ሶከር መጻሕፍት | የላይኛው የሜዳ ክፍል እንቅስቃሴዎች (ምዕራፍ ሦስት – ክፍል አንድ)

THE PHILOSOPHY OF FOOTBALL፡ UNDER THE SHADOWS OF MARCELO BIELSA” ለአራት ዓመታት ያህል ከፍተኛ ጥናትና ምርምር የተደረገበት ሥራ ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙረያ ቡና ፉት እየተባለ ከተደረጉ ምሁራዊ ውይይቶች አንስቶ ማርሴሎ ቢዬልሳን የተመለከቱ በርካታ ቃለ-መጠይቆችን መሥራት ጠይቋል፡፡ የእግርኳስ ሐሳባውያኑን ፍለጋ የተደረጉ የውጭ ጉዞዎችና አያሌ መጻሕፍትን መዳሰስም የዚህ መጽሐፍ ግብዓቶች ሆነዋል፡፡ ጸሃፊው በዚህኛው ምዕራፍ አርጀንቲናዊው የእግርኳስ ታክቲክ ባለሟል ከሌሎች በተለየ ኅልዮታዊ ልህቀት ያገኙበትን ምስጢራት ለማብራራት ይጥራል፡፡

” እግርኳስ በተጋጣሚ ቡድን ዙሪያ ማሰላሰል ብቻ አይበቃውም፡፡ የኳሱን ፍሰትና እንቅስቃሴ ማጤን ብቻም ጨዋታውን ምሉዕ አያደርገውም፡፡ ይልቁንም በጨዋታ ወቅት ኳሱ በአንጻራዊነት የሚገኝበት እንዲሁም ተጫዋቹ የሚንቀሳቀስበት ቦታ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡” – ሉዊ ቫንሃል

ባለ ብሩህ አዕምሮ ባለቤት ከሆኑትና በእግርኳሱ የስልጠና ዓለም ታትረው ከሚሰሩ ወዳጆቼ መካከል አንዱ የሆነው ጄምስ ናሽ ነው፡፡ ሁለታችንም አዘወትረን የምንከውነው ድርጊት አለን፡፡ በእግርኳስ ዙሪያ ለሥምንት ሰዓታት የሚቆይ ሰፊና ጥልቅ ውይይት ማድረግ፡፡ ከለንደን ሰሜናዊ ምዕራብ ሰማንያ ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በሚገኘው የሚልተን ኬይንስ ከተማ ቡና እየጠጣን የተለመደው ውይይታችንን ስናካሂድ ለተጫዋቾቹ አዘወትሮ የሚሰነዝረውን ጥያቄ አነሳልኝ፡፡ ” የቅብብሉ ፋይዳ ምን ነበር?”    

የጄምስ የአስተሳሰብ መንገድ ሁሌም ሐሳብ አመንጪ፣ አነሳሽ እና አከራካሪ ነው፡፡ በእርግጥ ለብቻ ሆኖ እርሱን መከራከር ያዳግታል፡፡ እርሱን  ሙግት መግጠም በአንድ በኩል መነቃቃት ይፈጥራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በማናቸውም እግርኳሳዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ሲያሰላስል፣ ሲመራመርና ትንታኔ ሲሰጥ የመስማት ዝለት ላይ ይጥላል፡፡   

በጨዋታችን መሃል ” የቅብብሉ ፋይዳ ምን ነበር?” በማለት ለተጫዋቾቹ የሚያቀርበው ጥያቄ ትኩረቴን ስቧል፡፡ ምክንያቱም በጨዋታ ወቅት ሜዳ ላይ ለሚከወኑ እግርኳሳዊ እንቅስቃሴዎች (በተለይም-ለቅብብሎች) በተለያዩ ጊዜያት ቁጥራዊ ወይም ስሌታዊ ዋጋ መተመን ከግል ሥሜት ጋር የተያያዘ ፍረጃ የመስጠት ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሶስተኛው ወይም አራተኛው ተጫዋች እንቅስቃሴ ተብሎ ለሚጠራው ታክቲካዊ ኅልዮት የሚያግዙ መነሻ ሐሳቦችን ጠቀሜታ ያኮስሳል፡፡ እንዲያም ሆኖ ናሽ ሊያስተላልፍ ከሚሻው መልዕክት ጥሩ ትምህርት አግኝቼበታለሁ፡፡    

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማርሴሎ ቢዬልሳ በሚያሰለጥኗቸው ቡድኖች የሚተገበሩ በርካታ የልምምድ መርኃግብሮችን የማጥናት ዕድሉ ገጠመኝ፡፡ በእያንዳንዳቸውን ቅብብሎች ትግበራ፣ ፍሰትና ግለት ዙሪያ የሚሰጡ ሐተታዎችን በአንክሮ ስከታተል ሁሉም ዝርዝር ጉዳዮች የራሳቸው የሆነ ትርጉም እንዳላቸው ተረዳሁ፡፡

” በቅብብሎች አማካኝነት የሚደረጉ ሰላሳ ስድስት ዓይነት የመግባቢያ መንገዶች አሉ፡፡” – ማርሴሎ ቢዬልሳ   

በቅብብሎች ሳቢያ የሚፈጠሩ መግባቢያዎችን   በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ለማስቀመጥ የሚረዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ መንገዶች ይኖራሉ፡፡ የቢዬልሳ ሰላሳ ስድስት መግባቢያ መንገዶች የተመረጡትና የሚታወቁትም በማርሴሎ ቢዬልሳና የፍልስፍናቸው አራማጅ በሆኑ ተከታዮቻቸው አማካኝነት ነው፡፡ የእርሳቸውን የቅብብሎች ኅልዮታዊ አወቃቀር ተጫዋቾቻቸው እንኳ በስፋት የሚያውቁት አይመስልም፡፡ ይሁን እንጂ ትክክለኛውን የመግባቢያ ሥርዓት(ቅብብል) ተገቢ በሆነ መንገድ ለሚጠቀሙት አካላት በጥሩ ሁኔታ ይገለጥላቸዋል፡፡ ይህ ማለት አንድ አጥቂ እና አንድ የመሃል ተከላካይ በጨዋታ ወቅት በቅብብሎች አማካኝነት በምን መልኩ መግባባት እንዳለባቸው የሚሰጣቸው ዝርዝር ትዕዛዛት እና እንዲወጡ የሚጠበቅባቸው ኃላፊነቶች ለየቅል ናቸው፡፡       

ከዚህ የምንረዳው ለማርሴሎ ቢዬልሳ ወለል ብሎ በግልጽ የሚታያቸው የመግባቢያ መንገድ በሜዳው ቁመት የሚደረጉ ቅብብሎችን የሚያሳልጥ እንዲሁም የተዘጋውን የተጋጣሚ ቡድን የመከላከል አደረጃጀት ማስከፈት የሚያስችል ሐሳብ መሆኑን ነው፡፡  

በ2014 ማርሴሎ ቢዬልሳ የማርሴይ አሰልጣኝ ሆነው ሲሾሙ አርጀንቲናዊው የታክቲክ ሊቅ በሰኔ ወር መጨረሻ በሁለተኛው የልምምድ መርኃግብራቸው ላይ ተጫዋቾቻቸው ከተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች አንጻር ሜዳ ላይ የተሻሉ ቅብብሎች የሚከውኑባቸውን፣ የጨዋታ ቅጽበቶችን የሚረዱባቸው፣ የቅብብሎችን አቅጣጫዎችና ልኬት የሚገነዘቡባቸውን የተለያዩ ዘዴዎች እንዲለምዱላቸው ጠይቀው ነበር፡፡    

የአትሌቲክ ቢልባዖን ክለብ የልምምድ መርኃግብሮች ላይ እየተገኘሁ እያንዳንዱን ሁኔታ ስቃኝ በሜዳው ላይ በርካታ ምልክቶች መቀመጣቸውን አየሁ፡፡ የሚሰጡት የልምምድ አይነቶች የተለመዱትን የሚጻረሩ አልነበሩም፡፡ ስለ እነዚህ ምልክቶች ከመጠየቄ በፊት እኔው ራሴ የምልክቶቹን ምንነት ለመረዳት መጣር ፈለግሁ፡፡ ተጫዋቾቹ ሲሰሩት ከነበረው ልምምድ አንጻር ምልክቶቹ የቅብብሎችን ሒደት ትክክለኝነት መጠበቂያ መሆናቸው ገባኝ፡፡ የተሳኩ ቅብብሎች አፍ-አዊ ባልሆነ መንገድ ሜዳ ላይ የመግባባት  መገለጫዎች መሆናቸው እሙን ነው፡፡ የልምምዱ ዓቢይ ዓላማም ይህንኑ ተግባቦት መፍጠር ነበር፡፡    

ሌሎች ጥልቅ ምርምርና ጥናቶችን ሳስስም ጠቃሚ በሆኑ የቅብብል ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በቸልተኝነት ምክንያት ብዙ  እንደሚቀረኝ ተገነዘብኩ፡፡ በአየር የተሞሉ የተጫዋቾች ቅርጽ ያላቸው ምስሎች በልምምድ ሜዳው ላይ እንዲቆሙ ይደረግና በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በ1-4-4-2 ፎርሜሽን የተጋጣሚ ቡድን አማካይ ክፍል እንቅስቃሴያዊ ቦታ አያያዙን እና የመከላከል አደረጃጀትን እንዲወክሉ ይደረጋሉ፡፡ በሜዳው ስፋት በሚሰመሩ የአግድሞሽ መስመሮች በሚደረደሩ ተጫዋች-ወካይ አሻንጉሊቶች አጠገብ ለእያንዳንዳቸው አንድ-አንድ በአጠቃላይ አራት ኮኖች ይቀመጥላቸዋል፡፡ ይህም ሜዳውን በቁመቱ በኩል ሶስት እኩል መጠን ያላቸው መተላለፊያዎች ለማግኘት ይረዳል፡፡ በዚህኛው የልምምድ መርኃግብር ላይ ማርሴሎ ቢዬልሳ በእግርኳስ ለሁሉም እንቅስቃሴዎች እንደ መነሻ የሚጠቀሙባቸውን እጅግ በጣም ወሳኞቹን ምልክቶች ሳስተውል እንደነበር አውቄያለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የልምምድ መርኃግብር ላይ ለአትሌቲክ ቢልባዖ ዋናው ቡድን የተወሰኑ ተጫዋቾች የጨዋታ ምስረታን በሚመለከት ያላቸውን የተዛባ ግንዛቤ ማስተካከያ ይሆን ዘንድ የተለያዩ የአጨዋወት መርህ አማራጮች ማሳያም እንደነበር ለመጠርጠር ጊዜ ወስዶብኛል፡፡

ይቀጥላል…

የመጽሃፉ ደራሲ ጄድ ሳይናን ዴቪስ ይባላል፡፡ ዌልሳዊው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በዋና አሰልጣኝነት፣ በኢስቶኒያ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ በምክትል አሰልጣኝነት ሰርቷል፡፡ የሰላሳ ሁለት ዓመቱ ወጣት በአሁኑ ወቅት <ኦታዋ ፈሪ> በተባለው የካናዳ ክለብ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ከ2019 ጀምሮ በኦታዋ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ የእግርኳስ ፕሮፌሰር ሆኖ Strategy in Association Football ያስተምራል፡፡ ዴቪስ በ2013 ” Coaching the Tiki-Taka Style of Play” የተሰኘ መጽሃፍ አሳትሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ