የዳኞች ገፅ | ባለግርማ ሞገሱ የቀድሞ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኪነ ጥበቡ

በአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያን በመወከል ካጫወቱ ዳኞች መካከል የሚመደበው እና በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ጨዋታ በመዳኘትም እውቅና ያተረፈው የቀድሞ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኪነ ጥበብ የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችን ነው።

ኑሮውን በሀገረ አሜሪካ ካደረገ ዓመታት አስቆጥሯል። አልፎ አልፎ ወደ ትውልድ ሀገሩ በመምጣት ያለውን ልምድ በተለያዩ ጊዜዓት አካፍሏል። ከአስራ አምስት ዓመት በላይ በቆየው የዳኝነት ህይወቱ በሀገር ውስጥ ከሀገር ውጭ ለቁጥር የሚታክቱ በርካታ ጨዋታዎችን በብቃት ዳኝቷል። ከምንም በላይ ለሀያ ሁለት ዓመታት በአፍሪካ ከተስፋዬ ገብረየሱስ በኃላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የሚወክል ዳኛ ተቋርጦ የነበረውን ሁኔታ ያስቀጠለው እርሱ ነው። የሸገር ደርቢን ጨዋታን ለተከታታይ ዓመት በመዳኘት የሚታወቀው ባለ ግርማ ሞገሱ ልባም ዳኛ እንደሆነ የሚነገርለት የቀድሞ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኪነ ለእረፍት ወደ ትውልድ ሀገሩ በመጣበት ጊዜ አግኝተነው በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን እንግዳ አድርገነው በርከት ያሉ ጥያቄዎች አንስተንለት ተከታዩን ምላሹን እንዲህ ሰጥቶናል።

ከትውልድ እና እድገትህ በመጠየቅ ጥያቄዬን ልጀምር ?

ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ቀበና አካባቢ ነው። ተወልጄ ከሀገሬ እስክወጣ ድረስ በሌላ አካባቢ አልኖርኩም። የኔ መነሻዬም መድረሻዬም ቀበና ናት።

ዳኛ ለመሆን ያነሳሳህ ምክንያት ምድነው?

የሚገርመው ከልጅነቴ ጀምሮ እግርኳስን እወድ ነበር። ኳስ እንድወድ ያደረጉኝ በሰፈራችን አንድ የፖሊስ አባል የሆኑ ሀምሳ አለቃ ንጉሴ የሚባሉ ሰው ነበሩ። ልጅ ሆኜ ወደ ስታዲየም ይዘውኝ ይሄዳሉ። እኔም እየሄድኩ ጨዋታ እመለከት ነበር። እያደግን ከፍ እያልን ስንመጣ በኃላ እርሳቸው ጡረታ ሲወጡ ስታዲየም የመግባት እድሉን እያጣው መጣሁ። ከፍዬ ለመግባት ደግሞ አቅም ይጠይቃል። የሚገርመው ለኳስ ካለኝ ከፍተኛ ስሜት የተነሳ ስታዲየም ባልገባ እንኳ በሩ ላይ ደርሼ የምመለስበት ሁኔታ ነበር። አያቴ ፍልውሀ ይሰሩ ስለነበር እርሳቸው ጋር ምሳ እየበላሁ የጨዋታ ቀን ስታዲየም እውል ነበር። አንዳንዴም የማውቃቸው የሰፈር ፖሊሶችን እየጠየቅሁ እገባ ነበር። ይሄም ካልተሳካ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው በሩ ተከፍቶ ይለቀቃል ስለነበረ እየሮጥን በመግባት የቀረችውን ደቂቃ እንመለከት ነበር። በአጠቃላይ የኳስ ስሜቴ እና ፍቅሩ ወደ ዳኝነቱ እንድገባ ምክንያት ሆኖኛል። ሌላው ምክንያቴ በፌዴሬሽኑ ተመዝግቦ የሚያጫውት ዳኛ የስታዲየም ነፃ መግቢያ የሚያገኝ ስለነበር እኔም ካለኝ የእግርኳስ ፍቅር ይህን መንገድ ተጠቅሜ ስታዲየም ለመግባት ዳኛ ለመሆን ችያለው። እግርኳስን በመጫወት ከሰፈር ያለፈ ብዙ አልተጫወትኩም።

ታዲያ የመጀመርያውን መምርያ ዳኝነት ኮርስ እንዴት ልትወስድ ቻልክ ?  

አንድ ጓደኛዬ ኮርስ እንደሚሰጥ እና በአዲስ አበባ በአራቱም ዞን የዳኞች ስልጠና እንደሚሰጥ ማስታወቂያ ወጥቶ ስለነበር እኔም አራት ኪሎ ወዕክማ ከሰፈር አንድ አራት ልጆች ሆነን ሄደን ተመዘገብን። ለአንድ ወር ወደ መቶ ሀምሳ አካባቢ እንሆናለን አቶ አባይ ተሾመ፣ ኮነሬል ደነቀ መንግሥቴ እና አቶ ሞገስ የሚባሉ አሰልጣኞች ኮርሱን ወሰድን። በተለይ አቶ ዓባይ በጣም ልምድ ያላቸው ከጋሽ ይድነቃቸው ጋር አብረው የሰሩ ሰው ናቸው። ኮሩሱን ወሰድን የሚያልፈው አለፈ የሚወድቀው ወደቀ። በዓመቱ ሁለተኛ ደረጃ መምርያ ኮርስ ተሰጠ። እርሱንም ወሰድኩ። በወቅቱ ከእኔ ጋር እኩል የወሰደው ኃይለመላክ ተሰማ ነበር። ይህን ኮርስ የወሰድንበት ዘመን ከ1972 ይሆናል።

ከስልጠናው በኃላ በመምርያ ደረጃ  ማጫወቱ እንዴት ነበር ?

በወቅቱ ገና ጀማሪ ስለነበርን በከፍተኛ ሁኔታ የቀበሌ ጨዋታ የተጋጋለበት ጊዜ ስለነበረ ፌዴሬሽኑ በቀበሌ እና በተለያዩ ውድድሮች እንድናጫውት ይመድበን ነበር። ይህ ለኛ ከፍተኛ ልምድ እንድናገኝ ረድቶናል። ከኛ ጋር ይሄን ኮርስ የጀመሩ ነበሩ። ብዙዎቹ አልገፉበትም አቋርጠው ወጡ። በጊዜው ዳኛ ለመሆን በጣም ፈተኝ ነበር። አንተ እንደፈለከው የምታጫውትበት ቦታ አትመደብም። በብዛት ረዳት ዳኛ ነው የምትሆነው። ልምድ ያለው ዳኛ አንዳንዴ ሲቀር እርሱን ተክተህ ዋና ዳኛ ትገባለህ እንጂ በአብዛኛው የሚሰጠው ረዳት ዳኛ መሆን ነው። በጊዜው በጣም ጠንካራ የነበሩ አቅም ያላቸው ዳኞች እንደ በቀለ ኪዳኔ፣ ጌታቸው ገብረማርያም፣ ታደሰ ደገፉ ሌሎችም ነበሩ። እነርሱ እያሉ የፈለክበት ቦታ ማጫወት የማይታሰብ ነው። ስለዚህ ደረጃህን ጠብቀህ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈህ ነው የምታስበው ቦታ የምትደርሰው። የምናጫውተውም ብዙ ጊዜ ፖሊስ ሜዳ፣ ጃን ሜዳ ሌሎችም ሜዳ ነው። አዲስ አበባ ስታዲየም ማጫወት በዛን ጊዜ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው።

ፌዴራል ዳኛ ለመሆን ምን ያህል ዓመት ወሰደብህ ?

ፌዴራል ዳኛ ለመሆን ወደ አስር ዓመት በላይ ወስዶብኛል። ባልሳሳት በ1984 ይመስለኛል የፌደራልነት ባጁን ያገኘሁት። በወቅቱም አንድ ዳኛ ከመምርያ ጀምሮ ፌደራል ለመሆን በቅድሚያ አስር ዓመት ማገልገል አለበት ስለሚል ህጉ ረጅም ዓመት ወሰዶብናል። ፌደራልም ለመሆን በብዙ ግፊት እነርሱ መምጣት አለባቸው ተብለን ነው ፌደራልነቱን ያገኘነው።

መቼም አንድ ዳኛ አዲስ አበባ ስታዲየም ገብቶ ማጫወት በዳኝነቱ ዘመን ትልቅ ስኬት ነው። በጊዜው አንተ ፌደራል ዳኛ ሆነህ መጀመርያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያጫወትከውን ጨዋታ ታስታውሰዋለህ ? 

ከዚህ በፊት ረዳት ዳኛ ሆኜ አዲስ አበባ ስታዲየም እየተመላለስኩ አጫውቻለው። ዋና ዳኛ ሆኜ ግን አግሮ እንዱስትሪ እና ባህር ኃይል ነበር ያጫወትኩት። ሁለቱም ቡድኖች አሁን የሉም። በዚህ ነው ዋና ዳኝ ሆኜ ለመጀመርያ ጊዜ ፊሽካ ይዤ የገባሁት። የሚገርመው በጊዜው ጥሩ ዳኝነት ሰጥቻለው፣ አሪፍ ነበርኩ ብዬ ለራሴ ተስፋን ሰጥቼ ነበር። ጋዜጦችም አዲስ ዳኛ ሲመጣ ጥሩ ነበር አልነበረም እያሉ ይፅፉ ነበር። የዛኔ ምንም አልፃፉም። ይገርምሀል አንድ አጋጣሚ በጨዋታው ጊዜ አጋጥሞኛል። ከእኔ ከስምንት ሰዓት ጨዋታ በኃላ አስር ሰዓት ትልቅ ጨዋታ ነበር። በወቅቱ አዲስ ህግ ወጥቶ ነበር። በፊት ተጫዋች የትም ቦታ ላይ ሲጎዳ ዳኛው የተጎዳውን ተጫዋች ሳይመለከት የህክምና ባለሙያው እንዲገባ ይፈቅድ ነበር። ሆኖም ይህ ህግ ተቀይሮ አንድ ተጫዋች ከተጎዳ ዳኛው ያለበት ቦታ ድረስ ሄዶ አይቶ ሲፈቅድ ነው ህክምና እንዲያገኝ ጥሪ አድርጎ የሚያስገባው። ይህ ህግ ከተቀየረ ሳምንት አይሆነውም። ይህንን ጨዋታ እያጫወትኩ ኳሱ ጎል ጋር ቆሞ እዛኛው ጎል ጋር ተጫዋች ተጎድቷል። ስለዚህ በተሻሻለው ህግ መሰረት ከነበርኩበት ቦታ ልጁ ወደ አለበት ቦታ መድረስ ስላለብኝ እየሮጥኩ ስሄድ በስታዲየሙ የነበረው ተመልካች ሾላ፣ ሾላ እያለ ይጮሀል። ስቴዲየም አቅም ካነሰህ ካልቻልክ ስድብ ነው እነርሱ ግን ሾላው እያሉ ይጮሀሉ። የቀድሞን ህግ ነው የሚያቁት እኔ የማላውቅ መስሏቸው “ሾላ ሾላ” ይላሉ። እኔ በውስጤ አይ እኔ እንኳን ሾላ አይደለሁም አላወቃቹሁኝም ብዬ በውስጤ እየሳኩ ሥራዬን ሰርቼ ወጣሁ። ከዚህ በኃላ ጋሽ ከበደ የሚባሉ የዛሬይቱ የስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ናቸው። ሁሌም ከእሳቸው አስተያየት እቀበል ነበር እና አራት ኪሎ አግኝቻቸው ‘ጋሽ ከቤ ሠላም ነው እንዴት ነው?’ ስላቸው፤ ‘እንደው የበቀደሙ ጨዋታ ሰዉ አልተቀበለውም። እኔም ደስ አላለኝም ትንሽ ግር አለህ’ አሉኝ። ‘ምነው እኔ እኮ ህጉን ነው የተገበርኩት’ አልኳቸው። ከዛ በመቀጠል አንድ የጡረታ ሚኒስቴር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ግርማ ደምሴ የሚባሉ ሰው ‘አንተ ዳኝነት ቢቀርብህ፤ አስቸግሮሀል ወይም በደንብ ተለማምደህ ና አለበለዚያ ግን ይቅርብህ’ አሉኝ። እኔም እነዚህ ሰዎች እንደዚህ የሚሉኝ ከሆነ ከባድ ነው። ግን ምን አጠፋው ህጉን ነው የተገበርኩት ብዬ ለራሴ መለስኩ። የሚገርመው ለስድስት ወር በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ ሳይሰጠኝ ቆይቼ በመጨረሻ መብራት ኃይል ከ አየር ኃይል የአዲስ አበባ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ተሰጠኝ። ዛሬ በደንብ ከሠራሁ ከቀናኝ ጥሩ፣ ካልሆነ ግን የኔ የዳኝነት ነገር አበቃ ብዬ ገባሁ። ፈጣሪም ረድቶኝ የተሳካ ጨዋታ ሆነ ስቴዲየም ተጨበጨበልኝ። ሁሌ የሚጨበጨብለት ሰለሞን ዓለምሰገድ ነበር። እንዴት ነው እርሱ የሚጨበጨብለት እል ነበር። እኔም ተሳካልኝ በዚህ ደስ አለኝ። በወቅቱ የነበሩ ጋዜጦች ሁሉ በቃ ስለኔ ብቃት ፃፉ። የሳምንቱ ኮከብ ዳኛ አድረገው መረጡኝ። ከዚህ በኋላ ኪነን ማን ያቁመው፤ ነገሥኩ። የሀገሪቱን ትልልቅ ጨዋታ ለኔ ይሰጠኝ ጀመር። በተለተይ የሸገር ደርቢን በተከታታይ ያጫወትኩ እኔ ነኝ። በኋላ ለከፉኝ እንጂ ምንም ተቃውሞ ሳይነሳ በመዳኘት እታወቃለሁ።

በምንድነው የጊዮርጊስ እና የቡና ጨዋታ “ለከፉኝ” ያልከው? እስቲ ሁኔታውን አብራራልኝ ?

ምን አለ መሰለህ የቡናና የጊዮርጊስ ጨዋታን አንዴ ስታጫውት ከለከፉሁ በቃ ለከፉህ ማለት ነው። ሰለሞን ዓለምሰገድን የመሰለ ዳኛ ያጣነው በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ነው። ለከፉትና በዛው ቀረ፤ አጣነው። እኔም የሁለቱን ቡድኖች በተከታታይ አራት አምስት ጨዋታ መርቼ በአንድ ጨዋታ አጋጣሚ በጣም ቀላል እኮ ነበር። አሰግድ ተስፋዬ ላይ ጥፋት ይሰራና ፊሽካ እነፋለው እርሱ ግን ኳሱን መቶ ጎል ያስቆጥራል። በዚህ ሰዓት እኔ ቀድሜ ፊሽካ ነፍቻለው ጎሉ አይፀድቅም አልኩ። በቃ ልነግርህ የማልችለው ተቃውሞ ተነሳ 3-1 ጊዮርጊስ እየመራ ነበር። ‘ይህች ጎል ብትገባ 3-2 እንሆን ነበር። አልፎም ተርፎ እኩል ልንሆን እንችላለን’ በማለት የሌለ ሂሳብ ያሰሉ ጀመር። እንዴ እነርሱ ሲያገቡ ጊዮርጊስ ቀሞ ያያል እኔ ደግሞ እንዲህ ያለ ስሌት የለም አይሆንም ብዬ ጎሉን ሻርኩ። በዚህ ሁኔታ ተቃውሞ ተነሳብኝ። እንዲያውም ከዚህ በኃላ የሁለቱን ጨዋታ አላጫውትም ብዬ ተውኩት።

በጊዮርጊስ ዙርያ ወደ ኃላ የማነሳው ጥያቄ ይኖራል። አሁን በፌደራል ዳኝነት ምን ያህ ዓመት ካገለገልክ በኋላ ነው ኢንተርናሽናል የሆንከው ?

ወደ አምስት ዓመት በፌደራል ዳኝነቱ ቆየሁና ኢትዮጵያ በኢንተርናሽናል ዳኝነት ለአንድ ዓመት ታግዳ በኃላ አራት ዳኞች ሲወጡ ለእኛ ትልቅ እድል ሆኖ ኃይለመላክ ተሰማ፣ ተድላ እኔ ሆነን እነርሱን ተክተን ከገባንበት ከ1988 ጀምሮ ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኛ በመሆን ከሰራሁ በኃላ ከሀገሬ እስከወጣሁበት 1998 ድረስ በኢንተርናሽናል ዳኝነቱ አገልግያለሁ። የመጀመርያ ጨዋታዬም የኬንያው ጎር ማሂያ እና የግብፁ አል አልአህሊ ጨዋታን በቀለ ኪዳኔ ዋና ሆኖ እኔና ሽፈራው እሸቱ ረዳት ሆነን አጫወትኩኝ። በመቀጠል ዋና ዳኛ ሆኜ የወጣሁት ዩጋንዳ ላይ ካምፓላ ሲቲ እና የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ጨዋታን ነበር።

በአፍሪካ በትልልቅ መድረኮች ለምሳሌ የክለቦች የፍፃሜ ጨዋታ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታን አጫውተሀል ? 

አዎ! በሚገባ። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የአንጎላው ስሙ ዘነጋሁት ክለብን ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ የመልስ ጨዋታ አጫውቻለው። የመጀመርያውን ቱኒዝ ላይ ኤስፔራንስ 2-0 አሸንፎ የመልሱን ጨዋታ አንጎላ ላይ የዳኘሁት እኔ ነኝ። ሌላው ከጋሽ ተስፋዬ ገብረየሱስ ዳኝነትን ካቆመ ከሀያ ሁለት ዓመታት በኃላ በአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያዊ ዳኛ በአፍሪካ ዋንጫ ተመድቦ አያቅም ነበር። እኔ ነኝ በ21ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡርኪናፋሶ ላይ (1998) የተመደብኩት። በአፍሪካ ዋንጫም ሁለት ጨዋታ ብቻ ነው ያጫወትኩት በወቅቱ ትልልቅ ዳኞች ስለነበሩ ከዚህ በላይ እድሉን አላገኘሁም። በጊዜው ለምሳሌ የ1998 ዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ብራዚል ከፈረንሳይ ያጫወተው የሞሮኮ ዳኛ ሌሎችም ነበሩ። በአጠቃላይ ለአንድ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተካፍዬ አውቃለው። ከዛ በኃላ በድጋሚ የመመደቡን እድል አላገኘሁም።

በነገራችን ላይ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በኃላ ለሁለት ዓመት ከማንኛውም ኢንተርናሽናል ጨዋታ እንዳታጫውት ካፍ ቅጣት ጥሎብህ ነበር። ምክንያቱ ምን ነበር ?

ቅድም እንዳልኩሁ የአንጎላው እና የቱኒዚያው ክለብ የመልሱን ጨዋታ እኔ እና ይግዛው ብዙ አጫውተን ቱኒዚያዎች ‘የማይሆን ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቶብናል። ሌሎችም ነገሮች አድርጎናል’ ብለው በጊዜው አረቦች በካፍ ተሰሚነት ስለነበራቸው ጫና አሳድረው ካፍ ከአቅም በታች አጫውታችኋል በሚል እኔና ይግዛውን ለሁለት ዓመት ቅጣት ቀጡን። በጊዜው በጣም አዘንኩ። እዚህ የነበሩ የኛ የፌዴሬሽን አመራሮች እኔን የማይፈልጉ ስለነበሩ ለኔ መከራከር እና ቅጣቱ እንዲነሳልኝ ማድረግ ሲገባቸው ጭራሽ ውሳኔውን አድንቀው ‘ካፍ የወሰነውን ውሳኔ እናደንቃለን’ ብለው የድጋፍ ደብዳቤ ለካፍ ፃፉ። በጣም ያሳዝናል። በግል እኔን ለመጉዳት የሚሮጡ ሰዎች ስለነበሩ አጋጣሚውን ተጠቅመው ይህን አደረጉ። ይግዛው ብዙ በዛው ዳኝነትን ሲያቆም እኔ ግን እልህ ይዞኝ እስከ መጨረሻው ተከራክሬ ከሦስት ዓመት በኋላ ወደ ኢንተርናሽናል ዳኝነቱ ቦታዬ ተመልሻለው።

በዳኝነት ዘመንህ እንዳጫወትከው በርካታ ጨዋታ ፈተነኝ የምትለው ጨዋታ አለ?

እውነት እኔ አብረውኝ የሰሩትን ጠይቀህ ማወቅ ትችላለህ። እኔ ከብዶኝ ፈትኖኝ ያለፈ ጨዋታ አጋጥሞኝ አያውቅም። ሌላው ቀርቶ በኃላ የመጡትን ሴቶች ዳኞች እነ ሊዲያ፣ ሰርካለም፣ ሳራ፣ ፅጌ መጠየቅ ትችላለህ። እርሱ ካለ ምንም ችግር ስለማይፈጠር ከእርሱ ጋር ሆነው ይለማመዱ በማለት ብዙ ጊዜ ይመደቡ ነበር። እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው አንድም ጨዋታ ችግር አጋጥሞኝ አያቅም ነበር ለማለት ነው። እንደው ረብሻ ተነሳብኝ የምለው አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ከመድን በነበረ ጨዋታ ነው። የሚገርመው ከዚህ ጨዋታ በፊት አዲስ አበባ ላይ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ኒያላ ከጨርቃጨርቅ ያደረጉትን ጨዋታ ያጫወትኩት እኔነኝ። ጨርቃጨርቅ አሸንፎ ፕሪምየር ሊግ ገብቷል። ታዲያ በዓመቱ ነው አርባምንጭ የሄድኩት ስታዲየም ውስጥ በሞንታርቦ ዓምና ወደ ፕሪምየር ሊግ ስንገባ ያጫወቱን በብቃት የመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ኪነ እያሉ አስወርተዋል። አንድ ሠላሳ ደቂቃ ጨዋታው ጥሩ ከሄ። በኋላ መድን ጎል ያስቆጥራል። በሜዳቸው ተመርተው አያቁም ነበር። በቃ ፔናልቲ እያሉ ይወድቃሉ፣ ይጮሀሉ እኔ ደግሞ ምንም የለም ተነሱ እያልኩ ጨዋታው እንደምንም አድርጌ አንድ ለዜሮ አለቀ። በቃ ተወው ከዚህ በኃላ ልነግርህ አልችልም። ድንጋይ ይወረወር ጀመር። ፖሊስ የለ ምን የለ ይወረወራል። ‘በቃ እኔ ዳኝነት ማቆም አለብኝ። እስከ ዛሬ ለራሴም ለሀገር ሰርቻለው። ከዚህ በኋላ ይሄ ህይወት የሚያጠፋ ነው በማይረባ ነገር ዋጋ አልከፍልም’ ብዬ ወስኜ ነበር። ከዚህ ውጭ በዳኝነት ዘመኔ ያጋጠመኝ የከበደኝ አንድም ጨዋታ የለም።

ከሀገርህ መቼ ወጣህ? በሰሜን አሜሪካ ኑሮ እንዴት ነው ?

ከሀገሬ ሐሙስ ልወጣ ማክሰኞ የመጨረሻ ጨዋታዬን መከላከያ ከ መብራት ኃይል አጫውቼ ሁለት ተጫዋቾችን ከሁለቱም ቡድኖች በቀይ ካርድ አስወጥቼ ነው ሐሙስ የሄድኩት። የሚገርመው ባለፈው ከአስር ዓመት በኃላ ተመልሼ ስመጣ አንድ ሐረሩ የሚባል ቅርጫት ኳስ የሚጫወት ጓደኛ ነበረኝ። እና የመብራት ሀይል ተጫዋች አይቶ ‘ኪነ ይህን ልጅ አወቅከው?’ አለኝ። ‘አይ አላወኩትም’ አልኩት። ‘የመሸኛ የመውጫ ፈልጎ ነው መሰለኝ ወደ አሜሪካ ልትሄድ ስትል በቀይ ካርድ ያስወጣኸው ተጫዋች ነው’ አለኝ አስታውሶ። እንግዲህ ከሀገሬ ከወጣው አስራ አምስት ዓመት ሆኖኛል።

ኪነ ምን አይነት ዳኛ ነበር ? 

ስለ ራሴ ማውራት ቢከብደኝም ሙያተኛው ቢናገር ጥሩ ነበር። በዳኝነት የማደንቀው ይሸበሩ ምልክት አሰጣጥህ፣ ግሬስህ፣ አካሄድህ ሁሉ ነገርህ ይለኝ ነበር። ከዚህ ውጭ ዳኝነቱ የሚፈቅድልኝ ማንኛውም ነገር ያለ ምንም ፍራቻ የምወስን ነበርኩ። አንዴ ኮምቦልቻ እያጫወትኩ አንድ ፖሊስ ትራኩ ላይ ሆኖ እየጠበቀ ከተጫዋች ጋር እያወራሁ ተጫዋቹን ስቆጣው ፖሊሱ ‘ምን ታስፈራራዋለህ?’ አለኝ። ‘እንዴ!’ ብዬ ተጫዋቹን ማናገር ትቼ ፖሊሱ ጋር ሄጄ ‘ውጣ ከሜዳ’ አልኩት። አለበለዚያ ጨዋታውን አልቀጥልም አልኩ። ከእኔ ጋር የነበሩት ረዳቶች እንለፈው ችግር የለውም ሲሉኝ ዝም በሉ አይሆንም ይህ የኔ ስራ ነው። ይወጣታል ይወጣል አልኩ። የፖሊስ አዛዡ መጣ። ሰድቦኛል ይውጣ አልኩት። እንቢ ካለ ህጉ በሚለው መሠረት አደርጋለው ስል እሺ ብሎ የወጣበት አጋጣሚ አለ። ስለዚህ የማልፈራ ደፋር ብዙም ልምምድ ላይ ሰነፍ የነበርኩ ዳኛ ነበርኩ።

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ዳኝነትን እንዴት ታየዋለህ ? 

እንደው እናተ ከምትፅፉት ነገር ተነስቼ ካልሆነ በቀር አሁን ያለውን ዳኝነት አስመልካቶ እንዲህ ነው ለማለት ይከብደኛል። አንድን ነገር ለመናገር ማየት ያስፈልጋል። ሀገሬ ስመጣ የሀገር ውስጥ ዳኞች ሲያጫውቱ አጋጥመውኝ አያቁም። ባለፈው ስመጣ የኢትዮጵያ የ20 ዓመት በታች ቡድን ከማሊ ጋር ሲጫወት ነው ያየሁት። እንደው ዘንድሮ ስለምቆይ በደንብ አይቼ አሁን ያለበትን ደረጃ መናገር እችላለሁ። ከዚህ ውጭ ግን በዓምላክ እና ሊዲያ ሀገራቸውን ወክለው እዚህ ትልቅ ደረጃ በመድረሳቸው በጣም አስደስተውኛል። ከስር ላሉት ዳኞች ትልቅ  በር ከፍተዋል። ትልቅ ስም አትርፈዋል፣ ተሰሚነት አግኝተዋል። በቀጣይ ከሥራቸው ላሉት ልምዳቸውን በማካፈል ይጠበቅባቸዋል። አሁን ሊዲያ ድፍረት፣ ወኔ እና አቅም ያላት እንደሆነ ይነግሩኛል፤ አላየኋትም። እኔ ድሮ የማቃት በረዳትነት ነው። አንድ ዓለም ዋንጫ ስታጫውት አይቻት በጣም የሚገም ከጠበኩት በላይ ጨዋታውን ተቆጣጥራ የወጣችበት ሁኔታ አሪፍ ነበረች። እንዲያውም ደውዬ አድናቆቴን ገልጬላታለው። በአጠቃላይ በዓምላክም ቢሆን ጎበዝ ዳኛ ነው። አሁን ከእነርሱ የሚጠበቀው እንደነርሱ ያሉ ዳኞችን ማፍራት አለባቸው።

ብዙ ጊዜ ‘ኪነ የጊዮርጊስ ደጋፊ ነው’ ይባላል። ለዚህ ያለህ ምላሽ ምድነው ?  

እዚህ ላይ ያለኝ ምላሽ በኢትዮጵያ ዳኝነት ትልቅ ስም ያላቸው እንደነ አየለ ተሰማ፣ ጌታቸው ገብረማርያምን ስትመለከት ለምሳሌ አየተ ተሰማ የመቻል ተጫዋች የነበረ ጌታቸው ገብረማርያም የፖሊስ ተጫዋች ነበር። ተመልከት ትልቅ ደረጃ የደረሱ ዳኞች ናቸው። እነርሱን የሚጠይቅ የለም። እኔ የጊዮርጊስ ተጫዋች ብሆን ዳኛ መሆን አልችልም? እኔ ላይ ይለጥፋሉ። ኪነ የጊዮርጊስ ነው። ተድላ ቡና ነው። እከሌ እንደዚህ ነው ብለው ይናገራሉ። መቼም አንድ ነገር ስታዲየም ሳላይ ዳኛ አልሆንኩም። በልጅነቴ ጊዮርጊስን እየተመለከትኩ አድጌ ልሆን እችላለው። ስለዚህ ዳኛ መሆን አልችልም? ሙሉጌታ ከበደ እና ገብረመድኅን ኃይሌ ጊዮርጊስ ተጫውተው ዳኛ መሆን አይችሉም? ዳኝነት እውነትን ይዘህ መዳኘት ብቻ ነው። አየለ ተሰማ የመቻል ተጫዋች ሆኖ መቻልን ያጫውት ነበር። ይህ ታዲያ እንግዲህ ማነው አየለ የመቻል ተጫዋች ሆኖ አይዳኝም የሚልህ? እኔ የምደገፈው ማልያዬ ዳኝነቴ ነው። በዓመት ውስጥ ጊዮርጊስን ሦስት ጨዋታ ላጫውተው እችላለሁ። የቀረውን ጨዋታ ማነው የሚያጫውተው። እኔ ከዚህ ሀገር ወጥቼ ጊዮርጊስ አስራ አራት ዓመት ዋንጫ ሲያነሳ እኔ እዚህ አለሁ። ሰው ይሄን መገንዘብ መቻል አለበት። ሁልጊዜ ዝም ብሎ በጥላቻ ተነስቶ የማይሆን ስም መስጠት የለበትም። እኔ መቶ ጊዜ ጊዮርጊስን ብወድ አንድ ፔናሊቲ የሚያሰጥበት ምክንያት ካለ እሰጣለው።

የዳኝነት ማልያን እስከለበስክ ድረስ ሙያው የሚጠይቀውን ታደርጋለህ። ግን በልብ ጊዮርጊስን ታደንቃለህ ?

ቅድም እንዳልኩህ ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ በወቅቱ በሀገሪቱ ትልቁ ቡድን አሪፍ እግርኳስ የሚጫወተው ጊዮርጊስ ስለነበረ ደስ ሊልህ ይችላል። ያ ስሜት ሊኖር ይችላል። ከዚህ ውጭ ተጫዋች ብሆንስ ኖሮ መዳኘት አልችልም ነበር? ይህን ጥያቄ እዚህ ሀገር እስካለው ድረስ መቶ ጊዜ ነበር የምጠየቀው። ከሀገርም ከወጣሁ በኃላ የጊዮርጊስ ነበርክ ይባላል። በተደጋጋሚም ምላሽ ሰጥቻለው። ይህንን ሰው ከጭንቅላቱ አውጥቶ ማስቀመጥ አለበት። እንዲያውም አንዳንዴ አሁን በህይወት አለ መጠየቅ ይቻላል። እነ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ አንተ እኛ ላይ በጣም ነው የምትጠነክርብን ባታጫውተን ይሻላ ይሉኝ ነበር። ውስጥ ተጫዋቾቹ እንዲህ ይላሉ ውጭ ሌላ ይባላል። ስለዚህ ለህሊናዬ ነው የምሰራው። የማምነውም አምላክ የማይሆን ነገር ስሰራስ ምን ይለኛል። ለሙያዬ ታምኜ ስሰራ የቆየሁት። 

ዳኛ መሆን ለሚያስቡ ካለህ ልምድ ምን መልዕክት ታስተላልፋለህ ? 

በመጀመርያ ዳኝነት ልብ ሙሉነት ይጠይቃል። ከፈራህ ዳኛ ባትሆን ይሻላል። በዳኝነት መሳሳት ሊኖር ይችላል። ማንም ፍፁም አይደለም። ዳኝነት የጨዋታን ህግ ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። የጨዋታ ህግ ሁልጊዜ አዲስ ነው። የጨዋታ ህግ ሁሌ ቢሮዬ ጠረቤዛ ላይ አይጠፋም ነበር። በቀን ውስጥ ሰዓት መድቤ አነብ ነበር። በፊትም በኛ ጊዜ አሁንም ያሉት ኢንስትራክተሮች እውነቴን ነው የምነግርህ በጣም ጎበዞች በቂ ችሎታ ያላቸው ናቸው። ስለዚህ አሁን ያሉትም ዳኞች ወደ ፊትም ዳኛ ለመሆን የሚያስቡት ከኢንስትራክተሮቹ ተከታትለው ማወቅ አለባቸው። ሌላው ጨዋታዎችን ማየት ይገባል። እኔ እውነት ነው የምለው ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ ትምህርት ሲሰጥ ሁሌ ምሳሌ ያደርገኛል። አዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ ካለ ኪነ አለ ብሎ ያነሳል። ኳስ ካለ አዲስ አበባ ስታዲየም በቃ አልቀርም መጥቼ አያለው። ቀን አላቅ ማታ አላቅ። ምን ቸገረኝ ሰው ከፍሎ ያይ የለ እኔ በነፃ ለምገባው ምን አስጨነቀኝ። ምክንያቱም በማየቴ የምማርበት ብዙ የተለወጥኩበት ነገር ስላለ። እንዲሁም ማየቴ ለዳኞች ትክክለኛ አስተያየት ለመስጠት በማሰብ ነው። በዚህም ዳኝነት አቁም ጥሩ አይደለህም ያልኩት ሁሉ አለ። ጥሩ ሲሆኑም ገንቢ አስተያየት እሰጥ ነበር። በዚህ አጋጣሚ በጣም የምቆጭበት እንደ ሰላሙ በቀለ ያለ ጎበዝ ዳኛ እንዲሁም ክንዴ ኃይሉ የመሰለ ጎበዝ ዳኛ ነበሩ። ሆኖም ክንዴን ሞራሉን ነኩት ኢንተርናሽናልነቱን አጣ። ዳኝነትን አቆመ በዛው ወቶ ቀረ። ሰላሙም አግኝቼ አልጠየኩትም። ወጥቶ ቀረ በጣም ምርጥ ዳኛ ነበር። እነዚህን የመሰሉ ዳኞች የት ይደርሳሉ እያልኩ ስጠብቅ ያለ ምክንያት ወጥተው ሲቀሩ ቅር ይለኛል። በተረፈ ጨዋታዎችን መከታተል በድፍረት መምራት ነው። ዋናው ህጉ የሚለውን መተርጎም ነው። ተመልካች ጮህ ምን አለ መስማት አያስፈልግም። ዳኝነት ትልቁ ስህተት የሚሆነው ባላንስ ለማድረግ ስትሄድ ነው። ስህተት ልትሰራ ትችላለህ። ግን ይህ ሆነ ብለህ ባላንስ ለማድረግ ከሞከርክ ትልቅ ስህተት ነው። ያ ስህተት ሆነ እዛው ይቅር ያንን ቀጥለህ ከሄድክ አንዳንዴ ጥሩ አይደለም ጨዋታው ይበላሽብሀል። እሰማለው የደርቢ ጨዋታ አልተመደብኩም ለምን ብለው ሲጠይቁ ይገርመኛል። እንዴት ሰው ይህን ጨዋታ ላጫውት ብሎ ራሱን ከዳኝነት ላውጣ ብሎ ማመልከቻ ያስገባል። ኮሚቴው ካልመደበው በቃ የተመደበበት መሥራት አለበት። አንድ ዳኛ የትኛውንም ጨዋታ ሳይመርጥ ዝቅም ብሎ ከፍም ብሎ ማጫወት አለበት። የትም ሀገር ቢሆን ዳኛ ማለት ወታደር ነው። የሚገርመው እኔ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆኜ የፕሮጀክት ታዳጊዎች ጨዋታ አጫውቻለው፤ ልጆቹ ደስ እንዲላቸው ተብዬ። ስለዚህ የሚሰጣቸውን ጨዋታ ሳይመርጡ በእኩል አቅም ማጫወት አለባቸው።

የቤተሰብ ህይወትህ ምን ይመስላል ? 

ለጊዜው ብቻዬን ነው ያለሁት። አንዲት ልጅ አለችኝ። አሜሪካ ኦክላንድ ከተማ ትምህርት እየተማረች ነው። ትምህርት እና ስራ አቀላቅላ እየኖረች ነው። በስራዋ ነርስ ነች። እድሜዋ ወደ 27 ይጠጋል። ወደ ዳኝነቱ ፈፅሞ የለችም። ወንድ ልጅም ብትሆኖ እንኳን ወደዚህ ሙያ አላሰማራውም። ሙያው ከባድ ነው። እንዲሁ ዘለህ የምትገባበት አይደለም።

በመጨረሻ…

በመጨረሻ ማለት የምፈልገው በዳኝነት ዙርያ አስቸጋሪ ነገር ቢኖር አሁን የዝቅተኝነት ስሜት መጥቷል። ፖለቲካው ወደ እግርኳሱ ገብቷል። ዳኞች በነፃነት ማጫወት የማይችሉበት ጊዜ ደርሷል። ፖለቲከኞች በእግርኳሱ ገብተው ይህ የኔ ክልል ነው። ተጎድቷል፣ ህዝቡ ኳስ ማየት ይፈልጋል። የኔ ክልል ስለሆነ ነው የምትጫነኝ የሚል የዝቅተኝነት ስሜት መጥቷል። በተለይ ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ ሁኔታ መካሄድ ከጀመረበት ወዲህ እኔ በነበርኩበት ጊዜ ወደ ተለያዩ ክልሎች ዞረን ስናጫውት በሠላም የምንወጣው ትግራይ ክልል ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ለወደፊቱ መታረም አለበት እያልኩ በዳኝነት ዘመኔ አብረውኝ የሠሩት ሰለሞን ዓለመሰገድ፣ ኃይለመላዕክ ተሰማ፣ ተድላ ተሰማ (በህይወት የለም) በጣም ነው የማደንቃቸው። ይሸበሩ ምትኬ፣ ይግዛው ብዙ  በጣም ብዙ አሉ ሳልጠቅሳቸው የማላልፋቸው ጥሩ ትምህርት የሚሰጡን የነበሩ። በአጠቃላይ ፈታኝ እና ከባድ የሆነውን ዳኝነት በቆየሁበት ዓመታት በነበረው በዳኝነት ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። እናንተም ፈልጋችሁ ቃለመጠይቅ ስላደረጋችሁ አመሰግናለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ