“እኔ የተቀጠርኩት ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማሳለፍ ነው” ተመስገን ዳና

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅትን አስመልክቶ ከሰዓታት በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

9:30 ወሎ ሠፈር አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ህንፃ ላይ በተሰጠው በዚህ አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ተመስገን ዳና ተገኝተዋል። አሠልጣኙም የዝግጅት ጊዜያቸውን በተመለከተ በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ገለፃ አድርገዋል።

“የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ሆኜ ከተሾምኩ 18 ቀን ሆኖኛል። ለተጫዋቾች ጥሪ አቅርቤ ዝግጅት ከጀመርን ደግሞ 14 ቀን ሆኖናል። የመጀመሪያውን 10 ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ ነበር ልምምድ ስንሰራ የነበረው። በዋናነትም በጠዋቱ የልምምድ መርሐ-ግብር የተጫዋቾቹን የአካል ብቃት ለማሳደግ ስንሰራ ከሰዓት ደግሞ ታክቲካዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥተን ሰርተናል። የጊዮርጊሱን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ካደረግን በኋላ ደግሞ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ልምምድ ስንሰራ የነበረው። ከምንም በላይ ደግሞ ታክቲካዊ ነገሮች ላይ ስራዎችን ስንሰራ ታንዛኒያ ላይ የነበረውን ከ17 ዓመት በታች ቡድን መነሻ አድርገን ነበር። እንደምታቁት ታንዛኒያ ላይ የነበረው ቡድን ስኬታማ ነበር። ይህም ውድድር የታንዛኒያው ስብስብ ነፀብራቅ ስለሆነ ትኩረታችንን ስብስቡ ላይ አድርገናል። እንደምታስታውሱት የታንዛኒያው ውድድር ላይ 16 ጎሎችን አስቆጥረን ነበር። 8 ጎሎች ደግሞ ተቆጥረውብን ነበር። እኛም 16 ጎሎችን ያስቆጠርንበትን መንገድ አሁን ይጠቅመናል ብለን ስላሰብን መርምረነዋል። 8ቱ ጎሎች የተቆጠሩብንም መንገድ አይተናል። በዚህም ከስምንቱ አራቱ በግንባር የተቆጠረብን ነበር። ከዚህ መነሻነትም ይህንን የመከላከል ችግር ለመቅረፍ ስራዎችን ሰርተናል። እንዳልኩትም የቅዱስ ጊዮርጊሱን ጨዋታ ካደረግን በኋላም የአቋም መለኪያ ጨዋታውን መነሻ አድርገን በጠንካራ እና ደካማ ጎኖቻችን ላይ ስራዎችን ሰርተናል። በተለይ በጨዋታው የታየብንን ግብ የማስቆጠር ችግር ላይ ትኩረት ሰጥተን ሰርተናል። በአጠቃላይ ግን አጭር የዝግጅት ጊዜ ቢኖረንም መልካም ነገሮች ነበሩን።

“ተጫዋቾቻችንን የመረጥንበት መንገድ ግልፅ ነው። እንዳልኩት አጭር ጊዜ ስለነበረን ተዘዋውረን ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን በደንብ አላየንም። የኮቪዱም ነገር ስለነበረ ነገሮች አስቸጋሪ ነበሩ። ግን አሠልጣኞች ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች እንዲልኩ እና እኔ ከ17 ዓመት በታች ጀምሮ የማቃቸውን ተጫዋቾች ማምጣት የሚለውን አማራጭ ወሰድን። በዚህ መንገድ መጀመሪያ 35 ተጫዋቾችን መርጠን ዝግጅታችንን ጀመርን። ከዛም በፓስፖርት እና በብቃት የመጡትን ተጫዋቾች ለይተን 20 ተጫዋቾችን አሁን መርጠናል። ምናልባት ዛሬም የተመረጡትን ተጫዋቾች በፌዴሬሽናችን በኩል እናሳውቃለን።”

ከ20 ደቂቃዎች ባልዘለለው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አሠልጣኙ ለ14 ቀናት ያክል የቆየውን የዝግጅት ጊዜ ካብራሩ በኋላ የቡድኑን ግብ ተጠይቀው ተከታዩን ብለዋል።

“እኔ የተቀጠርኩት ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማሳለፍ ነው። ስለዚህ ግባችን ይህ ነው። ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈንም እስከ ዓለም ዋንጫ ድረስ ለመድረስ እናልማለን። እንደሚታወቀው ከዚህ ቀደም ለወራት ጊዜ ብቻ ነበር ውሎች የሚሰጡን። አሁን ግን እኔ ለ1 ዓመት ነው ውል የተሰጠኝ። ስለዚህ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላም ጊዜ ስላለኝ ነገሮችን ለማስቀጠል እንሞክራለን። ስለዚህ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ወደየቤታችን በባዶ አንመለስም የሚል እምነት አለኝ። ስለ አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏችን እያሰብን እንመጣለን።”

ዝግጅቱን ከጀመረ ከ10 ቀናት በኋላ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያከናወነው ቡድኑ ሌላ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊዎቹ ክለቦች ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ከቡድኑ ጋር ሀሙስ ጨዋታ ለማድረግ ቢፈልጉም ከጊዜዎች መጣበብ እና ጉዳትን ፍራቻ ጨዋታው እንደማይካሄድ ተገልጿል።

©ሶከር ኢትዮጵያ