ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ዲቻ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የነገ ረፋዱ የወላይታ ድቻ እና የሀዲያ ሆሳዕናን ጨዋታ የለተመለከቱ ሀሳቦችን እነሆ ብለናል።

ይህ ጨዋታ የ2012 የውድድር ዓመት መሰረዙ እፎይታ ከሆናቸው ክለቦች መካከል ሁለቱ የሚገናኙበት ነው ማለት ይቻላል። በደመወዝ ጥያቄ ምክንያት ልምምድ አቋርጠው ከጀመሩ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወላይታ ድቻ ሁኔታው በጥቅምት ወር አጋማሽ የጀመረው የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መንፈስ ረብሾት ጥሩ ላልሆነ አጀማመር እንዳይዳርገው ያሰጋል። በአሰልጣኝ ደሳለኝ ደቻሳ የሚመራው ወላይታ ድቻ እዮብ በቀታ፣ ያሬድ ደርዛ፣ ኤልያስ አሕመድ፣ ስንታየሁ መንግሥቱ ፣ አናጋው ባደግ እና ሰዒድ ሀብታሙን በማስፈረም እና የአብዛኞቹ ነባር ተጫዋቾቹን ውል በማደስ አዲሱን የውድድር ዓመት ይጀምራል። ድቻ በቡድን ግንባታው ላይ ነባር ተጫዋቾቹ መኖራቸው የተሻለ ውህደት እንዲኖረው እንደሚረዳው ሲታመን ከዋነኛው የቡድኑ ግብ አዳኝ ባዬ ገዛኸኝ ጋር መለያየቱን ተከትሎ ፊት ላይ ሊፈጠር የሚችልበትን ክፍተት በአግባቡ የመውጣት የቤት ሥራ ይጠብቀዋል። ከዚህ ውጪ እንደስንታየሁ መንግስቱ ፣ ኤልያስ አህመድ እና ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ የመሳሰሉ ተጫዋቼችን በእጁ ማስገባቱ በበድኑ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የመካተት ፉክክሩን ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

በብዙ መልኩ ዳግም በሊጉ ተሻሽሎ የመቅረብ ዕድልን ያገኘው ሀዲያ ሆሳዕና እንደተገመተውም በርካታ ዝውውሮችን ፈፅሟል። ደረጄ ዓለሙ፣ አይዛክ ኢዜንዴ (ዩጋንዳ) ፣ ሊ አዲ (ጋና) ፣ ብሩክ ቀልቦሬ፣ አማኑኤል ጎበና፣ ምኞት ደበበ ፣ ሱሌይማን ሰሚድ ፣ ኃይሌ እሸቱ ፣ አዲስ ህንፃ ፣ ቴዎድሮስ በቀለ ፣ ሚካኤል ጆርጅ ፣ ድንቅነህ ከበደ ፣ ዳዋ ሆቴሳ ፣ አልሀሰን ካሉሻ (ጋና) እና ዱላ ሙላቱም ዘንድሮ በሀዲያ ሆሳዕና መለያ የምንመለከታቸው ተጫዋቾች ናቸው። እንደተጋጣሚው ሁሉ የደመወዝ ጥያቄ እሰጥ አገባ አግኝቶት የነበረው ክለቡ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ ነው ሊጉን የሚጀምረው። ሀዲያ ምንም እንኳን በርካታ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም አብዛኞቹ በአዳማ ከተማ ቡድን ውስጥ አብረው በመጫወት ቆይታ ያደረጉ እና ከአሰልጣኝ አሸናፊ ጋርም አብረው የሰሩ መሆኑ ሲታሰብ ቡድኑን የማዋቀር ሥራው ብዙ እንዳይወሳሰብበት እንደሚረዳው ይታመናል። በነገውም ጨዋታ ምን አልባትም የመጀመሪያው አሰላለፍ በሙሉ በእነዚሁ ተጫዋቾች እንደሚያዝ ይገመታል።

ከጨዋታው በፊት በሀዲያ ሆሳዕና በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና ባይኖርም የወላይታ ድቻዎቹን እዮብ አለማየሁ ፣ ፀጋዬ አበራ እና ያሬድ ዳርዛ በጉዳት ምክንያት ነገ እንደማናያቸው ታውቋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ በድኖች ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ (በ2008) ተገናኝተው ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና 5-1 ፣ ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ 2-0 አሸንፈዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ