ፍቅሩ ተፈራ ወደ ሀገሩ ስለተመለሰበት ምክንያት ይናገራል

በሀገር ውስጥ በተለያዩ ክለቦች ከተጫወተ በኋላ ባለፉት 15 ዓመታት በ3 አህጉራት በሚገኙ ክለቦች ተዟዙሮ በመጫወት ዓለምን ያካለለው ግዙፉ አጥቂ ፍቅሩ ተፈራ ወደ ሀገሩ የተመለሰበትን ምክንያት ይናገራል።

በኢትዮጵያ ተጫዋቾች ታሪክ ለረጅም ጊዜያት በውጭ ሃገራት ሊጎች በመጫወት በተለይም በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሚስተካከለው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች የሌለው ፍቅሩ ተፈራ ወደ ሀገሩ መመለሱን ዛሬ በሸገር ደርቢ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ተመልክተናል። ያለፈውን አንድ ዓመት ከዕይታ የራቀው ፍቅሩ አሁን በምን ሁኔታ እንደሚገኝ እና በቀጣይ ስለሚያስበው እቅዱ አጭር ቆይታ አድርገናል።

” ወደ ሀገሬ ከመጣሁ ጥቂት ቀናት ሆኖኛል ፤ ኢትዮጵያም ትንሽ እቆያለው። በመጨረሻ የተጫወትኩት ህንድ ነበር። የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ እግርኳስን እየተጫወትኩ አይደለም። እነርሱ መጥቼ እንድጫወት ይፈልጋሉ። እኔ ግን እግርኳስ ወደ ማቆሙ ተቃርቤያለው። ምክንያቴ ደግሞ የወሰድኳቸው የአሰልጣኝነት ኮርሶች አሉ፤ በዛ ሀገሬ የመስራት ፍላጎት አለኝ። አንዳንድ እየሞከርኳቸው ያሉ ነገሮች አሉ። ሁኔታዎች ከተመቻቹ በሀገሬ በአሰልጣኝነቱ የመሥራት እቅድ አለኝ። ይህ ካልተሳካ ግን ወደ ደቡብ አፍሪካ በመሄድ እዛ ያሰብኳቸው ነገሮች አሉ። እርሱን የምከውን ይሆናል።”

በአየር ኃይል፣ አዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ግዙፉ አጥቂ እ.ኤ.አ. በ2006 ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቅቆ ኦርላንዶ ፓይሬትስን ከተቀላቀለ በኋላ በ3 አህጉራት በሚገኙ ክለቦች መጫወት ችሏል። የተጫወተባቸው ክለቦች እና ሀገራት የሚከተሉት ናቸው:-

ኦርላንዶ ፓያሬትስ (ደቡብ አፍሪካ) ማልዳ ቦልስላቭ (ቼክ ሪፐብሊክ)፣ ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ (ደቡብ አፍሪካ)፣ ኩፕስ (ፊንላንድ)፣ ታን ሆአ (ቬትናም)፣ ፍሪስቴት ስታርስ፣ ፕሪቶሪያ (ደቡብ አፍሪካ)፣ ሚላኖ ዩናይትድ (ደቡብ አፍሪካ)፣ አትሌቲክ ኮልካታ (ህንድ)፣ ቢድቬትስ ዊትስ (ደቡብ አፍሪካ)፣ ቼኔይን (ህንድ)፣ ሼይክ ረስል (ባንግላዴሽ)፣ ሃይላንድስ ፓርክ  (ደቡብ አፍሪካ)፣ ሞሐመዳን (2010/ህንድ)


© ሶከር ኢትዮጵያ