የታዳጊ ቡድኑ ለሴካፋ ዋንጫ ዝግጅቱን እያደረገ ነው

በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

ከታኅሣሥ 13-28 ጀምሮ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ይደረጋል ተብሎ መርሐግብር በወጣለት ከ17 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝ  እንድርያስ ብርሀኑ፣ በምክትልነት አሰልጣኝነት አሳምነው ገብረወልድ እና የግብጠባቂ አሰልጣኝ አዳሙ ኑመሮ እየተመራ አያት በሚገኘው የካፍ አካዳሚ ዝግጅቱን ከጀመረ ሳምንታት አስቆጥሯል።

መጀመርያ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ፌዴሬሽኑን ለገንዘብ ወጪ የዳረገው አብዛኛውን ማለት በሚቻል መልኩ በ MRI ምርመራ መውደቃቸው ነው። ይህን ተከትሎ ቡድኑ ሌሎች ተጫዋቾችን ለማግኘት ሲል ከክልል እና በየአካባቢው ምልመላ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ሀያ ሦስት ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምዱን እየሰራ ይገኛል። ዛሬም ረፋድ ላይም በአዲስ አበባ ስራዲየም በከፍተኛ ዲቪዚዮን ከሚሳተፈው የመከላከያ የወታደር ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጓል።

በቀሩት ቀናት ተመሳሳይ የአቋም ፈተሻ ጨዋታ እንደሚያደርግ ሲታወቅ በውድድሩ መዳረሻ ቀን 20 ተጫዋቾችን ይዞ በመያዝ ወደ ሥፍራው የሚያቀና ይሆናል። አጠቃላይ የተጫዋቾቹን ስም ዝርዝር እና የተመረጡበትን ክለብ በተመለከተ መረጃውን እንዳገኘን የምናሳውቅ ይሆናል።

አወዳዳሪው አካል ሴካፋ ዕድሜን በተመለከተ የሚለየው ፓስፖርትን ሳይሆን MRI በመሆኑ በ2009 የተደገመው ስህተት አሁንም ድጋሚ እንዳይፈፀም ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክታችን ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ