“እኔ ከሌላ አባት መወለድን ተመኝቼ አላውቅም” ዳዊት መንግሥቱ ወርቁ

እነሆ ታላቁን የእግር ኳስ ሰው በህይወት ካጣነው 10 ዓመታት ነጎደ። ታኅሣሥ 8 ቀን 2003 የተለየንን የሀገር ባለውለታ በክብር ለማሰብ ከመጨረሻ ልጁ ዳዊት መንግሥቱ ጋር አጭር ቆይታን አድርገናል።

ዛሬ ላይ ሆነን እግርኳሳችን ዝቅ ያለደረጃ ላይ እንደሚገኝ አምነን ለመቀበል ብንገደድም በአንድ ወቅት ግን ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ነበረን። እኛ ክብር መስጠቱን፣ ማስታወሱን፣ መዘከሩን ሰነፍን እንጂ ኢትዮጵያ ጀግና እግርኳሰኞችን ለመውለድ አልሰነፈችም። አሁን ላይ በአውሮፓ ሊጎች ተጫዋቾቻችንን ማየት ህልም ቢመስልም ታላቁ ኤሲ ሚላን እንዲጫወትለት የተመኘው ተጫዋች ግን ነበረን። ጎል ማስቆጠር ለአጥቂዎቻችን ከባድ የቤት ስራ ለኛም ምጥ ቢሆንብንም በአንድ ወቅት ግን ሁለገብ ፣ ኳስን ወደ መረብ መላክን ቀላል ያደረገ ታላቅ አጥቂ ነበረን ፤ መንግሥቱ ወርቁ።

1932 ላይ ተወልዶ ኳስን በተጫዋችነት ፣ በአሰልጣኝነት ፣ በኢንስትራክተርነት ኗሯት ከአስር ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት ያለፈው ታላቁ መንግሥቱ ወርቁን ለማሰብ ከእግርኳሱ ከባቢ ወጣ ማለትን መረጥን። መንግሥቱ እንደሰው ፣ እንደአባት ምን ዓይነት መልክ ነበረው ? ብለንም ከመጨረሻ ልጁ ዳዊት መንግሥቱ ጋር ተከታይዋን አጭር ቆይታ አድርገን ነበር።

ስለቤተሰብ ህይወቱ ?

መንግስቱ 7 ልጆችን ያፈራ ሲሆን በተመሳሳይ 7 የልጅ ልጆችም ነበሩት። የመጀመሪያ ባለቤቱ ሰናይት ትባላለች። ከእርሷም ሦስት ልጆች አፍርቷል። የመጀመሪያ ወንድ ልጁም ወርቁ መንግሥቱ ወርቁ ነው የሚባለው። ከሰናይት በኋላ ደግሞ ከአልማዝ ዓለማየሁ አራት ልጆችን (አንድ ሴት እና ሦስት ወንድ) ወልዷል።

እንደ ልጅ የመንግሥቱን አባትነት እንዴት ትገልፀዋለህ ?

እኔ የመጨረሻ ልጅ ነኝ። ግን ብዙ ትዝታዎች አሉኝ። ለምሳሌ ከኳስ ጋር በተገናኘ ወደ ተለያዩ ሀገራት ሲሄድ እግሬን ወረቀት ላይ አስደግፎ ስሎ ጫማ ያመጣልኝ ነበር። በፊት እነሱ የመጫወቻ ጫማ በዚህ መልክ ስለነበር የሚገዛላቸው እርሱም የእኛን እግር በወረቀት እየያዘ ይሄድ ነበር። ይህ የማልረሳው ነገር ነው። በነገራችን ላይ እኔን በጣም ነበር የሚወደኝ። ልምምድ ቦታ ራሱ ይዞኝ ይሄድ ነበር። ግን ቤት ውስጥ ያለነው ልጆች እንፈራው ነበር። የደከመ ውጤት በትምህርታችን ስናመጣ እርሱ እንዳያየው እናታችን ትደብቅልን ነበር። ወላጅ አምጡም ስንባል እንዳይገርፈን እሱ እንዳይሰማ እናደርግ ነበር። እኔ በግሌ እርሱን እያየሁ ስላደኩ ኳስ ተጫዋች መሆን ነበር የምፈልገው። ግን እሱ በትምህርቴ እንድበረታ ነበር የሚነግረኝ። ‘ኳስ ለእኔስ ምን ጠቀመ ?’ ይለኝ ነበር። ይህንን ግን የሚለኝ ለእኔው አስቦ ነበር። በአጠቃላይ ግን አባታችን ጥሩ አባት ነበር። ሁላችንም በፍቅር ነበር የምንወደው። እሱ ሲሞትም ሁላችንም በጣም አዝነናል።

የሀገር ባለውለታ ልጅ መሆንህ ምን ያስገኘለህ ነገር አለ ?

እኔ ከሌላ አባት መወለድን ተመኝቼ አላውቅም። ለልጄ እንኳን አስተላልፋለሁ ብዬ የማስበው የአባቴን ነገር ነው። ከምንም በላይ የመንግሥቱ ልጅ መሆናችንን ያወቁ ሰዎች በኩል ያገኘነው ነገር ክብር እና ፍቅር ነው። እርግጥ መንግሥቱን የሚያስታውሱ ብዙ ነገሮች የሉም። ግን ታሪክ የሚያውቁ ሰዎች እኛን ሲያገኙን የሚሰጡን ፍቅር እና ክብር ነው። ከዚህ ውጪ ግን የመንግሥቱ ቤተሰብ ናቸው ተብሎ የተጠቀምነው ነገር የለም። እናቴም የምትኖረው በጡረታ ነው። አባቴ በቅዱስ ጊዮርጊስ እያለ ብዙ ነገር ሰርቷል። ከክለብም አልፎ ለሀገር ትልቅ ነገር አበርክቷል። ኃይለሥላሴም “ፊት-አውራሪ” ብለውት ነበር። ይህንን ክብር ያገኘው ለሀገር ባበረከተው ነገር ነው። ግን ከተማ መስተዳድሩ እና እግርኳስ ፌዴሬሽናችን መንግሥቱን የሚዘክር ነገር ምንም አላደረጉም። በፊት እንደውም የካፍ ኢንስትራክተር ሆኖ አሠልጣኞችን እንዲያሰለጥን ተመርጦ ሲሄድ ወጪውን በራሱ ሸፍኖ በፌዴሬሽን በኩል ለእርሱ መሰጠት ያለበት ክፍያ ሲቀር እንደነበረም አስታውሳለው።

በመንግሥቱ ዙሪያ ብዙ ያልተነገረ እና ያልተፃፈ ነገር ካለ ?

አንድ ጊዜ ሲያወራ የሰማሁት ነገር አለ። ዝርዝሩን በደንብ ባላቀውም የማስታውሰውን ልንገርህ። ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ሩዋንዳ ሄደው ነበር። በጊዜው ሩዋንዳ በቀኝ ግዛት ስር የነበረች ሀገር ነበረች። እናም ሆቴሎች ላይ ‘ጥቁር እና ውሻ መጠቀም አይችልም’ (Blacks and Dogs are not allowed) የሚል ፅሁፍ ነበር። ደግሞ እነ መንግሥቱ የተያዘላቸው ሆቴል ይህ ህግ የተፃፈበት ነበር። ወደ ሆቴሉም ገብተው እራት ደርሶ ወደ መመገቢያ ስፍራ ተጉዘው ሊበሉ ሲሉ የሚታዘዛቸው ጠፋ። በመከራ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ተጠርቶ ከታዘዙ በኋላ በዘረኝነቱ ተናደው የመጣላቸውን ሾርባ ጠረቤዛ ላይ ደፍተውት ወጥተው ሌላ ቦታ በልተው ተመለሱ። ይህንን ያደረጉት በዘረኝነት ተግባሩ ስለተበሳጩም እንደነበር ሲያወራ ሰምቻለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ