትሰማም። የአሰልጣኝ ሀጎስ የተጫዋች አያያዝ የተለየ ነበር። ችግር ያለበት ተጫዋች ሲኖር ለብቻ ጠርቶ አናግሮ የቡድኑን ማንፈስ ሳይረበሽ የሚመልስበት መንገድም ይገርመኛል። የስልጠና ብቻ ሳይሆን የብዙ ነገር ተሰጥኦ ነበረው። ስህተት እንኳን አይቶ እንዳላየ አልፎ ነገሮች ካለፉ በኋላ ቆይቶ ባላሰብከው ሰዓት ያወራህና ነገሩን እዛው ጋር ይጨርሰዋል።

ኃይሉ:- ይሄ የጋሽ ሐጎስ መለያው ነው፤ ከአሰልጣኝነቱ በላይም አባትነቱ ይጎላ ነበር። ለሲኒየሮቹም ለእኛም እኩል ሰው ነበር። ይኖር የነበረው ደብረዘይት ነበር። ልምምድ ብዙ ጊዜ አራት ሰዓት ነው የምንጀምረው ፤ ብዙ ጊዜ ቁርስ ሰዓት ላይ ነበር የሚመጣው። አንድም ቀን በሳህን ምግብ ይዞ ሲበላ አይቼው አላውቅም። ሹካ ይይዝ እና ከእኛ ላይ ይቀማምሳል። ሲቀምስ ስለልምምድ ስለቤተሰብ መሰል ነገሮችን ያወራናን። ይሄንን በየጠረጵዛው እየዞረ ቆሞ እያወራ ሁሉም ጋር ያደርገዋል። ‘ምን በላህ ምን ጠጣህ ?’ እንደሚል እንስፍስፍ አባት ነበር። ብቻህንም ሲያገኝህ ብዙ ይመክርሀል። ኳስ ጨዋታ ጥልቅ እንደሆነ ፣ ወደፊት ተረጋግተህ ብዙ ነገር ማድረግ እንደሚገባህ ፣ የኳስ ተጫዋችነት ዘመን አጭር መሆኑን እና የወደፊት ህይወትህንም የምታስተካክልበት መሆን እንደሚገባው እያሳየ መንገድ የሚያሲይዝ አሰልጣኝ ነበር።

ከታችኛው ቡድን ያደጉ ታዳጊዎች በራስ መተማመን እንዲኖራቸው የሚያደርጉት በምን መንገድ ነበር ?

አፈወርቅ:- ሁሉንም በእኩል ማየቱ ታዳጊዎችም በፍላጎት እና በተስፋ ነገሮች እንደሚቀየሩ እያሰቡ እንዲሰሩ አድርጓል ብዬ አስባለሁ። ታዳጊ እና ነባር የሚለው ሀሳብ ቡድኑ ውስጥ እስከገባህ ድረስ እሱ ጋር ልዩነት የለውም። የተሻልክ ሆነህ ከታየህ ዕድሉን ይሰጥሀል። ታዳጊዎችም ሲመጡ የመጫወት ተስፋ እንዳላቸው አምነው ነበር የሚመጡት። ከነባሮቹም ጋር ሲጫወቱ አዲስነታቸው ተፅዕኖ እንዳይፈጥርባቸው አድርጓል። ድፍረት ኖሯቸው እንደፈለጉት ችሎታቸውን እንዲያሳዩ ጋሽ ሐጎስ የሚሰጣቸው ነገር በጣም ይረዳቸዋል። እዚህ ቦታ ላይ የአሰልጣኞች ሚና በጣም ወሳኝ ነው ፤ የእሱ ደግሞ የተለየ ነው ብዬ አስባለሁ። ልምምድ ላይ እንኳን ታዳጊው ጥሩ ነገር ሲያሳይ እዛው ወደ ዋናው ስብስብ ውስጥ ለውጦ በማስገባት የሚያጫውትበት ነገር ይገርመኝ ነበር። ይህ ደግሞ እርስ በእርስ ውድድር ውስጥ እንዲገቡ እና እንዲነሳሱ እገዛ አድርጎላቸዋል። በታዳጊዎች ላይ የነበረው ዕምነት ተጫዋቾቹን ብዙ ነገር እንዲቀልላቸው አድርጓል።

ኃይሉ:- ጋሽ ሐጎስ የሚለይበት አንዱ ነገር የ’ሲ’ን ጨዋታ ያያል ፣ የ’ቢ’ን ጨዋታ ያያል። አበበ ቢቂላ ቢሆን ፣ አቃቂ ቢሆን ፣ ጃን ሜዳ ቢሆን ጋሽ ሐጎስ የትኛውም ቦታ ላይ ቢሆን ይገኛል። በዛ ደረጃ የሚጫወት ልጅ በጋሽ ሐጎስ መታየቱ በራሱ ልበ ሙሉ ያደርገዋል። እሱ በተደጋጋሚ አይቶህ ጥሩ ከሆንክ በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን መጥተህ ልምምድ እንድትጀምር ነው የሚያደርገው። እንደሚኖርህ አቅም ልትጫወትም ላትጫወትም ትችላለህ። ነገር ግን ልምምድ አብረህ በመስራትህ ብቻ አቅምህን ከፍ ያደርገዋል። የራሱን የረጅም እና የአጭር ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ይዞ ይሄዳል። ከታች ለሚመጡ ተጫዋቾች በተለየ ከኳስ ጋር የተያያዙ ብዙ ስራዎችን እንዲሰሩ ይደረጋል። የመጫወት ጊዜህ ደርሷል ብሎ ሲያስብ ደግሞ ዕድሉን ይሰጠሀል። ለምሳሌ እኔ 1991 ላይ ነበር ያደግኩት፤ እየተቀየርኩ እገባ ነበር። 1992 ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ በነበረ ውድድር ሁሉንም ጨዋታዎች ተጫውቼ ከጊዮርጊስ ለፍፃሜ ደርሰን። ለጨዋታው ስንዘጋጅም አሰላለፍ የሚፅፍበት ቦርድ ላይ ስሜ አልተፃፈም። ከዚያ ስለጨዋታው ያለውን ሀሳብ ነግሮን ከጨረሰ በኋላ ጠራኝና ጨብጦኝ ‘ስምህን እዛ ጋር ፃፍ’ አለኝ። ‘ዛሬ አንተ ጥሩ ከሆንክ ዋንጫውን ይዘን ወደ ሜክሲኮ እንሄዳለን’ አለኝ። ተደራቢ አጥቂ አድርጎ ያጫውተኝ ስለነበር ከተቃራኒ ቡድኑ የተከላካይ አማካይ ጋር እገናኝ ነበር። ‘አንተነህ አላምረው ግዙፍ ነው አይደል? በኳስ ግን ካንተ ጋር በፍፁም አይገናኝም። ገብተህ በነፃነት ልምምድ ላይ የምታደርጋቸውን ነገሮች እንድታደርግ ነው የምፈልገው’ ብሎ አስገባኝ። እንዲህ ተብለን ነበር ስንጫወት የነበረው። እንዲህ ተብሎ ገብቶ አለመጫወት ደግሞ ከባድ ነው ! በዚህ ደረጃ ነበር ያነሳሳን የነበረው።

በጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ ቡድንን የሚመሩበት መንገድ ምን ይመስል ነበር? ውሳኔዎቻቸውስ ምን ያህል ጨዋታን ይቀይሩ ነበር ?

አፈወርቅ:- በአስልጣኝ ሐጎስ የጨዋታ ንባብ ያሸነፍንባቸው ወቅቶች ብዙ ናቸው። ብዙ ጊዜ በዕረፍት ሰዓት መቀየር የሚፈልገውን ነገር በግል ከአንድ ተጫዋች ጋር ወይም ደግሞ እንደቡድን ይጨርሳል። ከሁሉም ጋር መልካም ግንኙነት ስላለው ይሄን ማድረግ ለእሱ በጣም ቀላል ነው። በጣም ብዙ ጊዜ እሱ በቀየረው ስትራቴጂ አሸንፈን ወጥተናል። በጨዋታ መልዕክቶችን በተጫዋቾች በመላክ የቀየሯቸው ጨዋታዎች ነበሩ። ይህ ግን ሜዳ ላይ ብቻም ሳይሆን ከሜዳም ውጪ ነው። አንዴ ታመው ሆስፒታል በነበሩ ጊዜ ከቡና ጋር ትልቅ ጨዋታ ነበረን። እና ከሆስፒታል ሆኖ እንዴት መጫወት እንዳለብን እና እኔም ቡድኑን እንዴት መምራት እንዳለብኝ መልዕክት ላከልኝ። ብዙም እርግጠኛ ባልሆንበትም የተባልኩትን ለማድረግ ሞክሬ ጨዋታውንም አሸነፍን። በጣም በጥሩ ሁኔታ ነበር ያሸነፍነው። ከዚያም እንደጋና ሌላ የምስጋና መልዕክት ላከልኝ። ‘ያልኩህን በሙሉ አድርገሀል በጣም ነው የማመሰግንህ’ የሚል መልዕክት ላከልኝ። በጣም ነው ደስ ያለኝ። አይደለም ሜዳ ላይ ሆኖ ከሜዳ ውጪም ጨዋታን መቀየር ይችላል። ተጫዋቾችም የእሱን ትዕዛዝ ለመተግበር የነበራቸውን ተነሳሽነት ስትመለከት ያስገርማል።

ኃይሉ:- ጋሽ ሐጎስ የሚጮኸው፣ የሚቆጣው የሚለፋው ልምምድ ላይ ነው፤ ጨዋታ ላይ የተረጋጋ ነው። እኔ ከጋሽ ሐጎስ የወሰድኩት አንድ ነገር ታማኝነቱን ነው። ሜዳ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ በጣም በጥልቀት ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል። በተደጋጋሚ ዕድል ይሰጣል ፤ ያን ዕድል ካልተጠቀምክበት አሰላለፍ ሳይወጣ በፊት ነው ተጠባባቂ መሆንህን የምታውቀው። ገና ልምምድ ላይ ‘ቻይና እሱን ቢብስ አውልቅ እና ለእከሌ ስጠው’ በማለት ለሚፈልገው ሰው ያሰጣል። በሚታይ እና በሚያሳምን መልኩ ነው የሚያደርገው። ሜዳ ላይ ቡድን ሲመራ ቁጭ ብሎ ነው። ጨዋታውን በደንብ አድርጎ ይከታተላል። በተወሰነ መልኩ ጨዋታ ሲቆም ተነስቶ መልዕክት ያስተላልፋል እንጂ ቆሞ ሲጮህ የሚታይ ሰው አልነበረም ጋሽ ሐጎስ።

በአመዛኙ በዚህኛው ዘመን ሲተገበሩ የሚታዩ የአሰለጣጠን መንገዶች ነበሯቸው ይባላል። ስለዚህስ ምን ትላላችሁ ?

አፈወርቅ:- በህይወት ስናጣው ኢትዮጵያ በሙያው ትልቅ ሰው እንዳጣች ተሰምቶናል። ምክንያቱም እሱ በጣም አስፈላጊ ሰው ነበር። እግርኳስን በአግባቡ የሚተገብር ሁለገብ ሰው ነበር። ልምምዶቹን እንዲሰለችህ ሳይሆን እንድትወደው አድርገው የማሰራት ብቃት ነበረው። ደስ ብሎህ እንድትመጣ እንጂ አመመኝ እያልክ እንድትቀር አያደርግህም። ሁሉም ሰው በፍላጎት መጥቶ ነው የሚሰራው። ሥልጠና ላይ የሚከተለውን ስትራቴጂ ተጫዋቹ በፍላጎት እንሲሰራ ማድረግ ያውቅበታል። ይህን ለማድረግ ከተጫዋቾች ጋር የነበረውን ግንኙነት በተለየ መንገድ አባታዊ እና በፍቅር የተሞላ ማድረጉ ከዘመኑ የአሰልጣኞች አቀራረብ ጋር የሚሄድ ይመስለኛል።

ኃይሉ:- ጋሽ ሐጎስ የእውነት ያለጊዜው የኖረ ሰው ነው። በጣም ዘመናዊ፣ ሀቀኛ፣ በመነጋገር የሚያምን ሰው ነበር። ከሌላ ሰው እንኳን ምንም ነገር ስላንተ ቢሰማ ሲያገኝህ በግልፅነት ራስህን ነው የሚጠይቅህ። ወደ ሥልጠናው ስመጣ ያኔ ግብ ጠባቂዎቹ በለጠ ዋዳጆ ፣ ፀጋዘአብ አስገዶም እና ዳንኤል ነበሩ። በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ኳስ እንዲጠልዙ የሚፈልግ ሰው አልነበረም። ከፊት ካሉት ሦስት ተከላካዮች አንዱን ከበረኛው ፊት ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ በደንብ ይሰበዋል። ሁለቱ ደግሞ አስፍተው ይቆሙ እና የሚመጡትን ሁለት አጥቂዎች አራት ለሁለት በሆነ የቁጥር ብልጫ ተቆጣጥረህ ኳስ መስርተህ እንድትወጣ ያደርግ ነበር። ይህን የመሰሉ አሁን ላይ ያሉ የእግርኳስ ሀሳቦችን በዚያን ወቅት ይተገብር የነበረ ባለሙያ ነው።

በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ የነበረው የአሰልጣኝ ሐጎስ ባህሪ ምን ይመስል ነበር ?

አፈወርቅ:- ያዘዘህን ነገር ሳታደርግ ስትቀር ጋሽ ሐጎስ ቁጡ መሆኑን ልታይ ትችላለህ። ነገር ግን የአባትነት ቁጣ ነው፤ ወደሌላ ነገር አይወስድህም። ለምን እንደተቆጣህ ትረዳዋለህ። ከተወሰነ ደቂቃ በኋላም ቁጣውን አታየውም ወደነበረበት ይመለሳል። ነገሮችን ቶሎ የሚቀይርበት መንገድ ይገርመኛል ፣ የተቃራኒ ቡድንን በማየት የሚቀይርበት መንገድ ፣ በተጫዋች ቅያሪ ጨዋታው ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩበት መንገድ፣ ጥሩ ተጫዋቾች ደከም ሲሉም ጠርቶ አናግሮ እንዲስተካከል የሚያደርግበት መንገድ ያለውን ትልቅ ተሰጥኦ ያሳያል። ጋሽ ሐጎስን በቀላሉ መግለፅ ከባድ ነው። የእሱን ማንነት በእኔ አንደበት ብቻ መግለፅ ከባድ ነው። የሚያሰራ ሰው የፈለገው ነገር ካልሰራህለት ሊቆጣ ይችላል ፤ የእሱ ልዩነቱ አይቆይም። ይሄ ይሄ ነገር የሚገርመኝ ባህሪው ነው።

ኃይሉ:- ጋሽ ሐጎስን ከሥራ ውጪም ስታገኘው በጣም የተረጋጋ ሰው ነው። ብዙ ያወራሀል፣ መንገዶችን ያሳይሀል። በተለይ አሰልጣኝ ይሆናሉ ብሎ የሚያስባቸውን ሰዎች መንገዱን ለማሳየት ይጥራል። በዋዛ በፈዛዛ የሚያሳልፈው ነገር የለም። ረጅም ጊዜ ቢሮ ውስጥ ተቃምጦ ይሰራል። የጤና እክል ከገጠመው ጊዜ ውጪ የሚያድርበትም ጊዜ ነበር። የእያንዳንዱ ሰው ስኬት ፣የህይወት መንገድ የሚያሳስበው ከባለሙያነቱ ባላይ ትልቅ አባት ነበር።

1992 ላይ በሲኒየር ተጫዋቾቹ ቦታ ለወጣቶቹ ዕድል የሰጡበት ወቅት ሽግግር እንዴት ነበር ? ሲኒየሮችን ማሳመን፣ ታዳጊዎችን ማብቃት ላይ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር ?

ኃይሉ:- እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ይከታተል ስለነበር ‘ሲ’ ላይ ማን አለ ? ‘ቢ’ ላይ ማን አለ የሚለውን እያንዳንዱን ነገር በሚገባ ያውቀው ነበር። ስለዚህ ጉድለት ሲኖር አቅም ያለውን ሰው ወደ ዋናው ቡድን ይወስዳል። 1990 ላይ ቻምፒዮን ሆኖ በቀጣዩ ዓመት ግን በሚፈልገው መንገድ ቡድኑ እየሄደ አልነበረም። በጣም የሚገርመኝ በጣም ወሳኝ የነበሩት እነኤልያስ ጁዋር ፣ አክሊሉ ገብረማርያም (ዩዞቢዮ) ፣ ይልማ ደበሌ ፣ ሲሳይ ተሰማ ፣ ያሬድ ከበደ ፣ በለጠ ወዳጆ ናቸው የተቀነሱት። እዛ ለነበርነው ሰዎች ራሱ በፍፁም የማይጠበቅ ውሳኔ ነበር ፤ በጣም ያስደነግጣል። ግብ ጠባቂ ላይ እነፀጋዘአብ አሉ ፣ ተከላካይ ላይ አፈወርቅ አለ ፣ አማካይ ላይ አንዋር ከዛ በተረፈ ያሉት ተጫዋቾች በቂዎች ናቸው ነበር የሚለው። እኔ ከዚህ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ኳስ ጨዋታ ላይ አንድ አሰልጣኝ በትልቅ ደረጃ ኃላፊነት ሊወስድ እንደሚገባው ነው። እሱ በመረጠው መንገድ ሲሄድ ኃላፊነት መውሰድ የት ደረጃ ይደርሳል የሚለውን በጋሽ ሐጎስ ውስጥ አይቼዋለሁ። እኛ ገብተን እንድንጫወት ቅድም እንዳልኩት ልምምድ ላይ በጣም ያሰራን ነበር፣ በጣም ያወራን ነበር፣ እንደጓደኛ ነበር፣ አቅም እንዳለን ይነግረን ነበር። ዕድሉን ሲሰጠን ደግሞ እነሱ የሰሩትን ታሪክ አይተን በዛ መንደርደሪያነት የራሳችንን ታሪክ ለመስራት ጥረናል። መብራት ኃይል ደግሞ በተለየ ሁኔታ ለህፃናት ዕድል ይሰጥበት ነበር። እነሱም በዛ መንገድ ስለነበር ያለፉት ያውቁታል። ይመስለኛል በዛ መስመርም ስላለፉ ይረዱታል። ኳስ ጨዋታ ደግሞ የዕድሜ ገደቦች አሉት። አሁን ላይ ቢሆን ኤልያስ በከዘራም ይጫወት ነበር ፤ ማንም አይነካውም የእውነቴን ነው። በዚህ ሰዓት ቢኖር ምንም አድርገህ አትነካውም። ያኔ ራሱ ቢቆይ የመጫወት አቅሙ ነበረው። ግን ጋሽ ሀጎስ ከዚህ በኋላ ከቆዩ ቡድኑ ምንም ዕድገት አይኖረውም ስለዚህ ታች ላሉት ልጆች ዕድሉ ይሰጣቸው ነበር ያለው።

በ1993ቱ የቡድናችሁ ጉዞ አሰልጣኝ ሐጎስ በህይወት አለመኖራቸው የነበረው የሥነ-ልቦና ጫና ወይም ስማቸውን ለማስጠራት የነበረ ተነሳሽነት ምን ይመስል ነበር ?

አፈወርቅ:- ከእሱ ህይወት ማለፍ በኋላ ስሜታችን ተጎድቶ ነበር። ዋንጫውን አንስተን የእሱን ስም እስከመጨረሻው ማስጠራት ያለምንም ንግግር እያንዳንዱ ተጫዋች ፊት ላይ ይታይ ነበር። ሁሉም በሰዓት ይገኛል በፍላጎት ይሰራል። ሁሉም ከውስጡ ለእሱ ክብር የሆነ ነገር ለመስራት እየታገለ እንደነበር ይታያል። በዛን ሰዓት ጉልላት ላይም ተመሳሳይ ስሜት ነበር። በምክትልነትም ከጋሽ ሐጎስ ጋር አብሮ ስለነበር የተጀመረውን ሥራ በዛው አስቀጥሎ 93 ላይ ሁሉንም ዋንጫ አምጥተናል። ይሄ ታሪክ በተነሳ ቁጥር የጋሽ ሀጎስም ስም አብሮ ይነሳል። ህይወቱ አልፎ እንኳን መንፈሱ ከእኛ ጋር ነበር። ዋና ተሰላፊው ብቻ አይደለም ተቀያሪው እና ከጨዋታ ውጪ ያለው ተጫዋች ደጋፊውም ጭምር ጋሽ ሐጎስ በህይወት እንዳለ ያህል እያሰበ ነበር ኃላፊነቱን የሚወጣው። ይሄ ደግሞ የጋሽ ሐጎስን ሞገስ የሚያሳይ ነው። እኔ መቼም የማልረሳው ነገር ነው። ያ ዓመት ኤልፓ ሁሉንም ነገር ያገኘበት መቼም የማይረሳ ዓመት ነበር ፤ ሁሌም ደግሞ ጋሽ ሐጎስ አብሮ ይነሳል።

ኃይሉ:- ያ ቡድን የተሰራ ቡድን ነበር ፤ ጉልላት ነበር የተረከበው። ጋሽ ሐጎስ ከቅድመ ውድድር ዝግጅት ስንመለስ ነበር ያለፈው። አሁንም ነፍሱን በአፀደ ገነት ያሳርፋት እላለሁ። እንደሱ ያለ አብሮን የኖረ አባት ሲለየን ቀላል አልነበረም። የዛን ዓመት እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን እሱን ለማሰብ ነበር ያደረግናቸው። ምክንያቱም የሰጠን ነገር በህይወት ዘመናችን ሙሉ የምንጠቀምባቸው ነበሩ። ጋሽ ሐጎስን ስናጣው ከመጎዳታችን በላይ ለእሱ ክብር ያለንን ነገር ሁሉ ለመስጠት የተፈጠረብን ተነሳሽነት ይበልጥ ነበር። በጣም ብናዝንም በዚያን ዓመት ባደረግናቸው ነገሮች ሁሉ ውስጣችን ነበር።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!