ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ አንደኛ ሳምንት ላይ የተመረኮዙ ዕውነታዎች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲህ አጠናቅረናል።

– በ11ኛ ሳምንት በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች 14 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም ባለፈው ሳምንት ከተቆጠረው በሁለት ያነሰ ነው።

– ከ14 ጎሎት መካከል አምስቱ ብቻ በመጀመርያ አጋማሽ ሲቆጠሩ ዘጠኙ ጎሎች ከዕረፍት በኋላ ተቆጥረዋል።

– ኢትዮጵያ ቡና አምስት ጎሎች ተጋጣሚው ላይ በማስመቆጠር የሳምንቱን ብሎም የዓመቱን ከፍተኛ ቁጥር አስመዝግቧል።

– ከተቆጠሩት ጎሎች መካከል (2) ዳዊት እስጢፋኖስ እና አቡበከር ናስር በፍፁም ቅጣት ምት፣ (1) ዳዋ ሆቴሳ በቅጣት ምት ከተቆጠሩ ጎሎች ውጪ ሌሎቹ በክፍት ጨዋታ ተቆጥረዋል።

– ዳዋ ሆቴሳ ካስቆጠረው የቅጣት ምት በስተቀር ሌሎቹ አስራ ሦስት ጎሎች የተቆጠሩት በሳጥን ውስጥ ተመትተው ነው።

– ምንይሉ ወንድሙ ጅማ ላይ በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠራት ጎል የሳምንቱ ብቸኛ የግንባር ኳስ ጎል ናት።

– 10 ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት ጎል አስቆጥረዋል። አቡበከር ናስር በሦስት ጎል ቀዳሚ ሲሆን ተመስገን ደረሰ በሁለት ተከታዩን ይዟል።

– በረከት ደስታ እና ሄኖክ አዱኛ የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ጎላቸውን ያስቆጠሩት በዚት ሳምንት ጨዋታዎች ነው።

– ስምንት ተጫዋቾች በጎል ማመቻቸት ተሳትፎ አድርገዋል። አቡበከር ናስር ሁለት በማመቻቸት ቀዳሚ ነው።

– ጎል በማስቆጠርም በማመቻቸትም የተሳተፉ ተጫዋቾች ሁለት ሲሆኑ አቡበከር ናስር (3 ጎል / 2 አሲስት) ቀዳሚ ነው። አሥራት ቱንጆ ደግሞ አንድ ጎል እና አንድ አሲስት አስመዝግቧል።

– ዳዋ ሆቴሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ያስቆጠረው ጎል ሁለተኛ የቅጣት ምት ጎሉ ነው። ይህም ከሊጉ ተጫዋቾች ቀዳሚ ያደርገዋል።

– ሀዲያ ሆሳዕና ከአራት ተከታታይ ጨዋታ በኋላ ግብ አስተናግዷል። በተመሳሳይ ተጋጣሚው የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስም ከሦስት ጨዋታ በኋላ ጎል ተቆጥሮበታል።

– ፋሲል ከነማ ለአምስተኛ ተከታታይ ጨዋታ መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት የዓመቱን ከፍተኛ ቁጥር አስመዝግቧል። አምስተኛ ተከታታይ ድላቸውም ከፍተኛ ቁጥር ነው።

– ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል።

– ሙጂብ ቃሲም ከሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ጎል ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል።

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በአስራ አንደኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች 18 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲመዘዙ ምንም የቀይ ካርድ አልታየም።

– ሀዲያ ሆሳዕና በሦስት ቢጫ ካርዶች ከፍተኛ ቁጥር ሲያስመዘግብ አዳማ ከተማ ምንም ካርድ ያልተመለከተ ቡድን ነው።

የአቡበከር ናስር ቁጥሮች

– ባለፉት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል አስቆጥሮ ወጥቷል። ይህም በዚህ ዓመት ሰባት ተከታታይ ጨዋታ ካስቆጠረው ሙጂብ ቃሲም ጋር በአንድ ያነሰ ነው።

– በአንድ የውድድር ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ሐት-ትሪክ መሥራቱን ተከትሎ ይህን ሪከርድ ለመጨረሻ ጊዜ በ2010 ኦኪኪ አፎላቢ (አርባምንጭ እና አዳማ ከተማ ላይ) ካስመዘገበ በኋላ የመጀመርያ ተጫዋች ሆኗል።

– ሲዳማን 5-0 በረቱበት ጨዋታ ላይ አቡበከር ናስር ሁሉም ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። (ሦሰት ጎል እና ሁለት አሲስት) ይሆም በውድድር ዓመቱ ከፍተኛው ቁጥር ነው።

– አቡበከር በዚህ ዓመት ከወዲሁ ያስቆጠራቸው ጎሎች ባለፈው ዓመት እስከ አስራ ሰባተኛው ሳምንት ካስቆጠረው ጎል መጠን በስድስት ከፍ ያለ ሲሆን በእግርኳስ ህይወቱ በርካታ ጎሎች ካስቆጠረበት የ2011 የውድድር ዓመት (11 ጎሎች) ከወዲሁ በሦስት የላቀ ነው።

– በኢትዮጵያ ቡና እስካሁን ሦስት ሐት-ትሪኮችን የሰራው አቡበከር (አንዱ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ነው) ሁሉንም ያከናወነው ቡድኑን በአምበልነት ሲመራ መሆኑ አጋጣሚውን አስገራሚ ያደርገዋል።

የሳምንቱ ስታቶች

(ቁጥሮቹ የተገኙት ከሱፐር ስፖርት ነው)

ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ

ከፍተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (9)
ዝቅተኛ – ወልቂጤ ከተማ (1)

ጥፋቶች

ከፍተኛ – ወልቂጤ ከተማ (29)
ዝቅተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (11)

ከጨዋታ ውጪ

ከፍተኛ – አዳማ ከተማ (8)
ዝቅተኛ – ሆሳዕና እና ጊዮርጊስ (1)

የማዕዘን ምት

ከፍተኛ – ባህር ዳር ከተማ (7)
ዝቅተኛ – ወልቂጤ እና ሆሳዕና (1)

የኳስ ቁጥጥር ድርሻ

ከፍተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (64%)
ዝቅተኛ – ሲዳማ ቡና (36%)


© ሶከር ኢትዮጵያ